የግንቦት 09/2012 ዓ.ም የ5ኛው የፋሲካ ሳምንት ሰንበት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ
ወደ ዘለዓለም ሕይወት የምመራን መንገድ ኢየሱስ ብቻ ነው በእርሱ እንመን
የዕለቱ ንባባት
1. የሐዋርያት ሥራ 6፡ 1-7
2. መዝሙር 32
3. 1ጴጥሮስ 2፡4-9
4. ዮሐንስ 14፡ 1-12
የዕለቱ ቅዱስ ወንጌል
“ልባችሁ አይጨነቅ፤ በእግዚአብሔር እመኑ ፤ በእኔም ደግሞ እመኑ። በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ ይህ ባይሆንማ ኖሮ እነግራችሁ ነበር፤ የምሄደውም ስፍራ ላዘጋጅላችሁ ነው። ሄጄም ስፍራ ካዘጋጀሁላችሁ በኋላ፣ እኔ ባለሁበት እናንተም ከእኔ ጋር እንድትሆኑ ልወስዳችሁ ዳግመኛ እመጣለሁ። እኔ ወደምሄድበትም ስፍራ የሚያደርሰውን መንገድ ታውቃላችሁ።”
ወደ አብ የሚያደርሰው መንገድ
ቶማስም፣ “ጌታ ሆይ፤ ወዴት እንደምትሄድ አናውቅም፤ ታዲያ፣ መንገዱን እንዴት ማወቅ እንችላለን?” አለው። ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “መንገዱ እኔ ነኝ፤ እውነትና ሕይወትም እኔው ነኝ፤ በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም። እኔን ብታውቁኝ ኖሮ አባቴንም ባወቃችሁት ነበር። ከአሁን ጀምሮ ግን ታውቁታላችሁ፤ አይታችሁታልም።” ፊልጶስም፣ “ጌታ ሆይ፤ አብን አሳየንና ይበቃናል” አለው። ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “አንተ ፊልጶስ! ይህን ያህል ጊዜ ከእናንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን? እኔን ያየ አብን አይቶአል፤ እንዴትስ፣ ‘አብን አሳየን’ ትላለህ? እኔ በአብ እንዳለሁ፣ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን? የምነግራችሁ ቃል ከራሴ አይደለም፤ ነገር ግን ሥራውን የሚሠራው በእኔ የሚኖረው አብ ነው። እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ ስነግራችሁ እመኑኝ፤ ሌላው ቢቀር ስለ ድንቅ ሥራዎቹ እንኳ እመኑ። እውነት እላችኋለሁ፤ በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ ይሠራል፤ እንዲያውም እኔ ወደ አብ ስለምሄድ፣ ከእነዚህም የሚበልጥ ያደርጋል።
የዕለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ
ውድ ወንድሞች እና እህቶች እንደምን አረፈዳችሁ!
በዛሬው ቅዱስ ወንጌል (ዮሐ 14፡ 1-12) የኢየሱስን “የመሰናበቻ ንንግር” ጅማሬ እንሰማለን። ከመጨረሻው እራት ማቢቂያ ላይ እና መከራውን መቀበል ከመጀመሩ በፊት የተናገራቸው ቃላት ናቸው። በእንደዚህ ዓይነት አስገራሚ ቅጽበት ኢየሱስ ንግግሩን የጀመረው “ልባችሁ አይጨነቅ” (ዩሐንስ 14፡1) በማለት ነበር። በህይወት ድራማዎችም መካከል ለምንገኝ ለእኛም በተመሳሳይ መንገድ ይናገረናል። ነገር ግን ልብ እንዳይሸበር እንዴት ማድረግ እንችላለን? ምክንያቱም ልብ ይሸበራልና።
ጌታ ልባችን እንዳይሸበር የሚረዳ ሁለት መፍትሄዎችን ጠቁሟል። የመጀመሪያው “እምነት ይኑራችሁ” (ዩሐንስ 14፡ 1) የሚለው ነው። ይህ ደግሞ ትንሽ ሥነ-ልቦናዊ ፣ ረቂቅ የሆነ ምክር ይመስላል። በምትኩ ፣ ኢየሱስ አንድ የተወሰነ ነገር ሊነግረን ይፈልጋል። በህይወት ውስጥ እጅግ በጣም መጥፎ ጭንቀት ፣ ሁከት የሚመጣው ነገሮችን የመጋፈጥ ስሜት ስናጣ፣ ብቸኝነት ሲሰማን እና እየተከሰቱ በሚገኙ ነገሮች ፊት ለፊት የማጣቀሻ ነጥቦች ስናጣ እንደ ሆነ ያውቃል። ይህ ጭንቀት በችግር ላይ ችግር በመደራረብ ጭንቀትን በመፍጠር ለብቻችን የምንቋቋመው ነገር ላይሆን ይችላል። የኢየሱስ እርዳታ ያስፈልገናል፣ እናም በዚህ ምክንያት ኢየሱስ በእርሱ ላይ እምነት እንዲኖረን ይጠይቃል ፣ ይህም በእኛ ጉልበት ሳይሆን በእርሱ ላይ መታመናችን ነው። በኢየሱስ ላይ እምነት ይኑረን። እናም ይህ ከጭቀት ነጻ ያወጣናል። ከሙታን የተነሳው እና ሕያው የሆነው እየሱስ ሁሉ ጊዜ ከእኛ ጎን ሆኖ አብሮን ይጓዛል። ከዚያ እንዲህ ማለት እንችላለን: - “ኢየሱስ ሆይ ፣ በእውነት ተነስተሃል እንዲሁም ከእኔ አጠገብ እንደሆንክ አምናለሁ። እንደምታዳምጠኝ አምናለሁ። የሚያስጨንቀኝን ነገር ሁሉ ወደ አንተ አቀርባለሁ፣ በአንተ አምናለ፣ በአንተ እተማመናለሁ”።
