ፈልግ

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት ስርጭት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት ስርጭት 

በጣሊያን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት ያላገኙ መኖራቸው ተነገረ

በጣሊያን ውስጥ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ አቅመ ደካሞች፣ ስደተኞች፣ ቋሚ የመኖሪያ ፍቃድ እና መጠለያ የሌላቸው ሰዎች የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት ላያገኙ እንደሚችሉ፣ በሮም ሀገረ ስብከት በሚገኝ ካቶሊካዊ ዕርዳታ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት የጤና አገልግሎት መምሪያ ተወካይ የሆኑት ክቡር አቶ ሳልቫቶሬ ጄራቺ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገልጸዋል። በጣልያን ውስጥ ከማኅበረሰቡ የተገለሉ እና በጤናው ዘርፍ መንግሥት ሃላፊነትን ወስዶ የማይከታተላቸው በርካታ ሰዎች መኖራቸውን እኝሁ ተወካይ ገልጸው፣ ሁሉን አቀፍ እና ውጤታማ አስተዳደርዊ መዋቅር ሊዘረጋ ይገባል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በጣሊያን ውስጥ ለስደተኞች የሚቀርብ የሕክምና እና የመድኃኒት አቅርቦት የሚከታተል ማኅበር እንደገለጸው፣ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ እና በማኅበራዊ ችግሮች የተጠቁ ሰዎች መኖራቸውን አስታውቆ፣ እነዚህ ሰዎች ከኅብረተሰቡ በመገለላቸው ምክንያት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት ላያገኙ ይችላሉ በማለት ያደረበትን ስጋት ገልጿል። እንደ ብሔራዊው የክትባት ስርጭት አስተባባሪ ማዕከል እቅድ መሠረት፣ አንድ ሰው ሕጋዊ የመኖሪያ ፍቃድ ባይኖረውም በጣሊያን ውስጥ በየትኛውም አካባቢ የሚኖር ከሆነ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መካላከያ ክትባት መውሰድ እንዳለበት መወሰኑን በሮም ሀገረ ስብከት በሚገኝ ካቶሊካዊ ዕርዳታ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት የጤና አገልግሎት መምሪያ ተወካይ የሆኑት ክቡር አቶ ሳልቫቶሬ ጄራቺ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አስታውቀዋል።  

በሀገረ ስብከቱ የዕርዳታ ማስተባበሪያ ውስጥ የጤና አገልግሎት መምሪያ ተወካይ የሆኑት ክቡር አቶ ሳልቫቶሬ፣ በጣሊያን ውስጥ በተለያዩ ማኅበራዊ እና አስተዳደራዊ ምክንያቶች፣ ከእነዚህም መካከል ሕጋዊ የመኖሪያ ፍቃድ ባለመያዛቸው እና በተጋላጭነታቸው ምክንያት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባትን የማያገኙ በመቶ ሺህዎች የሚገመቱ ሰዎች መኖራቸውን አስታውቀዋል። የመከላከያ ክትባትን ማግኘት ከማይችሉት መካከል ሕጋዊ የመኖሪያ ፍቃድ ባለመያዛቸው ምክንያት የሕክምና ዕርዳታን ማግኘት የማይችሉ በቁጥር በርካታ ስደተኞች መኖራቸውን ገልጸዋል። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባትን ከማያገኙት መካከል መጠለያ አልባ የሆኑ የአገሪቱ ዜጎች እና የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው ሰዎች መኖራቸውን ገልጸው፣ የመከላከያ ክትባት ስርጭት መርሃ ግብሩ ሁሉን ያካተተ ካልሆነ ውጤታማ ሊሆን እንደማይችል አቶ ሳልቫቶሬ ጄራቺ አስረድተዋል። 

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባትን ለመቀበል ሕጋዊ ማንነት የሚገልጽ መታወቂያ ካርድ ይዞ ቀርቦ መመዝገብ እንደሚያስፈልግ ያስረዱት አቶ ሳልቫቶሬ፣ ያለ ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ እና የመታወቂያ ካርድ የሚንቀሳቀሱ በርካታ ሰዎች መኖራቸውን አስታውሰው፣ አንድ ሰው የመኖሪያ ፈቃድ ባይዝም በአገሪቱ ክልል ውስጥ የሚኖር ማንም ሰው የሕክምና አገልግሎት የማግኘት መብት እንዳለው የሚደነግግ ሕግ መኖሩን አስታውሰዋል። አንድ ሰው የሕክምና አገልግሎት ማግኘት የሚያስችል መታወቂያ ካርድ ቢኖረውውም በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ተቀባይነት ያለው አለመሆኑ ችግር እያስከተለ መሆኑን አስረድተው፣ በአገሪቱ የሚገኙ የጤና አገልግሎት ማስተባበሪያ ማዕከላት የወረርሽኙን መከላከያ ክትባት አቅርቦት መርሃ ግብሩን እንደገና በማጤን ክትባቱ ለሁሉም ሰው የሚደርስበትን መንገድ ማመቻቸት እንደሚያስፈልግ አስተያየታቸውን ገልጸዋል።

በሮም ሀገረ ስብከት የሚገኝ ካቶሊካዊ የጤና አገልግሎት መምሪያ በከተማው መሃል አንድ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት ምስጫ ጣቢያ መኖሩን ያስታወቁት አቶ ሳልቫቶሬ ጄራቺ፣ ጽሕፈት ቤታቸው በመኖሪያ ቤት እጦት ምክንያት በከተማው ጎዳናዎች የሚንከራተቱ በርካታ ሰዎች መኖራቸውን በመገንዘብ የሕክምና አገልግሎትን በመስጠት ላይ መሆናቸውን ገልጸው፣ በጣልያን ውስጥ መንግሥት በጤናው ዘርፍ ያለውን ሃላፊነት በአግባቡ በመወጣት በተለያዩ ምክንያቶች ከማኅበረሰቡ ለተገለሉት በርካታ ሰዎች የሕክምና አገልግሎትን መስጠት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ስደተኞች ወረርሽኙን የመቋቋም ከፍተኛ አቅም አላቸው ወይም የመከላከያ ክትባትን ለመውሰድ ፍላጎት የላቸውም የሚል ሐሰተኛ መረጃ በጣሊያን ውስጥ መሰራጨቱን ያስታወሱት አቶ ሳልቫቶሬ ጄራቺ፣ በዚህ እና በሌሎች የሐሰት መረጃዎች የተነሳ በጣሊያን ውስጥ ሰደተኞችን ችግር የሚደርስባቸው መሆኑን ገልጸዋል። አክለውም ስደተኞችን በተመለከተ የሚሰራጩ የሐሰት መረጃዎች በጣሊያን ብቻ ሳይሆን በመላው የዓለማችን ክፍሎች መኖራቸውን አስታውሰው፣ የጤና አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤታቸው በእነዚህ የሐሰት መረጃዎች ሳይደናገር የወረርሽኙ መከላከያ ክትባት ለስደተኞችም እያዳረሰ መሆኑን ማስገንዘብ እንደሚፈልግ፣ በሮም ሀገረ ስብከት በሚገኝ ካቶሊካዊ ዕርዳታ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት የጤና አገልግሎት መምሪያ ተወካይ የሆኑት ክቡር አቶ ሳልቫቶሬ ጄራቺ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገልጸዋል።  

17 June 2021, 16:20