ፈልግ

የምያንማር ወታደራዊ ኃይል የምያንማር ወታደራዊ ኃይል 

ካርዲናል ቦ፣ ወደ ፊት የሚያራምድ ብቸኛው መንገድ ሰላምና የጋራ ውይይት መሆኑን አስገነዘቡ

በምያንማር ውስጥ በወታደራዊ ኃይሉ የተካሄደውን መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ ሊመጣ የሚችለውን አመጽ በማስወገድ ወደ ፊት መጓዝ የሚቻለው በአገሪቱ ውስጥ ሰላም ሰፍኖ የጋራ ውይይችን በማካሄድ መሆኑን የያንጎን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ቻርል ቦ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ወታደራዊ ኃይሉ፣ አገርን የማስተዳደር ስልጣን በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተረከበውን መንግሥት በኃይል በመገልበጥ የቀድሞዋ የኖቤል ሎውሬት አን ሳን ሱ ቺን ጨምሮ በርካታ የመንግሥት መሪዎችን ማሰሩ የተነገረ ሲሆን፣ ይህን ተከትሎ የያንጎን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ቻርል ቦ፣ በሁለቱ ወገኖች መካከል የጋራ ውይይትን በማድረግ ሰላምን ማምጣት ቀዳሚ መንገድ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

አገሪቱ የምትገኝበት የጨለማ አዘቅት

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ቻርል ቦ፣ ጥር 26/2021 ዓ. ም. ለወታደራዊ ኃይል፣ ለሕዝባዊ ተቋማት እና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በላኩት መልዕክታቸው፣ አገራቸው በታሪኳ እጅግ ከባድ የሆኑ ወቅቶችን በማለፍ ላይ መሆኗን አስታውቀው፣  ዘላቂ መፍትሄዎችን በማግኘት አገሪቱ ከገባችበት የጨለማ አዘቅት ውስጥ እንድትወጣ ጸሎት በማድረግ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል። ለምያንማር ሕዝብም ባስተላለፉት መልዕክት፣ በአገሪቱ ውስጥ ከዚህ በፊት ብዙ ደም መፍሰሱን አስታውሰው፣ ይህ እንዳይደገም ሕዝቡ ራሱን ለአመጽ ሳይዳርግ ተረጋግቶ እንዲቆይ አሳስበዋል።

የውይይት እና የእርስ በእርስ ግንኙነት እጥረት

ካርዲናሉ ቀጥለውም በአገሪቱ የተፈጸሙት አሳዛኝ ክስተቶች ምንጫቸው ከውይይት እና እርስ በእርስ ግንኙነቶች ማጣት የመጡ ናቸው ካሉ በኋላ ሰብዓዊ ክብርን ለማስጠበቅ እና እውነትን ለመግኘት ጥረት በሚደረግበት በዚህ ወቅት ጥላቻን ማስወገድ ያስፈልጋል በማለት አሳስበዋል። ለዚህም መላው የማኅበረሰብ እና የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች የጋራ ጸሎትን በማቅረብ፣ ለተፈጠረው የፖለቲካ አለመረጋጋት ሰላማዊ መፍትሄን ማግኘት እንደሚያስፈልግ አደራ ብለዋል።  

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና የተቃውሞ ሰልፎች

በምያንማር የያንጎን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ቻርል ቦ፣ አገራቸው በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት እንደምትሰቃይ አስታውሰው፣ በተፈጠረው የፖለቲካ ቀውስ ምክንያት የጤና ባለሞያዎች አገልግሎታቸውን እንዳያቋርጡ አሳስበዋል።

አመጽ የሌለበትን ሰላማዊ መንገድ መከተል ያስፈልጋል

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ቻርል ቦ፣ ለምያንማር ወታደራዊ ኃይል በላኩት መልዕክት፣ ወታደሩ ሥርዓትን በማስከበሩ ሂደት ለሕዝቡ አስፈላጊውን እንክብካቤን እንዲያደርግ፣ ሰብዓዊ ክብሩን እና ሰላሙን በመጠበቅ ምንም ዓይነት የጭካኔ ተግባር እንዳይፈጸም አሳስበዋል። አክለውም በዴሞክራሲያዊ መንገድ ተመርጠው ወደ ወሂኒ የተጣሉት የሕዝብ ተወካዮች ሰብዓዊ መብት እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል። “የሕዝብ ተወካዮች የጦር ምርኮኞች አይደሉም” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ቻርል ቦ፣ የዴሞክራሲያዊ ሂደት እስረኞች በመሆናቸው በተገባዉ የዴሞክራሲ ቃል ኪዳን መሠረት ከእስር ሊፈቱ ይገባል ብለዋል።  

የታሰሩ መሪዎችን በተመለከተ

ካርዲናል ቦ ታስረው ለሚገኙት ለአን ሳን ሱ ቺ እና ለፓርቲያቸው በላኩት መልዕክት፣ ባጋጠማቸው ችግር የተሰማቸውን ቅሬታ ገልጸው መንፈሳቸውን ከፍ በማድረግ በህዝቡ መካከል እንደገና ጎልተው እንዲታዩ  አሳስበው በጸሎት ማስታወሳቸውንም ገልጸውላቸዋል።

እርቅን ማድረግ እንጂ ማዕቀብን መጣል አያስፈልግም

ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ቦ ትኩረታቸውን ወደ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማዞር፣ በአሳሳቢ ወቅት ርህራሄን በማሳየት አጋርነታቸውን በመግለጻቸው አመስግነው፣ በምያንማር ላይ ማዕቀብ መጣል አገሪቱ ወደ ፊት እንዳትጓዝ፣ ኢኮኖሚዋን በማፍረስ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩትን ወደ ድህነት እንደሚጥል አስረድተው፣ “በምያንማር እርቅ እንጂ ማዕቀብ መጣል አያስፈልግም” ብለዋል። ካርዲናል ቦ በማጠቃለያ መልዕክታቸው አለመግባባቶችን በውይይት መፍታት እንደሚገባ፣ ይህን ካደረጉ ሰላምን ማምጣት እንደሚቻል፣ ሰላም እና ዴሞክራሲ ወደ ብርሃን የሚያደርሱ ብቸኛ መንገዶች መሆናቸውን አስረድተዋል።

08 February 2021, 14:18