ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የተራቡትን መመገብ እንደሚገባ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ዓለም አቀፍ የጥራጥሬ እህሎች ቀንን ምክንያት በማድረግ የተባበሩት መንግሥታት የእርሻ እና የምግብ ድርጅት በቅርቡ ባካሄደው የአውታረ መረብ ስብሰባ፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ መልዕክት ማስተላለፋቸው ይታወሳል። ቅዱስነታቸው በመልዕታቸው በዓለማች ውስጥ በርካታ ሰዎች፣ ከእነዚህም መካከል ሕጻናት በቂ የዕለት ምግብ ሳያገኙ ቀርተው የሚሰቃዩ መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል። አክለውም መሬትን ለእርሻ ሲጠቀሙ ጉዳት እንዳይደርስበት ጥንቃቄ ሊደረግለት እንደሚገባ እና ለመጭው ትውልድ ማሰብ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው፣ ምግብ ሲዘጋጅ መጠኑም መወሰን እንዳለበት ያሳሰቡ ሲሆን፣ እ. አ. አ ዘንድሮ በኅዳር ወር 2020 ዓ. ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ አዳራሽ ውስጥ ከድሃ ቤተሰቦች ጋር ማዕድ በተካፈሉበት ወቅት፣ የወጥ ቤት ሠራተኞችን በሙሉ ለአገልግሎታቸው ማመስገናቸው ይታወሳል።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በጤናው ዘርፍ ብቻ ሳይሆን በምግብ ቤቶችም ጭምር ከፍተኛ ጉዳት ማስከተሉ የሚታወስ ሲሆን በአንዳንድ የዓለማችን ክፍሎች ምግብ ቤቶች ለረጅም ወራት ተዘግተው እንዲቆዩ የተገደዱ ሲሆን ይህም በሠራተኞች ቤተሰባዊ ሕይወት ከፍተኛ ጫናን ያስከተለ መሆኑ ታውቋል። ጣሊያንን ጨምሮ በብዙ አገሮች ሁኔታዎች ተለውጠው ምግብ ቤቶች በመጠኑም ቢሆን ሥራቸውን መጀመራቸው ተስተውሏል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እ. አ. አ ሰኔ 16/2014 ዓ. ም በሮም ከተማ በተካሄደ ጉባኤ ላይ፣ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር የሚያሳልፉት ሰዓት ማነስ እንደሌለበት ገልጸው፣ ሥራ ቢበዛባቸውም ከልጆቻቸው ጋር አብረው የሚሆኑበት በቂ ጊዜ ሊኖራቸው እንደሚገባ ማሳሰባቸው ይታወሳል።
በአስከፊው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ቤተክርስቲያን በከፍተኛ ችግር ውስጥ ለወደቁት፣ በረሃብ እና በውሃ ጥም ለሚሰቃዩት የዓለማችን ሕዝቦች ዕርዳታዋን በማቅረብ ላይ መሆኗን በጣሊያን ውስጥ ቦሎኛ ከተማ የሚገኝ የዕርዳታ መስጫ ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት ክቡር አባ ጃንፓውሎ ካቫሊ አስታውቀዋል። ዳይሬክተሩ በማዕከሉ የሚቀርቡ የዕርዳታ ተግባራትን በማስተወስ እንደተናገሩት፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ባስከተለው የማኅበራዊ ኑሮ መቃወስ ምክንያት በርካታ ሰዎች በችግር ውስጥ እንደሚገኙ ገልጸው፣ ማዕከላቸው ለዕርዳታ ፈላጊዎች ከዕለታዊ ምግብ አቅርቦት ጀምሮ የተለያዩ አገልግሎቶችን በማቅረብ ላይ መሆኑን አስረድተዋል።
ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እ. አ. አ ሰኔ 7/2015 ዓ. ም በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ ከተገኙት ምዕመናን ጋር ሆነው ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ባቀረቡት ጸሎት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋው እና በደሙ በየዕለቱ የሚመግበን መሆኑን አስታውሰው፣ በከፍተኛ ማኅበራዊ ችግር እና ስቃይ ውስጥ ሆነው ዕርዳታን ለሚለምኑት በሙሉ የዕርዳታ እጃችንን መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ማሳሰባቸው ይታወሳል። በጣሊያን ውስጥ ግንቦት 26 የወጥ ቤተኞች ባልደረባ የሆነው የቅዱስ ፍራንችስኮስ ካራቾሎ መታሰቢያ ቀን መሆኑ ታውቋል። በጣሊያን ውስጥ አብሩዞ ክፍለ ሀገር እ. አ. አ በ1563 ዓ. ም. የተወለደው ቅዱስ ፍራንችስኮስ ካራቾሎ፣ እንደ አሲዚው ቅዱስ ፍራንችስኮስ ከሃብታም ቤተሰብ የተወለደ ሲሆን፣ በምድራዊ ሃብቱ እግዚአብሔርን እና ድሆች ሲያገለግል የኖረ ርኅሩኅ ሰው መሆኑ ታውቋል።