የመጋቢት 06/2012 ዓ.ም ሰንበት ዘመፃጉዕ ቃለ እግዚኣብሔር አስተንትኖ
“እነሆ ተፈውሰሃል! ከእንግዲህ ወዲህ ግን ኀጢአት አትሥራ፤ አለበለዚያ ግን ከዚህ የባሰ ይደርስብሃል”
የእለቱ ምንባባት
1. ገላቲያ 5፡1-26
2. ያዕቆብ 5፡14-20
3. ዩሐንስ 5፡1-24
የእለቱ ቅዱስ ወንጌል
በቤተ ሳይዳ የተደረገው ፈውስ
ከዚህ በኋላ የአይሁድ በዓል ነበረ፤ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። በኢየሩሳሌም፣ በበጎች በር አጠገብ፣ አምስት ባለ መጠለያ መመላለሻዎች የነበሯት፣ በአራማይክ ቋንቋ ቤተ ሳይዳ የተባለች አንዲት መጠመቂያ አለች። በእነዚህም መመላለሻዎች ውስጥ ብዙ አካለ ስንኩላን፣ ዐይነ ስውሮች፣ አንካሶችና ሽባዎች ይተኙ ነበር። [የውሃውንም መንቀሳቀስ እየተጠባበቁ፣ 4ዐልፎ ዐልፎ የጌታ መልአክ ወርዶ ውሃውን በሚያናውጥበት ጊዜ፣ ቀድሞ ወደ መጠመቂያዪቱ የገባ ካደረበት ማንኛውም በሽታ ይፈወስ ነበር።] በዚያም ለሠላሳ ስምንት ዓመት ሕመምተኛ ሆኖ የኖረ አንድ ሰው ነበር። ኢየሱስም ይህን ሰው ተኝቶ ባገኘው ጊዜ፣ ለብዙ ጊዜ በዚህ ሁኔታ እንደ ነበር ዐውቆ “ልትድን ትፈልጋለህን?” አለው።
ሕመምተኛውም መልሶ፣ “ጌታዬ፣ ውሃው በሚናወጥበት ጊዜ ወደ መጠመቂያዪቱ የሚያወርደኝ ሰው የለኝም፤ ለመግባትም ስሞክር ሌላው ይቀድመኛል” አለው።
ኢየሱስም፣ “ተነሥ! መተኛህን ተሸክመህ ሂድ” አለው። ሰውየውም ወዲያው ተፈወሰ፤ መተኛውንም ተሸክሞ ሄደ። ይህም የሆነው በሰንበት ቀን ነበር። አይሁድም የተፈወሰውን ሰው፣ “ሰንበት ስለ ሆነ መተኛህን እንድትሸከም ሕጉ አይፈቅድልህም” አሉት። እርሱ ግን፣ “ያ የፈወሰኝ ሰው፣ ‘መተኛህን ተሸክመህ ሂድ’ ብሎኛል” ሲል መለሰላቸው። እነርሱም፣ “ ‘መተኛህን ተሸክመህ ሂድ’ ያለህ እርሱ ማነው?” ብለው ጠየቁት። ኢየሱስ ፈቀቅ ብሎ ወደ ሕዝብ መካከል ገብቶ ስለ ነበር፣ ሰውየው ማን እንደፈወ ሰው አላወቀም።
ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ያን ሰው በቤተ መቅደስ አግኝቶ፣ “እነሆ፣ ተፈውሰሃል፤ ከእንግዲህ ግን ኀጢአት አትሥራ፤ ያለዚያ ከዚህ የባሰ ይደርስብሃል” አለው። ሰውየውም የፈወሰው ኢየሱስ መሆኑን ሄዶ ለአይሁድ ነገራቸው።
ወልድ ሕይወትን ይሰጣል
አይሁድም፣ በሰንበት ቀን እነዚህን ድርጊቶች በመፈጸሙ፣ ኢየሱስን ያሳድዱት ነበር። ኢየሱስም፣ “አባቴ እስካሁን እየሠራ ነው፤ እኔም ደግሞ እሠራለሁ” አላቸው። እንግዲህ አይሁድ፣ ኢየሱስ ሰንበትን ስለሻረ ብቻ ሳይሆን፣ እግዚአብሔርን አባቱ በማድረግ፣ ራሱን ከእግዚአብሔር እኩል በማድረጉ፣ ሊገድሉት አጥብቀው ይፈልጉት ነበር።
ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ አብ ሲሠራ ያየውን ብቻ እንጂ ወልድ ከራሱ ምንም ሊያደርግ አይችልም፤ አብ የሚያደርገውን ሁሉ ወልድ ደግሞ ያደርጋልና፤ አብ ወልድን ስለሚወድ የሚያደርገውን ሁሉ ያሳየዋል፤ ትደነ ቁም ዘንድ ከእነዚህም የሚበልጥ ነገር ያሳየዋል። ምክንያቱም አብ ሙታንን እንደሚያስነሣ፣ ሕይወትንም እንደሚሰጥ፣ ወልድም ደግሞ ለሚፈቅደው ሁሉ ሕይወትን ይሰጣል። አብ በማንም ላይ አይፈርድም፤ ነገር ግን ፍርድን ሁሉ ለወልድ አሳልፎ ሰጥቶታል፤ ይኸውም፣ ሁሉ አብን እንደሚያከብሩ ወልድን ያከብሩት ዘንድ ነው፤ ወልድን የማያከብር፣ የላከውን አብንም አያከብርም።
“እውነት እላችኋለሁ፤ ቃሌን የሚሰማ፣ በላከኝም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ ከሞት ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም።
የሰንበት ዘመፃጉዕ ቃለ እግዚኣብሔር አስተንትኖ
በክርስቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!
