የመጋቢት 5/2013 ዓ.ም ዘቅድስት ዕለተ ሰንበት መልዕክቶች እና ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ
የዕለቱ ምንባባት
1. 1ኛ ተሰ.4፡1-12
2. 1ኛ ጴጥ 1፡13-25
3. ሐዋ.ሥ.10፡17-29
4. ማቴ 6፡16-24
የእለቱ ቅዱስ ወንጌል
ስለ ጾም
“ስትጾሙ እንደ ግብዞች አትጠውልጉ፤ እነርሱ መጾማቸው እንዲታወቅላቸው ሆን ብለው በፊታቸው ላይ የሐዘን ምልክት ያሳያሉና፤ እውነት እላችኋለሁ፤ እንዲህ የሚያደርጉ ዋጋቸውን በሙሉ ተቀብለዋል። አንተ ግን በምትጾምበት ጊዜ ፊትህን ታጠብ፤ ራስህንም ተቀባ፤ በዚህም መጾምህ በስውር ያለው አባትህ ብቻ የሚያውቀው፣ ከሰዎች ግን የተሰወረ ይሆናል፤ በስውር የተደረገውን የሚያይ አባትህም ዋጋህን ይከፍልሃል።
ሰማያዊ ሀብት
“ብል ሊበላው፣ ዝገት ሊያበላሸው፣ ሌባም ቈፍሮ ሊሰርቀው በሚችልበት በዚህ ምድር ላይ ለራሳችሁ ሀብት አታከማቹ። ነገር ግን ብል ሊበላው፣ ዝገት ሊያበላሸው፣ ሌባም ቈፍሮ ሊሰርቀው በማይችልበት በዚያ በሰማይ ለራሳችሁ ሀብት አከማቹ፤ ሀብትህ ባለበት ልብህም በዚያው ይሆናልና።
“ዐይን የሰውነት መብራት ነው፤ ስለዚህ ዐይንህ ጤናማ ከሆነ መላው ሰውነትህ በብርሃን የተሞላ ይሆናል። ዐይንህ ታማሚ ከሆነ ግን መላው ሰውነትህ በጨለማ የተሞላ ይሆናል። እንግዲህ በአንተ ውስጥ ያለው ብርሃን ጨለማ ከሆነ፣ ጨለማው እንዴት ድቅድቅ ይሆን? “አንድ ሰው ሁለት ጌቶችን ማገልገል አይችልም፤ አንዱን ጠልቶ ሌላውን ይወዳል፤ ወይም አንዱን አክብሮ ሌላውን ይንቃል። እግዚአብሔርንና ገንዘብን በአንድነት ማገልገል አይቻልም።
የእለቱ አስትንትኖ
በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ! ዛሬ እንደ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓት ዓምልኮ አቆጣጠር ዘቅድስት የሚለውን ሰንበት እናከብራለን።
በዚህ ዕለት በተለይም በዐብይ ጾም ወቅት የእግዚአብሔር ቃል በመልዕክቶቹና ወንጌሉ አማካኝነት ወደ እያንዳንዳችን ይመጣል በቃሉም አማካኝነት እንዴት እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሕይወት መኖር እንደሚገባን ይመክረናል።
ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በዛሬው መልዕክቱ ሲናገር እግዚአብሔር ከእኛ የሚፈልገው አንድ ነገር ብቻ ነው ይኸውም “ለቅድስና ተጠርተናልና ለቅድስና እንድንኖር” በማለት ይናገራል።
“እግዚአብሔር ቅዱስ ነው” ለዚህም ነው መላእክትና ቅዱሳን ዘወትር እርሱን ቅዱስ ቅድስ ቅዱስ እያሉ የሚያመሰግኑትና የሚሰግዱለት።
እኛ በእርሱ አምሳል የተፈጠርን እንደመሆናችን መጠን እግዚአብሔር ለጠራን የቅድስና ጉዞ እርሱ በሰጠን ጸጋ በመታገዝና ልቦናችንን በማዘጋጀት የድርሻችንን በመወጣት የእርሱ ቅድስና ተካፋዬች እንሁን፤ ይህንንም ቅድስና እግዚአብሔር በሕይወታችን ውስጥ እንድንኖረው ይፈልጋል በመሆኑም በቅድስና ለመኖር የሚያስችለንን ጸጋ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት አብዝቶ ይሰጠናል።
