የእንግሊዝ እና ዌልስ ጳጳሳት፣ መንግሥታቸው የትግራይን ፍትህ እና ሰላም ጥረት እንዲያግዝ ጠየቁ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በኢትዮጵያ የፌዴራላዊ መንግሥት መከላከያ ኃይል እና በትግራይ ክልላዊ መንግሥት ሠራዊት መካከል፣ ባለፈው ኅዳር ወር የተከሰተው ግጭት በክልሉ ነዋሪዎች ላይ ሰብዓዊ ቀውስን ማስከተሉ ታውቋል። በክልሉ ሰብዓዊ ዕርዳታን በማቅረብ ላይ የሚገኙት መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዳስታወቁት፣ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ነሪዎች መፈናቀላቸውን ገልጸው፣ በርካቶች ደግሞ በረሃብ ሊጠቁ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል። የእንግሊዝ እና ዌልስ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት፣ በትግራይ ክልል ነዋሪዎች ላይ የደረሰው ሰብዓዊ ቀውስ ምላሽ እንዲያገኝ በማለት ድምጻቸውን አሰምተዋል።
ዓመፅ እና ረሃብ
የአፍሪካ ጉዳዮች ተጠሪ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ስዋርብሪክ በትግራይ ክልል ነዋሪዎች ላይ ለደረሰው ሰብዓዊ ቀውስ የእንግሊዝ መንግሥት የዕርዳታ እጁን እንዲዘረጋ፣ በክልሉ ሰላምን ለማስፈን በሚደርግ ጥረት እንዲተባበር ጠይቀዋል። ብጹዕ አቡነ ፖል ጥር 25/2013 ዓ. ም. ለእንግሊዝ መንግሥት የአፍሪካ ጉዳዮች ተጠሪ ጽሕፈት ቤት በጻፉት መልዕክታቸው፣ ከኢትዮጵያ ቤተክርቲያን ጋር ያላቸውን ወዳጅነት ገልጸው፣ በትግራይ ክልል የሚታየው ሰብዓዊ ቀውስ ተወግዶ ሰላም እንዲሰፍን ተመኝተዋል። ከተለያዩ ሪፖርቶች እንደተረዱት በክልሉ የተስፋፋው ወሲባዊ ጥቃት እንዳሳሰባቸው የገለጹት ብጹዕ አቡነ ፖል፣ ለሴቶች እና ለልጃገረዶች አስቸኳይ ጥበቃን ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።
በክልሉ ከፍተኛ የምግብ፣ የውሃ፣ የመድኃኒት እና የሌሎች አስፈላጊ ፍጆታዎች እጥረት በመኖሩ የተነሳ በየቀኑ ሰዎች እንደሚሞቱ ብጹዓን ጳጳሳት ከተለያዩ ሪፖርቶች መረዳታቸውን አስታውቀዋል። ብጹዕ አቡነ ፖል በመልዕክታቸው ሰብዓዊ ቀውሶችን ለመቀነስ የተዘጋጁ የዕርዳታ ሰጭ ድርጅቶች፣ በግጭቱ ምክንያት ከመኖሪያ አካባቢያቸው ለተፈናቀሉት ሰዎች የዕርዳታ አገልጎሎታቸውን እንዳያቀርቡ እንቅፋቶች መኖራቸውን ገልጸዋል።
አስቸኳይ የዕርዳታ ጥሪ ስለመኖሩ
በእንግሊዝ እና ዌልስ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ውስጥ የአፍሪካ ጉዳዮች ተጠሪ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ፖል፣ ለእንግሊዝ መንግሥት ባቀረቡት የአስቸኳይ የዕርዳታ አቅርቦት ጥሪ፣ መንግሥታቸው ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ በእጥፍ እንዲያሳድግ፣ ለሰላም ያለውን ተነሳሽነት በማሳደግ በግጭቱ ለተጎዱት የክልሉ ነዋሪዎች አስቸኳይ እርዳታ እንዲያደርግ ተማጽነዋል።
ብጹዕ አቡነ ፖል ለእንግሊዝ መንግሥት የአፍሪካ ጉዳዮች ተጠሪ ጽሕፈት ቤት በጻፉት መልዕክታቸው፣ በግጭቱ ዙሪያ ያለውን የሁሉን ወገን አስፈላጊነት በማጤን፣ ዓለም አቀፍ ህጎችን በማክበር፣ ከጎረቤት ሀገሮች ጋርም ያለውን ግንኙነት በማየት፣ የተፈናቃዮችን ድህንነት የሚያስጠብቅ አስተማማኝ የመጠለያ አገልግሎት እንደሚዘጋጅ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።