ፈልግ

በሴቶች ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት ለመግለጽ በኃይል የተሰበረች ጽጌረዳ አበባ  በሴቶች ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት ለመግለጽ በኃይል የተሰበረች ጽጌረዳ አበባ  

በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጾታዊ ጥቃትን የሚያወግዝ እንቅስቃሴ መጀመሩ ተነገረ

የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ፣ እሑድ የካቲት 7/2013 ዓ. ም. “ፍቅር ይፈውሳል እንጂ አያቆስልም” በሚል መሪ ቃል በአውታረ መረብ አማካይነት የሚካሄድ አንድ እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታወቀ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤው እንዳታወቀው ዘንድሮ የተከበረው የቫሌንታይን ቀን በሴቶች ላይ እየደረሰ ያለውን ጾታዊ ጥቃት  ኅብረተሰቡ በተለያዩ መንገዶች እንዲያውቅ የሚደረግበት መሆኑን ገልጿል። ጉባኤው የፍቅረኛሞችን ቀን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፈው መልዕክቱ፣ በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ትንኮሳ ፣ በደል እና ወሲባዊ ጥቃት ሳይፈሩ በመቃወም የዓለምን ምኞት እንደገና ለማረጋገጥ በአውታረ መረብ አማካይነት አዲስ ዘመቻ ለመጀመር መወስኑን አስታውቋል። በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጾታዊ ጥቃት አካላዊ ብቻ ሳይሆን ስሜታዊ እና ስነ-ልቦናዊ መሆኑን ጉባኤው አስረድቶ ይህም በኅብረተሰብ መካከል፣ በቤት ውስጥ፣ በትምህርት ተቋማት፣ በሥራ ቦታዎች እና ሌላው ቀርቶ በአምልኮ ቦታዎችም ጭምር የሚታይ መሆኑን አስረድቷል።

ፍቅር ይፈውሳል እንጂ አያቆስልም!

የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ የጀመረው አዲስ የቅስቀሳ እና ግንዛቤን የማስጨበጥ ጥረት በማኅበራዊ ሚዲያዎች አማካይነት፣ ቀይ የጽጌረዳ አበባ ምስልን በማያዝ “ፍቅር ይፈውሳል እንጂ አያቆስልም” ፣ “ፍቅር ደግ ነው” ፣ “ጾታዊ ጥቃትን በፍቅር ማሸነፍ ያስፈልጋል” ፣ “ክብርን ፣ አድናቆትን እና ፍቅርን ዘወትር ማሳየት ያስፈልጋል” የሚሉ መልዕክቶችን ለማስተላለፍ መነሳቱን አስታውቋል። በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ውስጥ በሚገኝ ዓለማችን ውስጥ የቤት ውስጥ ጥቃት እና አመጽ እየተበራከቱ መምጣቱን የሚገልጹ መረጃዎችን በድረ ገጹ ላይ ማመልከቱን ጉባኤው አስረድቷል።

“ተረስዴይ ኢን ብላክ”

የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ ከአሥር ዓመታት ወዲህ “ተረስዴይ ኢን ብላክ” የተባለ የቅስቀሳ እና ግንዛቤ ማስጨበጫ እንቃስቃሴ እ.አ.አ ከ1988-1998 ዓ. ም. ተዘርግቶ መኖሩን አስታውቆ፣ በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት በማኅበረሰብ ውስጥ ትልቅ ቁስል የፈጠረ መሆኑን ለመግለጽ ዘወትር ሐሙስ ጥቁር ልብስ ሲለበስ መቆየቱን ገልጿል። እንቅስቃሴው በሴቶች ላይ የሚደርስ ጾታዊ ጥቃትን እና ኢ-ፍትሃዊነትን ለመዋጋት ዋነኛ መሣሪያ ሆኖ መቆየቱን የገለጸው የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሴቶች ላይ የሚፈጸም የቤት ውስጥ ጥቃትን ይፋ በማድረግ፣ ጥቃቱ አካባቢን ሳይለይ በመላው ዓለማችን፣ ባደጉት ሆነ በማደግ ላይ ባሉት አገሮች ውስጥ የሚከሰት መሆኑን ገልጾ፣ በተለይ ደግሞ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ተብሎ በሚደረገው የቤት ውስጥ ቆይታ ጊዜ በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃቱ በሚያስደንቅ ሁኔታ ማደጉን አስታውቋል።

የተሳሳቱ አመለካከቶች

“እኛ ሴቶች ከሰዎች ጋር ያለንን ግንኙነት ላለማቋረጥ በርካታ ችግሮችን እና አመጾችን ማለፍ ነበረብን” በማለት የ “ተረስዴይ ኢን ብላክ” እንቅስቃሴ ባልደረባ የሆኑት ወ/ሮ ላሪሳ ግራሲያ ገልጸዋል። እነዚህን የመሳሰሉ የተሳሳቱ አመለካከቶች በስነ-ጽሑፍ እና በማኅበራዊ መገናኛዎች ሲነገሩ መቆየታቸውን አስታውሰው፣ ሆኖም ግን ፍቅር ደግ፣ ሁሉን የሚያቅፍ እና ክቡር መሆኑን አስረድተዋል። አክለውም ዘንድሮ የተከበረው የቫሌንታይን ቀን፣ ፍቅር የሚፈውስ እውነተኛ ስሜት መሆኑን ለዓለም ሕዝብ ማስገንዘብ እንደሚችል ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

የፍቅርን ፅንሰ-ሀሳብ ማዛባት አያስፈልግም

በዜግነት ዛምቢያዊ የሆኑት እና የ “ተረስዴይ ኢን ብላክ” እንቅስቃሴ አባል የሆኑት መጋቢ ዶማን ምካንዳዊረ፣ ሰዎች የፍቅርን ፅንሰ-ሀሳብ ማዛባት እንደሌለባቸው አደራ ብለው፣ ቅዱስ ቫሌንቲኖ እንዳስተማረን ሁሉ ፍቅር ማንንም የማይጎዳ መሆኑን አስረድተዋል። አክለውም ይህን እውነት ማዛባት እንደማያስፈልግ እና የቅዱስ ቫሌንታይን ዕለት መልዕክቶችን እና ምስሎችን ከዓለም አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ ድረ-ገጽ በመውሰድ ከሌሎች ሰዎች ጋር መጋራት እንደሚያስፈልግ አደራ ብለዋል።   

15 February 2021, 15:26