ፈልግ

የነሐሴ 03/2011 ዓ.ም ዘክረምት 6ኛ እለተ ሰንበት ቅ. ወንጌል እና የቅ. ወንጌል አስተንትኖ የነሐሴ 03/2011 ዓ.ም ዘክረምት 6ኛ እለተ ሰንበት ቅ. ወንጌል እና የቅ. ወንጌል አስተንትኖ  

የነሐሴ 03/2011 ዓ.ም ዘክረምት 6ኛ እለተ ሰንበት ቅ. ወንጌል እና የቅ. ወንጌል አስተንትኖ

የዕለቱ ምንባባት

1.      1ቆሮ 8፡ 1-13

2.    1ጴጥ 4፡ 1-5

3.    ሐዋ 26፡ 1-23

4.    ማቴ 12፡ 38-50

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ማረጋገጫ ምልክት ስለ መሻት

ከዚያም አንዳንድ የአይሁድ ሃይማኖት መምህራንና ፈሪሳውያን፣ “መምህር ሆይ፤ ከአንተ ታምራዊ ምልክት ማየት እንፈልጋለን” አሉት። እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ይጠይቃል፤ ነገር ግን ከነቢዩ ዮናስ ምልክት በስተቀር ሌላ ምልክት አይሰጠውም። ዮናስ በዓሣ ዐንበሪ ሆድ ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ቈየ፣ እንዲሁ የሰው ልጅ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት በምድር ሆድ ውስጥ ይቈያል። የነነዌ ሰዎች በፍርድ ዕለት ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው  ፈርዱበታል፤ እነርሱ በዮናስ ስብከት ንስሓ ገብተዋልና። እነሆ፤ ከዮናስ የሚበልጥ እዚህ አለ።

በፍርድ ዕለት የደቡብ ንግሥት ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥታ ትፈርድበታለች፤ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳርቻ መጥታለችና። እነሆ፤ ከሰሎሞን የሚበልጥ እዚህ አለ። “ርኩስ መንፈስ ከሰው ከወጣ በኋላ ዕረፍት ለማግኘት ውሃ በሌለበት ደረቅ ቦታ ይንከራተታል፤ የሚሻውን ዕረፍት ግን አያገኝም። ከዚያም፣ ‘ወደ ነበርሁበት ቤት ተመልሼ ልሂድ’ ይላል፤ ሲመለስም ቤቱ ባዶ ሆኖ፣ ጸድቶና ተዘጋጅቶ ያገኘዋል። ከዚያም ይሄድና ከራሱ የባሱ ሌሎች ሰባት ክፉ መናፍስት ይዞ ይመጣል፤ እነርሱም ሰውየው ውስጥ ገብተው ይኖራሉ። የዚያም ሰው የኋለኛው ሁኔታ ከፊተኛው የከፋ ይሆናል። በዚህ ክፉ ትውልድም ላይ እንዲሁ ይሆንበታል።”

የኢየሱስ እናትና ወንድሞች

ኢየሱስ ለሕዝቡ ሲናገር ሳለ፣ እናቱና ወንድሞቹ ሊያነጋግሩት ፈልገው በውጭ ቆመው ነበር። አንድ ሰውም፣ “እነሆ፣ እናትህና ወንድሞችህ ሊያነጋግሩህ ፈልገው በውጭ ቆመዋል” አለው። ኢየሱስም፣ “እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነማን ናቸው?” ሲል መለሰለት። በእጁም ወደ ደቀ መዛሙርቱ እያመለከተ እንዲህ አለ፤ “እናቴና ወንድሞቼ እነዚህ ናቸው፤በሰማይ ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፣ ወንድሜ፣ እኅቴና እናቴም ነው።

