የሰኔ 07/2012 ዓ.ም ዕለተ ሰንበት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ
“ቅድስት ስላሴ ዓለምን የሚያገለግል ፍቅር ነው”
የእለቱ ምንባባት
1. ዘጸዐት 34፡4-6, 8-9
2. 2ኛ ቆሮንጦስ 13፡11-13
3. ዮሐንስ 3፡16-18
የእለቱ ቅዱስ ወንጌል
በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስከ መስጠት ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወዶአልና፤ እግዚአብሔር ልጁን ወደ ዓለም የላከው በዓለም ለመፍረድ ሳይሆን፣ ዓለምን በእርሱ ለማዳን ነው። በእርሱ የሚያምን ሁሉ አይፈረድበትም፤ በእርሱ የማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ፣ አሁኑኑ ተፈርዶበታል።
የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ
የቅድስት ስላሴን በዓል በምናክብርበት በዛሬው ዕለት የተነበበው ቅዱስ ወንጌል (ዮሐ 3፡16-18) ትርጓሜ ሐዋርያው ዮሐንስ በተዋሃደ ቋንቋ - እግዚአብሔር እርሱ ለፈጠረው ፍጥረት ለዓለም ያለው ፍቅር ምስጢር ይገልጻል። ከኒቆዲሞስ ጋር ባደረገው አጭር ውይይት ዓለምን ለመደገፍ የአባቱን የደኅንነት ዕቅድ የሚያከናውነው ኢየሱስ ራሱ እንደ ሆነ ይገልጻል። “እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና” (ዮሐንስ 3፡16) በማለት ማረጋገጫ ይሰጣል። እነዚህ ቃላት የሚያመለክቱት የሦስቱን መለኮታዊ አካላት ተግባር ሲሆን - አብ ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ - ሁሉም ሰብአዊነትን እና ዓለምን የሚያድን አንድ የፍቅር ዕቅድ አላቸው፣ እሱም እኛን የመዳን ዕቅድ ነው።
እግዚአብሔር ዓለምን መልካም እና ውብ አድርጎ ፈጠረ፣ ነገር ግን የሰው ልጅ ኃጢአት ከሠራ በኋላ ዓለም ክፋት እና የሥነ ምግባር ውድቀት ምልክት ሆነች። እኛ ወንዶች እና ሴቶች ኃጢአተኞች ነን ፣ ስለሆነም እግዚአብሔር በዓለም ላይ መፍረድ ፣ ክፉ ተግባራትን ማጥፋት እና ኃጢአተኞችን ለመቅጣት ጣልቃ መግባት ይችላል። በምትኩ ኃጢያቶች ቢኖሩም እንኳን እግዚአብሔር ዓለምን ይወዳል፣ እኛ ስህተት በምንፈጽምበት ጊዜ እና ከእርሱ በምንርቅበት ጊዜያት እንኳን ሳይቀር እግዚአብሔር እያንዳንዳችንን ይወደናል። እግዚአብሔር አብ ዓለምን እጅግ ስለወደድ ዓለምን ለማዳን ውድ የሆነውን ስጦታ ሰጠን፤ አንዲያ ልጁን ለእኛ ሰጠን፣ ለያንዳንዱ የሰው ልጅ ሕይወቱን የሚሰጠ፣ ለዚህ ሲል የሞተ ከሙታን የተነሣ እና ወደ አባቱ ተመልሶ የሄደ፣ ከአባቱ ጋር ሆኖ መንፈስ ቅዱስን ሊልክልን ቃል የገባውን ልጁን ይልክልናል።ስለሆነም ቅድስት ሥላሴ ፍቅር ነው ፣ ዓለምን የሚያድን እና እንደ አዲስ አድርጎ የሚፈጥር ፍቅር። ዛሬ ስለ እግዚአብሔር አብ፣ ስለ ወልድ እና ስለ መንፈስ ቅዱስ ስናስብ ስለ እግዚአብሔር ፍቅር እናስባለን! እንደተወደድን ሆኖ ከተሰማን መልካም ነው። “እግዚአብሔር ይወደኛል” - ይህ ዛሬ ሊሰማን የሚገባን ስሜት ነው።
