ሐዋርያው ማቲያስ ስለራሱ ሳይሆን ስለክርስቶስ ምስክርነትን ሰጠ!
የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ ዛሬ ግንቦት 06/2012 ዓ.ም በዩሁዳ ቦታ የተመረጠው እና ከሙታን የተነሳውን ኢየሱስ ክርስቶስን በድፍረት የመሰከረው የሐዋርያው ቅዱስ ማቲያስ አመታዊ በዓል እየተከበረ ይገኛል።
ማትያስ በይሁዳ ምትክ ተመረጠ
በእነዚያም ቀናት፣ ጴጥሮስ መቶ ሃያ በሚሆኑ ወንድሞች መካከል ቆሞ፣ እንዲህ አለ፤ “ወንድሞች ሆይ፤ ኢየሱስን ለያዙት ሰዎች መሪ ስለ ሆናቸው ስለ ይሁዳ፣ መንፈስ ቅዱስ አስቀድሞ በዳዊት አፍ የተናገረው የመጽሐፉ ቃል መፈጸም ስላለበት፣ እርሱ ከእኛ እንደ አንዱ ተቈጥሮ በዚህ አገልግሎት የመሳተፍ ዕድል አግኝቶ ነበር።” ጴጥሮስም በመቀጠል እንዲህ አለ፤ “በመዝሙር መጽሐፍ፣ ‘መኖሪያው ባዶ ትሁን፤ የሚኖርባትም ሰው አይገኝ’ ደግሞም፣ ‘ሹመቱን ሌላ ሰው ይውሰደው’ ተብሎ ተጽፎአል። ስለዚህ ጌታ ኢየሱስ በመካከላችን በገባበትና በወጣበት ጊዜ ሁሉ፣ ከእኛ ጋር ከነበሩት መካከል አንድ ሰው መምረጥ ያስፈልጋል፤ ይኸውም፣ ከዮሐንስ ጥምቀት ጀምሮ ኢየሱስ ከእኛ ተለይቶ እስካረገበት ቀን ድረስ የነበረ መሆን አለበት፤ ምክንያቱም ከእነዚህ ሰዎች አንዱ ከእኛ ጋር የትንሣኤው ምስክር እንዲሆን ያስፈልጋል።” ስለዚህ ኢዮስጦስ የሚሉትን፣ በርስያን የተባለውን ዮሴፍንና ማቲያስን ሁለቱን አቀረቡ፤ እንዲህም ብለው ጸለዩ፤ “ጌታ ሆይ፤ አንተ የሰውን ሁሉ ልብ ታውቃለህ፤ ከእነዚህ ከሁለቱ መካከል የመረጥኸውን ሰው አመልክተንና ይሁዳ ወደ ገዛ ራሱ ስፍራ ትቶት በሄደው በዚህ አገልግሎትና በሐዋርያዊነት ቦታ ላይ ሹመው።” ከዚያም ዕጣ ጣሉላቸው፤ ዕጣውም ለማትያስ ወጣ፤ እርሱም ከዐሥራ አንዱ ሐዋርያት ጋር ተቈጠረ (ሐዋ 1፡15-17. 20-26)።
የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ !
በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ በተጠቀሰው የቅዱስ ወንጌል ቀጣይ ክፍል ላይ ያለውን "ጉዞ" የሚያመልክት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ማድረጋችንን ዛሬ እንቀጥላለን። ሁሉም ነገር የሚጀምረው ከኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ ነው። ይህ በእርግጥ በሌሎች ክስተቶች መካከል የተከሰተ አንድ ክስተት ሳይሆን ነገር ግን የአዲስ ህይወት ምንጭ ነው። ደቀ-መዛሙርቱ ይህን አውቀው -ለኢየሱስ ትዕዛዝ ታዛዦች ሆነው - ሁሉም በአንድ ላይ ሆነው በመግባባት መንፈስ በአንድነት እና በጽናት ይጸልዩ ነበር። እናት የሆነችውን ማርያምን አጥብቀው ይዘዋል፣ የእግዚአብሔርን ኃይል አጋጣሚ በሆነ መንገድ ሳይሆን ነገር ግን በመካከላቸው ያለውን ኅብረት በማጠናከር በመጠባበቅ ላይ ነበሩ።
ይህ የመጀመሪያ ማኅበረሰብ በ 120 ወንድሞች እና እህቶች የተገነባ ሲሆን በውስጡ 12 የእስራኤልን ነገዶች የሚወክሉ ምልክቶች የሚታዩበት እና የቤተክርስቲያን አርማ የሆኑ ኢየሱስ የመረጣቸው አስራ ሁለት ሐዋርያቶች በውስጥ አቅፎ የያዘ ነው። ነገር ግን አሁን አስከፊ ከሆነው መከራ እና ሞት በኋላ የጌታ ሐዋርያት ቁጥራቸው አስራሁለት ሳይሆን 11 ሆኗል። ከእነርሱ መካከል አንዱ የነበረው ይሁዳ በፈጸመው ተግባር ተጸጽቶ ራሱን በማጥፋቱ የተነሳ ከእነርሱ ጋር የለም።
እርሱ ከጌታ እና ከሌሎቹ ጋር የነበረውን ኅብረት በመተው ራሱን ማገልገል የጀመረ ሲሆን ብቸኛ በመሆን ብቻውን ለመሥራት ይፈልግ ነበር፣ ራሱን ከሌሎች ገለልተኛ በማድረግ፣ ራሱን በነጻ የመስጠት ጸጋ ችላ በማለት፣ የትዕቢት ቫይረስ በጭንቅላቱ እና በልቡ ውስጥ እንዲገባ በመፍቀድ ድሆችን በመጠቀም ድሆችን ለመበዝበዝ በመፈለግ፣ ከ“ጓደኛነት” ወደ ጠላትነት በመቀየርና “ኢየሱስን ለመያዝ የሚሄዱትን ሰዎች በመምራት” ሥራ ላይ ተጠምዶ ነበር። ይሁዳ የኢየሱስ የቅርብ ወዳጆች ቡድን አባል በመሆን እና በአገልግሎቱ ውስጥ በመሳተፍ ታላቅ ጸጋን ተቀብሏል፣ ነገር ግን በአንድ ወቅት የራሱን ሕይወት በራሱ ኃይል ያዳነ መስሎት ሕይወቱን ያጣል። እርሱ ልቡን ከኢየሱስ ጋር ማደረጉን አቁሟል፣ ከኢየሱስ እና ከሌሎች ጋር የነበረውን ግንኙነት አቁሟል። ደቀ መዝሙር መሆኑን አቁሞ እርሱ ራሱን ከጌታው በላይ አደረገ። ኢየሱስን በመሸጥ ባገኘው ገንዘብ አንድ መሬት ተገዛበት፣ ይህ መሬት ምንም ዓይነት ፍሬ አላፈራም፣ ነገር ግን የገዛ የራሱ ደም ፈሰሰበት።
ይሁዳ ከሕይወት ይልቅ ሞትን መርጦ (ዘዳ 30:19፣ ሲራቅ 15.17 ይመልከቱ) ክፉዎች የሚጓዙበትን የጨለማ መንገድ ተከትሉዋል (ምሳሌ 4.19; መዝ 1, 6)፣ በተቃራኒው ደግሞ ዐስራ አንዱ ሕይወትን እና በረከትን መረጡ፣ ይህ በረከት በታሪክ ውስጥ፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ፣ ከእስራኤል ሕዝብ ወደ ቤተክርስቲያን እንዲፈስ አላፊነቱን ተቀበሉ።