ዛሬ እንደ ቤተ ክርስቲያናችን የሥርዓተ አምልኮ አቆጣጠር መሠረት ዘመፃጕዕ የተሰኘውን ሰንበትን እናከብራለን። በዚህም ዕለት በተለይ አሁን በምንገኝበት የዐብይ ጾም ወቅት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዴት ይበልጥ ወደ እርሱ መቅረብ እንደምንችል እንዴት ከኃጢአት በመራቅ መንፈሳዊ እሴቶቻችንን ማሳደግ እንደምንችል መንገዱን ያሳየናል፡፡
በመጀመሪያው ንባብ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ለገላቲያ ሰዎች በጻፈው መልዕክቱ “በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢያት ቀንበር ነፃ ወጥተናል፣ ከሞት ፍርድም ድነናል ከእስራትም ተፈትተናል ታዲያ ወደ ግዞትና ወደ ኃጢያት ባርነት ተመልሰን የምንሔደው ለምንድን ነው?” በማለት ይጠይቀናል። የገላትያ ሰዎች በመልዕክቱ እንዳዳመጥነው ለግርዘት ሥርዓት ትልቅ ቦታን ይሰጡ ነበር፣ ሰው ስለተገረዘ ብቻ የሚድን ይመስላቸው ነበር። ሰው ስለተገረዘና ሕግን ስለጠበቀ ብቻ የሚድን ይመስላቸው ነበር። ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ዛሬ እንደሚያስተምረን ግን መገረዝ ወይንም አለመገረዝ ወይንም በክርስቶስ አምኖ መጠመቅ ብቻውን ሊያድነን እንደማይችል ያሰምርበታል።
ቅዱስ ሐዋርያው ያዕቆብ በመልእክቱ “እምነት ራሱን በፍቅር አማካኝነት ይገልፃል ከሥራ የተለየ እምነት ቢኖር ደግሞ ይህ እምነት በራሱ የሞተ ነው ይላል” (ያዕ. 2፡17)። እምነታችን ዘወትር ከሥራችን ጋር አብሮ ሊሄድ ያስፈልጋል። አብርሃም በእግዚአብሔር ላይ የነበረውን ጠንካራ እምነት አንድያ ልጁን ይስሐቅን ባለማመንታት ለመሥዋት በማቅረብ በምግባሩ እምነቱን ማስመስከሩን ልናስታውስ ይገባል። ስለዚህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዛሬ ይህንን እምነት በእኛ ሕይወት ውስጥ መመልከት ይፈልጋል፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዛሬ ይህ እምነት በእኛ በእያንዳዳችን ሕይወት ውስጥ ነፍስ ሲዘራ መመልከት ይፈልጋል።
“ዛሬ እኔ እምነቴን፣ ክርስቶስን መውደዴን ክርስቶስን ማወቄን በሥራዬ አሳያለሁን? ወይንስ ደግሞ በክርስቶስ አምኜ ተጠምቄያለሁና ይህ ብቻ ይበቃኛል ብዬ እጄንና እግሬን አጣጥፌ ተቀምጫለሁ?”። ወይንስ ደግሞ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደም አንድ ጊዜ ከኃጢአቴ ሁሉ ተፈትቻለሁና እንደ ፈቀደኝ እኖራለሁ በማለት ራሴን አታልላለሁ?