የእለት ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የተከበራችሁ የእግዚአብሔር ቅዱሳን ቤተሰቦች እግዚአብሔር ታላቅ ነው በእድሜአችን ላይ ዛሬን እንድናይ ፈቅዶአልና ስሙ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም የተመሰገነ ይሁን፡፡ እንደ ሁልጊዜው በቃሉ አማካኝነት ሲጎበኘን ዛሬ በተነበቡልን ምንባባቶችም አባታዊ ምክሩንና አምላካዊ ተግባሩንም ያስታውሰናል፡፡ አሁን የምንገኝበት ወቅት የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወደ ሰማይ መውጣትዋን ለማስታወስ የአስራ ስድስት ቀን ጾምና ሱባዔ በማድረግ ለመንፈሳዊ ሕይወታችን ቦታ በመስጠት እያንዳንዳችን ራሳችንን የምንመረምርበት ጊዜ ነው፡፡

ብዙ ስጋዊ ነገሮችን እየወደድናቸው ለጌታ ክብር ብለን እንዳልወደድናቸው በመተው በሁለንተናዊ የሕይወት ጉዞአችን ለሌሎች ምሳሌ በመሆን እንድንጓዝ በአንደኛው ቆሮንቶስ 8፥1-13 ባለው ክፍል ያስተምረናል። በዚህ መንፈስ ተጉዘን እንደሆን ለእኛስ ነገር ሁሉ ከእርሱ የሆነ ለእርሱ የሆንን አንድ አምላክ አብ አለን ነገር ሁሉም በእርሱ በኩል የሆነ እኛም በእርሱ በኩል የሆንን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን በማለት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ቁ፣ 8 ላይ ያረጋግጥልናል፡፡

ስለዚህ ይህንን ጌታ ለማገልገል ዝግጁ  እንድንሆንና ሁለንተናዊ ማንነታችን በእርሱ በጌታችን በአምላካችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ጥለን ራሳችንን ዝቅ አድርገን እርሱ ወደ ሚመራን እርሱ ወደ ሚጠቁመንና ያዋጣችኃል ወዳለን ወደ እርሱ እንድንገሰግስ ተጋብዘናል፡፡ ምክንያቱም ይህ ጌታ ነው ስለ እኛ በስጋው መከራንና ስቃይን ተቀብሎ ነጻ ያወጣን ሰለሆነም ከእንግዲህ ወዲህ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንጂ እንደ ሰው ምኞት እንዳንኖር ተጠርተናል ይህንንም በ1ጴጥ 4፥1-2 ላይ ተብራርቶልናል፡፡ በእርግጥ ይህ ጉዞ ቀላል አይደለም ብዙ ድካምና መከራ አለው፡፡

የተወደዳችሁ የክርስቶስ ቤተሰቦች! ብዙ ቅዱሳን አባቶች ጌታን መከተል የቻሉትና እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ ድረስ እሱን መስለው ሕይወታቸውን ያሳለፉት በክርስቲያናዊ ጉዞአቸው መንገዱ ሁልጊዜ አለጋ በአልጋ እየሆነላቸው አልነበረም፡፡ በብዙ ድካምና መከራ ወደ እግዚአብሔር መንግስት እንገባ ዘንድ ይገባናል (ሐዋ 14፥22) ብለው ሐዋርያት እንዳስተማሩን ያለ ኃጢአታቸው እየተከሰሱ እየተደበደቡ አንዳንዴም ለተራበ አንበሳ እየተሰጡ መከራን በትዕግሥት እየተቀበሉ ነበር፡፡ ክርስቶስን መምሰል እና መስቀሉን መሽከም ማለት ያለ ኃጢአት ለወንጌል ለቤተ ክርስቲያን ህልውና ለእግዚአብሔር ክቡር ስም ሲሉ ከዓለምና ከዓለማውያን የሚመጣ መከራን ሳይሳቀቁ መቀበል ነው፣ ይህም እግዚአብሔር ስለ እኛ ያደረገው መልካም ነገር መሆኑን ማመን ይኖርብናል፥

 መልካምን ነገር እንደ ጥፋት መቁጠር ከክርስቶስ እቅፍ ውስጥ እንደ መውጣት ይቆጠራል ምክንያቱም መልካምን ነገር ሁሉ የሚጠላ የክፋት አባት ዲያብሎስ ስለሆነ ነው፡፡ እግዚአብሔርን በሙሉ ልብ ለመከተል ምንም ዓይነት ምልክት አያሻንም፣ ለምን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከምልክቶች በላይ የሆነውን ምልክት ሞቶ በመነሳት አሳይቶናል። ነገር ግን ፈሪሳውያን ምልክት አሳየን ብለው በጠየቁት ጊዜ እነርሱን ወደ ንስሃ ለመመለስ የዮናስን ታሪክ ነበር የተረከላቸው፡፡