ወንጌላዊው ሉቃስ እንዳስቀመጠው ከአስራ ሁለቱ መኃል የአንዱ ሰው ክህደት ለተቀረው የማሕበሩ አባላት እመም የሆነባቸው በመሆኑ የተነሳ ይህ እርሱ የነበረው የሥራ ድርሻ ወደ ሌላ ሰው እንዲሻገር አደረጉ። ደግሞስ ማን ሊተካው ይችላል? ጴጥሮስ ይህንን ጥያቄ አመልክቷል- አዲስ የሚመረጠው ሰው የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዝሙር የሆነ፣ ከመጀመሪያው ማለትም በዮርዳኖስ ወንዝ ከተጠመቀበት እስከ መጨረሻው ማለትም ወደ ሰማይ እስከ ዐረገበት ቀን ድረስ ከኢየሱስ ጋር የነበረ መሆን እንዳለበት አመላክቷል (የሐዋ. 1፡21-22)። አስራሁለቱን በድጋሚ ሙሉ አድርጎ መገንባት አስፈላጊ ነበር። በዚህ ነጥብ ላይ የማህበረሰብ የነቃ ተሳትፎ ላይ የተመሰረት በማስተዋል ጥበብ የተሞላ ውሳኔ ማደረግ አስፈልጎ ነበር፣ ይህም እውነታውን በእግዚአብሔር ዓይን፣ በማኅበር እና በአንድነት ዓይን ጭምር ማየትን ያካትት ነበር።
ለእዚህ ተግባር የሚውሉ ሁለት ሰዎችን ማለትም ኢዮስጦስ የሚሉትን፣ በርስያን የተባለውን ዮሴፍንና ማቲያስን በእጩነት አቀረቡ። ከእዚያም በኋላ ሁሉም በአንድነት እንዲህም ብለው ጸለዩ፤ “ጌታ ሆይ፤ አንተ የሰውን ሁሉ ልብ ታውቃለህ፤ ከእነዚህ ከሁለቱ መካከል የመረጥኸውን ሰው አመልክተንና ። ይሁዳ ወደ ገዛ ራሱ ስፍራ ትቶት በሄደው በዚህ አገልግሎትና በሐዋርያዊነት ቦታ ላይ ሹመው።” (የሐዋ. 1፡24-25)። እናም ከአስራአንዱ ጋር ይቀላቀል ዘንድ በወቅቱ በተጣለው እጣ አማካይነት ጌታ ማቲያስን መረጠ። በእዚህም ሁኔታ ነበር አስራሁለቱ እንደ ገና አዲስ አካል በመሆን አዲስ ኅበረት የፈጠሩት፣ ይህም ኅብረት የመከፋፈልን፣ ገለልተኛ የመሆንን፣ የግል አስተሳሰባችን ለማርካት ብቻ በማሰብ የግል ቦታ መፈለግን፣ በማስወገድ ሐዋርያት በመጀመርያ ደረጃ ሊሰጡት የሚገባው ምስክርነት ኅብረት መፍጠር መሆኑን አሳይተዋል። "እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ" (ዮሐ. 13 35) በማለት ኢየሱስ ተናግሮ ነበር።
አስራሁለት ሐዋርያት በሐዋርያት ሥራ ውስጥ ጌታ ያሳያቸውን አብነት ሲከተሉ እናያለን። እነርሱም የክርስቶስ የማዳን ሥራ እውቅና ያላቸው ምስክሮች እና እነርሱ ራሳቸው ፍጹም መሆናቸውን ለዓለም ማሳየት ሳይሆን ነገር ግን በአንድነት መንፈስ ባገኙት ጸጋ በሕዝቦቹ መካከል በሚኖረውን አዲስ መንገድ የሚያሳየውን ጌታ ኢየሱስን ለሕዝቦች ሁሉ መሰከሩ። ሐዋርያት በወንድማማችነት መንፈስ ውስጥ በሚገኘው ከሙታን በተነሳው ጌታ ሥር ሆነው ለመኖር መርጠው ራሳቸውን ለመስጠት ያስቻላቸው ዘንድ ብቸኛው የጸጋ ስጦታ የሚገኘው ከእዚያ መሆኑን ተረድተው በእዚህ መንፈስ ይኖሩ ነበር።
እኛም የእግዚአብሄርን የጸጋ ስጦታ ችላ ሳንል እና አድሎአዊ ለሆነ ሥራ ያለንን እምቢተኝነት በመግለጽ ራሳችንን በራሳችን የማሞገስ ባህሪይ በማስወገድ ከሙታን የተነሳውን ጌታ መመስከር የሚያስገኘውን ውበት መልሰን መጎናጸፍ ያስፈልገናል። የክርስቲያን ማኅበረሰቡ ውስጥ በሚገኘው በሐዋርያትን መድበለ ዘር (DNA) ውስጥ በመግባት አንድነታችንና ነጻነታችንን እንዴት መጠበቅ እንደ ሚገባን በመረዳት፣ ብዝሃነትን ሳንፈራ አንድነትን እንድንፈጥር፣ ከቁሳቁሶች ጋር የተቆራኜ ሕይወት እንዳይኖረን በማድረግ እና ሰማዕታት ለመሆን የሚረዳንን ጸጋ በመጠየቅ በታሪክ ውስጥ የምንሰራ ህያው እግዚአብሔር ምስክሮች መሆን ይጠበቅብናል።
ምንጭ፡ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሰኔ 05/2011 ዓ.ም ካደረጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አሰትምህሮ የተወሰደ።
የቫቲካን ዜና