እንዲህ የማስብ ከሆነ በእርግጥም ተሳስቻለው ምክንያቱም ክርስቶስን መውደዴ ይሁን ክርስቶስን ማወቄ የግድ በሥራዬ የግድ በዕለታዊ ኑሮዬ መመስከር ይገባኛል። አንድ ሰው ክርስቶስን መውደዱ የሚረጋገጠው የእርሱን ቃል ሲፈፅም ብቻ ነው የእርሱን ትዕዛዝ ሲቀበል ብቻ ነው። የዮሐንስ ወንጌል 14፣23 ላይ የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል ይላል፡፡ አዎ ክርስቶስን መውደዴ ይሁን ክርስቶስን ማወቄ በተግባር ላይ ካልዋለ በተግባር ካልታየ 10 ጊዜ አምናለሁ አምናለሁ አምናለሁ ማለቱ ብቻ ምንም ዋጋ አይኖረውም። “ከሥራ የተለየ እምነት ብቻውን ምንም ዋጋ እንደሌለው ሁሉ የእኔም ክርስቶስን መውደድ የእኔ ክርስቶስን ማወቅ የእኔ አምናለሁ ማለት ከዕለታዊ ኑሮዬ ጋር ካልተዛመደ ምንም ዋጋ አይኖረውም”።
በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደም በመታጠባችን በእርግጥ ሁላችን ነፃነት ያለን ሰዎች ነን። ነገር ግን ይህን ነፃነታችንን ኃጢያት ለማድረግና ክፉ ልንሰራበት አይገባም። ነፃነታችንን ተጠቅመን ኃጢያት ከሠራን ነፃነታችንን ተጠቅመን ክፋትን ካዘወተርን ውስጣችን በኃጢያት ይሞላልናል በቀላሉ የሰይጣን ተባባሪዎች እንሆናለን - በቀላሉ የሰይጣን ወጥመድ ውስጥ እንወድቃለን። በገላትያ 5፣1 ላይ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ነፃነታችሁ የሥጋን ምኞት መፈፀሚያ ምክንያት አይሁን እያለ ይመክረናል ስለዚህ ነፃነታችን የቅድስናችን ምንጭ እንጂ የውድቀታችን ምክንያት ሊሆን አይገባም።
በአንፃሩ ነፃነታችንን ተጠቅመን መልካም ሥራን የሠራን እንደሆነ ደግሞ በመንፈስ ቅዱስ እንሞላለን የእግዚአብሔር ወዳጆች የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያዎች እንሆናለን። ይህ ነው እምነትን በተግባር ማስመስከር ማለት ይህ ነው ክርስቶስን መውደድ ማለት ይህ ነው ክርስቶስን ማወቅ ማለት። እግዚአብሔርን መውደድ ማለት በእርሱ አምሳል የተፈጠረውን ሁሉ መውደድ ማለት ነው በእርሱ አምሳል የተፈጠረውን ሁሉ ያለ ምንም መድልዎ ያለ ምንም ልዩነት ማፍቀር ማለት ነው፡፡ ተፈጥሮንም ሁሉ በሚገባ መንከባከብ ማለት ነው።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴዎስ ወንጌል 25፣45 ላይ “ከእነዚህ ለታናናሾች ለአንዱ ያደረጋችት ለእኔ እንዳደረጋችሁት ይቆጠራል” ይለናል። ሰውን ጠልተን እግዚአብሔርን መውደድ አንችልም ይህን ብናደርግ ስህተተን እንናገራለን። በትክክለኛ እምነት ባንኖር በመንፈስ ቅዱስ ባንመራ ራሳችንን የእግዚአብሔር ልጆች ወይንም ደግሞ ከእግዚአብሔር ጋር ሕብረት እንዳለን አድርገን መቁጥር አንችልም።
ከመንፈስ ቅዱስ አብረን ለመጓዝ የምንፈልግ ከሆነ ኃጢያተኛ እኛነታችንን ተቆጣጥረን ዘወትር በንስሃ በመታገዝ ከኃጢያት ርቀን መኖር ይገባናል። ይህ መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን ከሌለ ግን የኃጢያት ተገዢዎች እንሆናለን፡፡ ይህ መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን ከሌለ ሥጋዊ ፍላጎታችን በመንፈሳዊ ባሕሪያችን ላይ ተፅዕኖ በማሳደር ዘወትር የሥጋችንና የሥሜታችን ብቻ ተገዢዎች እንሆናለን።
ውስጣችን በኃጢያት በተሞላ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን ማረፊያ ቦታ ስለማያገኝ ወደ ውስጣችን አይዘልቅም ሥለዚህ ይህን ኃጢያተኛ ባህራያችንን ዘወትር በምስጢረ ንሰሀ ልንቆጣጠረው ይገባል በዚህ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን ማረፊያ ቦታ ያገኛል ዘወትር በለመለመው መስክም ይመራናል እምነታችንንም በሥራ ላይ የምንተረጉምበትን እውነተኛ ጸጋና ኃይል ይሰጠናል።
እውነተኛ እምነት በመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች የተከበበ ነው እነርሱም በገላ 5፣22 ላይ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ እንደገለፀው ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ደግነት፣ በጐነትና ታማኝነት ናቸው። ማንኛውም ክርስቲያን በእግዚአብሔር ላይ የጠበቀ እምነት አለኝ ካለ እነዚህን የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች በውስጡ ይዞ ሊጓዝ ይገባል፡፡ እያንዳዱ ሰው እምነቱ ምን ያህል ጠንካራ መሆኑን የሚከተሉትን ጥያቄዎች ራሱን በመጠየቅ መፈተሽ ይችላል፡፡ “ምን ያህል ባልእንጀራዬን አፈቅራለው?፣ ሕይወቴስ በፍቅር፣ በደስታ፣ በሰላም፣ በትዕግሥት የተሞላ ነውን? ታጋሽነቴስ እስከምን ድረስ ነው? የሚደርስብኝን ማንኛውንም ዓይነት ክፉ ነገር በመልካም ለማሸነፍ ተነሳሽነቴስ ምን ይመስላል? ካለኘ ነገር ላይ ለሌለው በማካፈል ደግነትን አደርጋለሁን? ለእራሴ እንዲሁም ለእምነቴስ ምን ያህል ታማኝ ነኝ? የተሰጠኝንስ ኃላፊነትስ ምን ያህል እወጣለሁ?
