ስሎቬኒያ፥ አባ ኦፔካን ለኖቤል የሰላም ሽልማት በዕጩነት አቀረበች
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እ.አ.አ መስከረም 8/2019 ዓ. ም. ወደ ሦስቱ የአፍሪካ አገሮች፥ ሞዛምቢክ፣ ሞሪሼስ እና ማዳጋስካር ሐዋርያዊ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ዕቅዶች ተከትለው በማዳጋስካር ዋና ከተማ አንታናናሪቦ ውስጥ የድሕነት ሕይወት ለሚኖሩት ሰዎች ዕድገትን እና ሰብዓዊ አንድነትን ለማምጣት ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኙትን ክቡር አባ ፔድሮ ኦፔካን ወደ ማዕከላቸው ሄደው መጎብኘታቸው ይታወሳል። ሚሲዮናዊው ክቡር አባ ፔድሮ ኦፔካ ከረዳቶቻቸው ጋር በመሆን በማዳጋስካር ዋና ከተማ አንታናናሪቦ ውስጥ የሚያቀርቡት ሰብዓዊ አገልግሎት ድህነትን፣ ልዩነትን እና ኢ-ፍትሃዊነትን ከዓለም ዙሪያ በማስወገድ፣ ድሆች ሰብዓዊ ክብራቸው ተጠብቆላቸው እንዲኖሩ ያደርጋቸዋል በማለት የስሎቬኒያ ሪፓብሊክ መንግሥት ያወጣው ዘገባ አመልክቷል። የስሎቬኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ያንሻ በተጨማሪም የቀድሞ የማዳጋስካር ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ሄንሪ ክቡር አባ ኦፔካን በማስታወስ ባሰሙት ንግግር “አባ ኦፔካ፣ ከድህነት ጋር በሚደረግ ውጊያ መካከል ተስፋ እና እምነት ያለው ህያው መብራት ናቸው” ማለታቸውን አስታውሰዋል። የላዛሪስት ሚሲዮናዊ ማኅበር አባል የሆኑት ክቡር አባ ኦፔካ፣ ድህነትን በመዋጋት በችግር ውስጥ ለሚገኘው የአንታናናሪቦ ከተማ ድሃ ማኅበረሰብ አዲስ ዕድሎችን በማመቻቸት ሰብዓዊ ክብራቸውን ለማስጠበቅ በርትተው የሰሩ እና በመስራት ላይ ያሉ መሆናቸው ታውቋል። ክቡር አባ ኦፔካ አሁን በሚኖሩበት አንታናናሪቦ ከተማ ለሃምሳ ዓመታት ያህል ድሆችን በመርዳት፣ መጠለያ ለሌላቸው መጠለያን በማዘጋጀት፣ የትምህርት እና የሥራ ዕድሎችን በማመቻቸት፣ በገንዘብ አቅም ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረጋቸው ታውቋል።
በማዳጋስካር ዋና ከተማ አንታናናሪቦ ውስጥ የሚገኝ የአካማሳ ማኅበረ ሰብ የተቋቋመበትን 30ኛ ዓመት እ.አ.አ በ 2019 ዓ. ም. ያከበረ ሲሆን፣ በከተማው ደሃ አካባቢዎች ባደራጃቸው 18 መንደሮች ውስጥ ከ4 ሺህ በላይ መጠለያ አልባ ቤተሰቦችን ተቀብሎ የሚያኖራቸው መሆኑ ታውቋል። በመንደሩ ውስጥ ለሚኖሩ ሕጻናት መዋዕለ ሕጻናትን፣ ለወጣቶች ዩኒቨርሲቲን በመክፈት በማስተማር ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ወደ 13 ሺህ የሚጠጉ ተማዎች በአሁኑ ወቅት በትምህርት ገበታ ላይ መሆናቸው ሲታወቅ ወጣቶችም በተለያዩ የትምህርት ዘርፍ በመሰማራት ሞያቸውን በማሳደግ ላይ መሆናቸው ታውቋል። መንደሮቹ ስድስት ክሊኒኮች፣ ሦስት ሆስፒታሎች እና የማዋለጃ አገልግሎትን የሚሰጡ የጤና ጣቢያዎች እና 18 የስፖርት ማዘወተሪያ ቦታዎች ያሏቸው መሆኑ ታውቋል። ክቡር አባ ኦፔካ ከረዳቶቻቸው ጋር በመሆን በማዳጋስካር እና ዋና ከተማዋ አንታናናሪቦ ውስጥ የሚገኙ፣ በቁጥር ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ድሆችን በመርዳት፣ በየዓመቱ በቁጥር ወደ አምስት ሚሊዮን ለሚጠጉ ሰዎች የዕለት ቀለብ በማቅረብ ላይ መሆናቸው ታውቋል። “የወዳጅነት ከተማ” ተብሎ በሚጠራው የዕርዳታ መስጫ ማዕከል ውስጥ ወደ 500 የሚጠጉ የአገሩ ተወላጆች በሥራ ተሰማርተው እንደሚገኝ፣ በጠቅላላው አራት ሺህ ሰራተኞች በእርሻ፣ በንግድ እና ሌሎች ሥራዎች ተሰማርተው የሚገኙ መሆናቸው ታውቋል። ክቡር አባ ኦፔካ ከተቋማቸው በተጨማሪ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በመንግሥት ስር ለሚገኙ የትምህርት መስጫ ማዕከላት ዕርዳታ በማድረግ ላይ መሆናቸው ታውቋል። ክቡር አባ ኦፔካ ከሁሉም በላይ ወጣቶች ለተፈጥሮ ከፍተኛ እንክብካቤን እና ጥበቃን እንዲያደርጉ ከማስተማር በተጨማሪ የዛፍ ችግኞችን እንዲተክሉ እና ደኖችን እንዲንከባከቡ በማስተማር ላይ መሆናቸው ሲታወቅ፣ በማዳጋስካር በዓመቱ 70 ከመቶ የሚሆን ደን የሚወድም በመሆኑ ክቡር አባ ፔድሮ ከበርካታ ወጣቶች ጋር በመተጋገዝ በየዓመቱ ወደ 50 ሺህ የሚደርሱ ችግኞችን የሚተክሉ መሆኑ ታውቋል። በዓለም ዙሪያ ወዳጆች እና ደጋፊዎች ያሉት የአካማሳ ማኅበር ለአካባቢው ድሃ ማኅበረሰብ በሚያበረክተው ድጋፍ መልካም ምሳሌ መሆኑ ታውቋል።