ፍጹም ቅድስናና ፍጹም መልካምነት ከእግዚአብሔር ብቻ ይመነጫል እኛም ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት በመፍጠር ይህንን ቅድስናና መልካምነት እንድንካፈል ዘወትር ይጋብዘናል።
ቅድስናችንን የሚያጐድፈው አንድ ነገር ብቻ ነው ይኸውም “ኃጢአት” ነው፤ የቅድስና ሕይወት ማለት እንከን የለሽ ሕይወትን መኖር አልያም ምንም ኃጢአት ሳይሰሩ መኖር ማለት አይደለም። ይልቁንስ በኃጢአት ቀንበር በምንያዝበት ወቅት እና ከቅድስና ሕይወት መስመር በምንስትበት ጊዜ ከኃጢአት ጋር ተጋድሎ የምናደርግበት መሣርያ ነው። ይህንንም ቃል ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን መልዕክቱ አበክሮ ይገልጽልናል። “ስለዚህ የእግዚአብሔርን የጦር መሣርያ በሙሉ አንሱ፣ በዚህ ሁኔታ ክፉ ቀን ሲገጥማችሁ የጠላትን ኃይል መቃወምና እስከመጨረሻም ከተዋጋችሁ በኋላ ጸንታችሁ መቆም ትችላላችሁ።” ኤፌ 6፡13
ሙሉ ለሙሉ የቅድስና ሕይወታችንን ታጥቀን በተጋድሎ እንኖር ዘንድ ክርስቲያናዊ ኃላፊነት አለብን፤ ይህም ትጥቃችን የእግዚአብሔር ቃል እና ምስጢራት ናቸው። በሕይወታችን የእግዚአብሔርን ቃል ከከበረው ዕንቁ በላይ ልንከባከበው የሕይወታችን መሣርያ ልናደርገው ይገባል ምክንያቱም ቃሉ ለሕይወታችን ስንቅ ለመንገዳችን ብርሃን ነውና። በኃጢአት በምንወድቅበት ወቅት እንደገና ኃይል የሚሰጠን ከጸጋው ሙላት እርሱ እግዚአብሔር ብቻ ነው። ስለዚህም ለቅድስና ሕይወታችን ጉዞ ስንቅ ይሆነን ዘንድ በተለይም በዚህ ጾም ወቅት በቃሉና በምስጢራቱ በሙላት በመሳተፍ ከሁሉ አብልጠን በልባችን ልንይዘው፣ ልንለማመደው፣ የእራሳችን ልናደርገው እና ዕለት በዕለት መሣርያችን ልናደርገው ይገባል።
ከእዚህም ጋር በማያያዝ ቅዱስ ሐዋርያው ጴጥሮስ በም. 1፡13-16 እንዲህ ይለናል “ስለዚህ ልባችሁን አዘጋጁ፤ እራሳችሁንም ግዙ፤ ተስፋችሁ እየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ ለእናንተ በሚሰጠው ጸጋ ላይ ሙሉ በሙሉ አድርጉ። ታዛዦችና ደጎች እንደመሆናችሁ መጠን ቀድሞ ባለማወቅ ትኖሩበት የነበረውን ክፉ ምኞት አትከተሉ። ነገር ግን የጠራችሁ እርሱ ቅዱስ እንደሆነ እናንተም በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ፤ ምክንያቱም እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ ተብሎ ተጽፎአልና።”
ቅዱስ የሆኑ ሰዎች ልባቸው ከኃጢአት የጸዳ ንጹህ የሆኑ ሰዎች ናቸው። ልባቸው ንጹህ የሆኑ ሰዎች ብጹአን ናቸው ይህ በመሆኑም እግዚአብሔርን እንደሚያዩትና እግዚአብሔርን እንዲያገኙት በማቴ. 5፡8 ላይ ተገልጾ እናገኛለን። እኛም ይህ ዕድል ተሰጥቶናል በዕድሉም መጠቀሙ ደግሞ የእየንዳንዳችን ክርስቲያናዊ ኃላፊነት ይሆናል።