ለእነዚህና ለመሳሰሉት ጥያቄዎች የምሰጠው መልስ እምነቴ ምን ያህል ጠንካራ ይሁን አይሁን በአጠቃላይ ያለበትን ደረጃ ያስተውሰናል። በዮሐንስ ወንጌል 5፡1-24 ጠንካራ እምነት ምን ያህል ኃይል እንዳለው- በዚህ 38 ዓመት ታሞ ይሰቃይ በነበረው ሰው ሕይወት ታሪክ ውስጥ እናያለን፡፡በዕብራይስጥ ቤተሳይዳ በምትባል መጠመቂያ ሥፍራ ብዙዎች እየመጡ ይፈወሱ ነበር ሰውየው ግን ካለበት ደዌ አንፃር ሮጦ ወደሚንቀሳቀሰው የኩሬ ውኃ ገብቶ ለመፈወስ አልቻለም ነበር። ነገር ግን እየሱስ ሰውዬው ያለበትን ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት በእርሱ እንደሚያምን እንኳን ሳይጠይቀው ፈውስን ሰጠው። ይህ 38 ዓመት ሙሉ አንድ ቀን ወደሚንቀሳቀሰው ውኃ ለመግባትና ለመፈወስ እምነትን ሰንቆ ይጓዝ የነበረው ሰው ዛሬ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ሕልሙ ተፈታ ጥያቄው ተመለሰለት።
ይህም እያንዳዳችን ባልተመለሱልን ጥያቄዎችና ባልተፈቱልን እንቆቅልሾች መቼም ቢሆን ተስፋ መቁረጥ እንደሌለብን ያስተምረናል። በእግዚአብሔር ላይ ያለን እምነታችን ጠንክሮ መጓዝ ያለበት ነገሮችን ስላደረገልን ነገሮች ስላመቻቸልን ብቻ ሳይሆን ባልተመቻቸም ሁኔታ በሚያስፈራ ማዕበል ውስጥ እንኳን ብንሆን እምነታችን ሁሌም የጸና ሊሆን ይገባል። ምክንያቱም በማቴዎስ ወንጌል 24፣13 ላይ እስከ መጨረሻ በትዕግስት የሚፀና ግን ይድናል ይላል።
እምነታችን ጠንካራ በሆነ መጠን ፈተናውም የዛን ያህል የበዛና የጠነከረ ይሆናል ምክንያቱም ሰይጣን የእኛን በእምነት መጠንከር በጣም ስለሚቃወም ይህንንም ጠንካራ እምነት ለመሰባበር ዘወትር በዙሪያችን እንደተራበ አንበሳ እያደባ ይዟዟራልና ነው። ነገር ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተናገረን ቃሉን ብንሰማ በእርሱም ብናምን በቃሉም ብንፀና የዘለዓለም ሕይወት እንደሚኖረን ቃል ገብቶልናል የቱንም ዓይነት የሰይጣን ፈተና እንደማያሸንፈን አረጋግጦለናል። ስለዚህ ለእርሱ ቃል በመታመን ለእርሱ ትዕዛዝ ተገዢ በመሆን የቅድስና ጉዞአችንን ወደፊት እንቀጥል።
ለዚህም ደግሞ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የክርስቲያኖች ረዳት የሆነች ከልጇ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን ፀጋና በረከር ታማልደን።
ምንጭ፡ የቫቲካን ሬዲዮ የአማርኛ አገልግሎት ክፍል
አቅራቢ መብራቱ ሀ/ጊዮርጊስ ቫቲካን