የተከበራችሁ የክርስቶስ ቤተሰቦች እኛ የሚያስፈልገን እንደ ፈሪሳውያን ተአምር ሳይሆን በእግዚአብሔር ላይ መታመን ነው፡፡ ይህ ከሌለን ከእግዚአብሔር ለመራቅ ቅርብ ነን በእኛ ላይ የእምቢተኝነት መንፈስ ይነግሳል፡፡ እምቢተኝነት ደግሞ ከእግዚአብሔር ያርቀናል ከእግዚአብሔር መራቅ ደግሞ የእግዚአብሔርን ጸጋና በረከት የእርሱን ቸርነትና ምህረት በማጣት ሕይወታችን አሰቃቂና በመከራ የተሞላ ነው የሚሆነው፡፡ ሕይወታችን የተድላና የደስታ የጸጋና የበረከት የሰላምና የምህረት ሕይወት ሊሆን የሚችለው በእግዚአብሔር ላይ እምነት ሲኖረንና የእርሱን ፈቃድ ስንፈጽም ብቻ ነው በዚህም የእግዚአብሔር ልጆች አባትና እናት ወንድምና እህት የምንሆንበትን ጸጋ ሰጥቶናል በዛሬውም ወንጌል የተላለፈልን መልዕክት ይህንኑ ነው፡፡

በእግዚአብሔር ላይ እምነት የሌለው ሰው እና የእርሱንም ፈቃድ የማይፈጽም አማኝ በቤቱ ሰላምና ፍቅር ጸጋና በረከት አይኖረውም፥፥ ቤታችን ቤተሰባችን ሀብታችን ንብረታችን ልጆቻችን የሚባረኩት በእግዚአብሔር ላይ እምነት ሲኖረንና የእርሱንም ፈቃድ ስንፈጽም ብቻ ነው፥

በተጨማሪም ልክ ሐዋርያው ጳውሎስ በሐዋርያት ሥራ (26፡ 6) ላይ አሁንም ከእግዚአብሔር ዘንድ ለአባቶቻችን ስለ ተሰጠው ስለ ተስፋ ቃል በጽናት መመስከር የምንችልበትን ጸጋ የምናገኘውም በዚሁ የእምነት ጽናት ነው፥፥ ስለዚህ ሁላችንም ለዚህ ተጠርተናል በዚህ መንፈስ ተጉዘን የአባታችን የልዑል እግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ለመመስከር ተነስና በእግርህ ቁም ስለዚህ እኔን ባየህበት ነገር ለአንተም በምታይበት ነገር አገልጋይና ምስክር ትሆን ዘንድ ልሾምህ ታይቼልሃለሁና ብሎ ጳውሎስን እንዳነሳሳው እኛንም በዚሁ መንገድ  ግብዣውን ያቀርብልናል፥፥

ለዚሁ ማረጋገጫ ይሆነን ዘንድ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርግላችኃለሁ ያለው ለደቀ መዛሙርቱ ብቻ ሳይሆን በእምነት ለሚለምኑት ሁሉ የተሰጠ ተስፋ ነው፡፡ ይሁንና ከፈጣሪያችን የምንለምነውን ሁሉ ለማግኘት በእኛ በሰዎች ዘንድ የሚፈለግ አንድ ቅድመ ሁኔታ አለ ይህም በእግዚአብሔር ላይ ሙሉ እምነት ሊኖረን ያስፈልጋል፥፥ ጌታም አምነን የምንለምነውን ሁሉ ይፈጽምልናል፡፡ በዚህ መንፈስ ኖረን ለመንግስቱ እንድንበቃ በጸጋው ይርዳን። አሜን!

ምንጭ፡ ሬዲዮ ቫቲካን የአማርኛ የስርጭት ክፍል

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

08 August 2020, 17:59