ከእዚያም ኢየሱስ በእነዚህ ቃላት የገለጠው ለተፈጠረው ሁከት ሁለተኛው መፍትሄ አለ “በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያዎች አሉ […] እኔ ቦታ እዘጋጃለሁ ”(ዩሐንስ 14፡2) ይለናል። ኢየሱስ ለእኛ ያደረገልን ነገር ይህ ነው - በመንግሥተ ሰማይ አንድ ቦታ አዘጋጅቶልናል። እሱ ሰብዓዊነታችንን ውስዶ እኛን ከሞት ባሻገር ለማሻገር፣ ወደ አንድ አዲስ ስፍራ ወደ መንግሥተ ሰማይ ሊወስድን ፈለገ፣ ምክንያቱም እርሱ በሚኖርበት በእዚያ ስፍራ እኛም ከእርሱ ጋር እንድንሆን ይፈልጋል። የሚያጽናናን እርግጠኛ የሆነ ነገር ነው-ለእያንዳንዳችን የተዘጋጀ አንድ ቦታ አለ። ለእኔም የተወሰነ ቦታ አለ። አንድ ቦታ አለ! እያንዳንዳችን ማለት እንችላለን አንድ የተወሰነ ቦታ አለን። ለእኔም አንድ ቦታ አለ። እኛ የምንኖረው ያለ ዓላማ እና ያለ መዳረሻ አይደለም። እግዚአብሔር ይወደናል። ለእኛም እጅግ ተስማሚ እና ቆንጆ የሆነ ሥፍራ አዘጋጅቷል። መዘንጋት የለብንም-የሚጠብቀን መኖሪያ መንግሥተ ሰማይ ነው። ይህ ምድር መሸጋገሪያችን ነው። እኛ የተፈጠርነው ለዘለዓለም እንድንኖር ነው ፣ ለዘለዓለም ሕይወት ነው። ለዘላለም: - አሁን እንኳን ማሰብ የማንችለው ነገር ነው። ነገር ግን ይህ ለዘላለም ፣ ለዘላለም ከእግዚአብሄር እና ከሌሎች ጋር ፣ ያለ እንባ፣ ያለ ቂም ፣ ያለ መከፋፈል እና ብጥብጥ ለዘላለም ደስታ ይሆናል ብሎ ማሰቡ የበለጠ ውብ የሆነ ነገር ነው።
ነገር ግን ወደ ገነት እንዴት መድረስ እንችላለን? መንገዱ የቱ ነው? የኢየሱስ ወሳኝ ሐረግ እነሆ! ዛሬ እሱ “እኔ መንገድ ነኝ” (ዩሐንስ 14፡6) ይለናል። ወደ መንግስተ ሰማይ ለመሄድ የሚያስችለን መንገድ ኢየሱስ ነው - ከእርሱ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ሲኖረን፣ በፍቅር እርሱን ስንመስል እና አካሄዱን ስንከተል በእርሱ መንገድ ላይ እንጓዛለን ማለት ነው። እኔ ክርስቲያን ነኝ፣ አንተም ክርስቲያን ነህ፣ እያንዳንዳችን ክርስቲያን ነን፣ “የትኛውን መንገድ ነው የምከተለው?” ብለን ራሳችንን እንጠይቅ። ወደ መንግስተ ሰማይ የማይመሩ መንገዶች አሉ፣ የዓለማዊ መንገዶች፣ ራሳችንን ሙሉ እንደ ሆንን አድርገን የምንቆጥርበት መንገዶች፣ የራስ ወዳድነት መንገዶች። እናም የኢየሱስ መንገድ ፣ በትህትና የተሞላ ፍቅር፣ የጸሎት ፣ የትህትና ፣ የታማኝነት ፣ ለሌሎች አገልግሎት መስጠትን የሚያመለክት መንገድ ነው። ከእኔ ከራሴ ጋር ብቻ የሚደረግ ጉዞ አይደለም፣ ኢየሱስ እያገዘኝ የምኖረው የሕይወት ጉዞ ነው። በየቀኑ “ኢየሱስ ሆይ ፣ ስለ ምርጫዬ ምን ታስባለህ? በእነዚህ ሁኔታ ከእነዚህ ሰዎች ጋር ስላለኝ ሁኔታ ምን ትላለህ? ብለን በእየቀኑ ልንጠይቀው ይገባል። ወደ መንግስተ ሰማያት የሚወስደውን መንገድ የሆነውን ኢየሱስ እንዲህ ብለን መጠየቅ መልካም ነው። የሰማይ ንግሥት የሆነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለእኛ መንግሥተ ሰማይ የከፈተልንን ኢየሱስን መከተል እንችል ዘንድ እንድትረዳን አማላጅነቷን ልንማጸን ይገባል።
ምንጭ፡ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በግንቦት 02/2012 ዓ.ም በቫቲካን ካደረጉት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የተወሰደ።
የቫቲካን ዜና