ኢየሱስ እግዚአብሔር አብ አንድያ ልጁን ለዓለም እንደ ሚሰጥ በሚናገርበት ወቅት ስለ አብርሃም እና ልጁን ይሳቅን ለመሰዋት ያደርገውን ሙከራ የሚገልጸው የዘፍጥረት መጽሐፍ የሚናገረው ቃል በአዕምሮአችን እናስባለን (ዘፍጥረት 22፡1-14)፣ “ጥልቀቱ የማይለካ” ፍቅር እግዚአብሔር ለልጆቹ አለው። እኛም እግዚአብሔር ለሙሴ እንዴት ራሱን እንደገለጠ እናስባለን “ሩኅሩኅ ቸር አምላክ እግዚአብሔር ለቍጣ የዘገየ፣ ፍቅሩና ታማኝነቱ የበዛ” (ዘጸ 34፡6)። የዘፀአት መጽሐፍ እንደሚተርከው ይህ ከእግዚአብሔር ጋር የተደረገው ግንኙነት ሙሴን አበረታቶታል፣ እርሱም “አቤቱ ጌታ ሆይ፤ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ፣ ጌታ ከእኛ ጋር ይሂድ፤ ይህ አንገተ ደንዳና ሕዝብ ቢሆንም እንኳ፣ ክፋታችንንና ኀጢአታችንን ይቅር በል፤ እንደ ርስትህም አድርገህ ውሰደን” (ዘፀሐት 34፡9)። እግዚአብሔር ልጁን በመላክ እንዲሁ አደረገ። እኛ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የልጁ ልጆች ነን! እኛ የእግዚአብሔር ቅርስ ነን!
ውድ ወንድሞች እና እህቶች! የዛሬው በዓል በእግዚአብሔር ውበት እንደገና እንድንደሰት ይጋብዘናል፣ ውበት ፣ ቸርነት እና በቀላሉ የማይገለጽ እውነት። ነገር ግን ውበት ፣ መልካምነት እና ትህትና ያለው እውነት ቅርብ ነው ፣ ወደ ህይወታችን ለመግባት ቃል ሥጋ ይሆናል፣ በታሪካችን፣ በእያንዳንዳችን ታሪክ ውስጥ ለመግባት እያንዳንዱ ወንድ እና ሴት የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው ወደ እኛ ይመጣል። እግዚአብሔር ፍቅር መሆኑን መቀበሉ በራሱ እምነት ነው፣ ይህንን ፍቅር መቀበላችን በራሱ ክርስቶስ የሚሰጠንን መንፈስ ቅዱስ መቀበል ማለት ነው፣ መንፈስ ቅዱስ እንድንነቃነቅ ያደርገናል፣ መንፈስ ቅዱስን እድንገናኝ፣ በእርሱ እንድንተማመን የሚያደርገን የክርስትና ሕይወት መሰረት ነው። መውደድ፣ እግዚአብሔርን መገናኘት ፣ እግዚአብሔርን መፈለግ፤ እርሱ እራሱ አስቀድሞ እኛን ይፈልገናል።
በቅድስት ሥላሴ ውስጥ ማረፊያ ያላት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የእግዚአብሔርን ፍቅር በደስታ በተሞላ ልብ እንድንቀበል ትረዳን ዘንድ በደስታ እንድንሞላ እንዲሁም በዚህ ዓለም ጉዞአችን ውስጥ ትርጉም ያለው ሕይወት እንድንኖር ወደ መንግሥተ ሰማይ በሚያመራው መንገድ ላይ መጓዝ የምንችልበትን ፀጋ ከልጇ እንድታሰጠን አማላጅነቷን ልንማጸን ይገባል።
ምንጭ የቫቲካን ሬዲዮ የአማርኛው አገልግሎት
አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን