በሶርያ ላይ የተጣለው የኤኮኖሚ ማዕቀብ አገሪቱን ለከፍተኛ ችግር የሚዳርጋት መሆኑ ተነገረ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በሶርያ ውስጥ ሰዎች ዕለታዊ ምግብን ለማግኘት ሰዓታትን የሚፈጅ ረጅም ሰልፍ እንደሚሰለፉ የደማስቆ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሳሚር ናስር በስደት ላይ ለምትገኝ ቤተክርስቲያን ዕርዳታን ለሚያደርግ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን ተናግረዋል። ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሳሚር በሶርያ ላይ የተጣለው ዓለም አቀፍ የኤኮኖሚ ማዕቀብ የሶርያን ሕዝብ ለከፋ ስቃይ የሚዳርግ፣ ዕርዳታ ለጋሽ መንግሥታት እና ግለሰቦች የገንዘብ እገዛን እንዳያደርጉ የሚከለክል፣ ኢ-ፍትሃዊ እና የሕዝቡን ስቃይ የሚያባብስ የፍጆታ ሸቀጦችን እጥረት የሚጨምር መሆኑን አስረድተዋል።
ሶርያ በችግር እና በማዕቀብ መካከል
ሶርያ የሚትገኝበት ኤኮኖሚያዊ ቀውስ ከፍተኛ ሆኖ ባለበት ወቅት ዓለም አቀፍ ማዕቀብ መጣሉ፣ ዋና የንግድ አጋር በሆነች ሊባኖስ ላይ ከደረሰው የኤኮኖሚ ውድቀት ጋር ተዳምሮ በሶርያ ላይ ከፍተኛ የምግብ እጥረትን ማስከተሉ ታውቋል። በሶርያ ውስጥ የእርስ በእርስ አመጽ ከመጀመሩ ማለትም ከአውሮፓዊያኑ 2011 ዓ. ም በፊት የአንድ ኪሎ ዳቦ ዋጋ 15 የሶርያ ሊሬ እንደነበር፣ ዛሬ ግን የአንድ ኪሎ ዳቦ ዋጋ ከ100 እስከ 500 የሶርያ ሊሬ የሚያወጣ መሆኑ ታውቋል። በሶርያ የአሌፖ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዣን ክሌሜንት ዣንባርት በበኩላቸው፣ በሶርያ ላይ የተጣለው ዓለም አቀፍ የኤኮኖሚ ማዕቀብ የሕዝቡን ስቃይ ከመጨመር እና ድህነት ከማስፋፋት ሌላ ምንም ፋይዳ የለውም ብለዋል። ኤኮኖሚያዊ ማዕቀቡ የሶርያን ሕዝብ የሚጎዳ እንጂ በመንግሥት ላይ የሚያስከትለው ምንም ዓይነት ጫና እንደማይኖር፣ በስደት ላይ ለምትገኝ ቤተክርስቲያን ዕርዳታን የሚያደርግ ጳጳስዊ ፋውንዴሽን ዋና ተጠሪ ክቡር አቶ አሌሳንድሮ ሞንቴዱሮ ለቫቲካን ዜና አገልግሎት አስታውቀዋል።
በሶርያ ላይ የተጣሉት ዓለም አቀፍ የኤኮኖሚ ማዕቀቦች የአገሪቱን ሕዝቦች ወደ አዲስ የእርስ በእርስ ጦርነት እና ስቃይ የሚዳርግ መሆኑን ክቡር አቶ አሌሳንድሮ ሞንቴዱሮ ገልጸው፣ ይህም ከረጅም ዓመታት ወዲህ በግልጽ ሲታይ የቆየ ነው ብለዋል። በመሆኑም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በሶርያ ውስጥ የባንክ አገልግሎቶች እንዲኖሩ፣ ከለጋሽ አገሮች እና ግለሰቦች የሚላኩ የገንዘብ ዕርዳታዎች በከፍተኛ ችግር ውስጥ የሚገኘውን የሶርያ ሕዝብ ለመርዳት የሚያችል መሆን ይኖርበታል ብለዋል። የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድምጽ የባንክ አገልግሎት እንዲኖር የሚያደርግ ብቻ ሳይሆን ምግቦች እና ሸቀጣ ሸቀጦች ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ የሚያደርግ እንደሚሆን ክቡር አቶ አሌሳንድሮ ሞንቴዱሮ አስረድተዋል። በሶርያ ውስጥ መልሶ የማቋቋም ሥራ አለመጀመሩ ወይም አለመቀጠሉ ብች ሳይሆን በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች ለተረጂዎች የዕለት ዳቦን እንኳን ማቅረብ ያልተቻለበት ሁኔታ መኖሩን አክለው ገልጸዋል።
በስደት ላይ ለምትገኝ ቤተክርስቲያን ዕርዳታን የሚያደርግ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን በበኩሉ ከወራት ወዲህ ለሶርያውያን ዕርዳታን ማቅረብ ያልቻለ መሆኑን አስታውቆ፣ በችግር ውስጥ ለሚገኝ የሶርያ ሕዝብ የሚላከው ዕርዳታ የሚገኘው ከጳጳሳት፣ ከሀገረ ስብከቶች እና ከቁምስናዎች መሆኑን ጳጳሳዊ ፋውንዴሽኑ አስረድቷል። ፋውንዴሽኑ በማከልም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በቆራጥ ኤኮኖሚያዊ ማዕቀቡ በሶርያ ያለውን ግዥ መንግሥት ለማንበርከክ ቢያስብም ወደ ከፋ ችግር ውስጥ የሚገባው ንጹሃኑ የሶርያ ሕዝብ መሆኑን ጳጳሳዊ ፋውንዴሽኑ አስረድቷል።