ቅዱስ ሐዋርያው ጴጥሮስ ይህንኑ የቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስን ቃል ያጠናክረዋል “የጠራችሁ እግዚአብሔር ቅዱስ ስለሆነ እናንተም ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ ይለናል” ግብረ-ገባዊ ትምህርቶች ሁሉ የተመሠረቱት በእግዚአብሔር ባህሪ እና በእግዚአብሔር ቅድስና ላይ ነውና እኛም ይህንን ቅድስና እንድንከተል የዛሬው መልዕክት ያሳስበናል።
እግዚአብሔር ታላቅ በረከትን ሰጥቶናል፣ ልጆቹም አድርጎናል፤ ይሁን እንጂ ከዚሁ በረከት ጋር አብሮ ታላቅ ኃላፊነትንም ሰጥቶናል፤ ልንታዘዝልትም ይገባል። አንድ ልጅ አባቱን ደስ ለማሰኘት እንደሚፈልግ ሁሉ፣ እኛም ለሰማዩ አባታችን በመታዘዝ ደስ ልናሰኘው ይገባል።
የእኛ የክርስቲያኖች እምነት መሠረቱ ዘለዓለማዊ የሆነው የእግዚአብሔር ቃል እንጂ ሌላ ነገር ሊሆን እንደማይገባው ቅዱስ ሐዋርያው ጴጥሮስ ያሳስበናል፡፡ ምክንያቱም ምድርና በውስጡዋ ያሉ ሁሉ እንደሚያልፉ የእርሱ ቃልና በእርሱ አምነው ቃሉን የፈፀሙ ሁሉ ደግሞ ለዘለዓለም እንደምኖሩ ተናግሯል፡፡ በዚሁ በጴጥሮስ መልዕክት ቁ.24-25 ላይ “ምክንያቱም መጸሐፍ እንደሚል ሥጋ ለባሽ ሁሉ እንደ ሣር ነው፤ ክብሩም ሁሉ እንደ ሜዳ አበባ ነው። ሣሩም ይጠወልጋል አበባውም ይረግፋል የጌታ ቃል ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል” ይላልና።
ወንጌላዊ ማቴዎስም ይህንኑ በመደገፍ ሃብታችንን ብልና ዝገት በማያጠፋው በእግዚአብሔር ዘንድ እንድናከማች ይነግረናል።
ለኛ ለክርስቲያኖች ሃብታቸን ምንድን ነው? ሃብታችን የእግዚአብሔር ቃል ነው ከእግዚአብሔር የወሰድነውን መልካምነና ቅድስና ነው።
ይህንን መልካምነት በሕይወታችን ከኖርነው ቃሉንም ከጠበቅን በእርግጥም ሃብታችንን በእግዚአብሔር ዘንድ አከማችተናል ማለት እንችላለን፡፡ ምክንያቱም ሃብትህ ባለበት ቦታ ልብም በዛ ይሆናልና ነው።
እግዚአብሔር በፍጹም ልባችን፣ በፍጹም ነፍሳችን፣ በፍጹም ሃሳባችን፣ በፍጹም ኃይላችን እንጂ በከፊል እንድናገለግለው አልጠራንም።
በአንድ ጊዜ ሰው ለሃብትና ለእግዚአብሔር ቅድሚያ የሚሰጥ ከሆነ የእግዚአብሔርም የገንዘብም ተገዢ ሊሆን አይችልም።አንዱን መምረጥ ይኖርብናል ለዚህም መንፈሳዊና የእምነት ዓይናችንን ከፍተን መልካም የሆነውን ነገር ልንከተል ይገባናል።
ሰው በክርስትና ሕይወት ውስጥ እግዚአብሔርን በጽናት ለመከተል እንዲችል በተጠራበት ሕይወት በመኖር ተጋድሎን ማድረግ ያስፈልገዋል። ተጋድሎአችን ደግሞ በጾምና በጸሎት ሲታገዝ ውጤታማ ይሆናል። ስለዚህ ጾማችንም ይሁን ጸሎታችን እንደ አይሁዳውያኑ ለታይታ ሳይሆን እግዚአብሔርን የሚያስደስት ለእኛም በረከትን የሚያመጣ ሊሆን ይገባዋል። እግዚአብሔር የሚፈልገው ጾም ደግሞ ትንቢተ ኢሳ. 58 ላይ እንደተጠቀሰው ትሕትናና መልካም ሥራ የታከለበት ጾም እንዲሆን ያስፈልጋል ይህንንም ለማድረግ እንድንችል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ታግዘን ጸጋና በረከቱን ከልጇ ታሰጠን።
የሰማነውን ቃል በሕይወት መኖር እንድንችል ጸጋና በረከቱን ያብዛልን !
አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ - ቫቲካን