ፈልግ

በሕይወት የመኖር መብት ይከበር በሕይወት የመኖር መብት ይከበር 

የሰሜን አይርላንድ ጳጳሳት የፅንስ ማስወረድ አገልግሎቶችን መቃወማቸው ተገለጸ

የሰሜን አይርላንድ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት፣ መንግሥት ያስተዋወቀውን ፅንስ የማስወረድ አገልግሎቶችን በጽኑ መቃወማቸው ተሰምቷል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የሰሜን አይርላንድ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ሰኞ መጋቢት 13/2013 ዓ. ም. ያወጡት መግለጫ እንዳመለከተው፣ በሰሜን አይርላንድ የመንግሥት ዋና ጽሕፈት ቤት የጤና ሚኒስቴሩን በማስገደድ ፅንስ የማስወረድ አገልግሎቶችን ለማቅረብ የሚያስችል ሊበራል ሥርዓትን ለመዘርጋት መሞከሩ በጽኑ ያሳሰባቸው መሆኑን ተናግረዋል። ብጹዓን ጳጳሳቱ አክለውም፣ ሙከራው “ጉድ ፍራይዴይ” የተባለውን የቤልፋስት ስምምነት መርሆችን ለሚደግፍ ማንኛውም ሰው አሳሳቢ ጉዳይ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

ፅንስን የማስወረድ ህጎች እ. ኤ. አ. በ 2019 ዓ. ም. በዌስት ሚንስተር ፓርላማ አባላት ውስጥ ስልጣንን መጋራት በተደመሰሰበት ወቅት እንዲወገዱ መደረጋቸው የሚታወስ ነው። በሰሜን አየርላንድ ፅንስን በማስወረድ አገልግሎቶች ላይ የተነሳውን ውዝግብ ለማቀዝቀዝ፣ የመንግሥት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ክቡር አቶ ብራንዶን ሌዊስ ሕጋዊ ዕርምጃ እንደሚወስዱ አስታውቀዋል።

በሕይወት የመኖር መብት

የሰሜን አይርላንድ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ደጋግመው እንደተናገሩት፣ እያንዳንዷ እናት እና ያልተወለደ ህፃን እኩል የመኖር መብት ሁል ጊዜ መከበር እና መጠበቅ አለበት ብለዋል። በብዙሃኑ ሕዝብ ግልጽ ፍላጎት ላይ ዌስትሚኒስተር ጫናን ለመፍጠር እንደሚፈልግ የገለጹት ብጹዓን ጳጳሳቱ፣ ለማጽደቅ የሚፈለገው ሕግ ገና ያልተወለዱ ሕፃናትን የመኖር መብት በግልጽ የሚነጥቅ እና የአካል ጉዳተኛ ሕጻናትም ከመወለዳቸው በፊት አድልዎን የሚያደርግ ሕግ መሆኑን ተናግረዋል።

በዝምታ የምንመለከትበት ጊዜ አይደለም

የሰሜን አይርላንድ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ለመንግሥት ምክር ቤት እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ባሰሙት መግለጫ፣ የመንግሥት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊው ለመጫን የሚፈልጉት የውርጃ ደንቦች እጅግ ጥልቅ የሆነ አድልዎ በመሆኑ፣ ድምጽን ከፍ አድርጎ መቃወም የሚያስፈልገው መሆኑን አሳስበው፣ አሁን የሚገኙበት ጊዜ በዝምታ የሚመለከቱት አለመሆኑን ተናግረዋል። ብጹዓን ጳጳሳቱ በማከልም በሕዝብ ለተመረጡት የሕዝብ ተወካዮች እንዳሳሰቡት፣ በማህፀን ውስጥ ያሉ ሕፃናት በእኩል ደረጃ የመታየት እና እንክብካቤን የማግኘት መብታቸው እንዲሁም በእናቶቻቸው በኩል ፍቅርን እና እንክብካቤን የማግኘት መብት በህብረተሰባችን ዘንድ የተጠበቀ እና የተከበረ መሆን አለበት ብለዋል።

24 March 2021, 14:21