ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለቅድስት መንበር ሠራተኞች መልካም ምኞታቸውን ሲገልጹ   ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለቅድስት መንበር ሠራተኞች መልካም ምኞታቸውን ሲገልጹ  

አባ ማርቲን የወንጌል ስርጭት ምዕመናንን በአካል ማግኘት እንደሚጠይቅ ተናገሩ

ክቡር አባ ጄምስ ማርቲን የቫቲካን ሚዲያ ባለሙያዎች ቅዳሜ ኅዳር 3/2015 ዓ. ም. ያካሄዱትን ጠቅላላ ስብሰባ በማስታወስ ከዜና አገልግሎቱ ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል። አባ ማርቲን በቃለ ምልልሳቸው የካቶሊክ ሚዲያ ባለሙያዎች ምን ጊዜም ቢሆን ትኩረታቸውን በኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት ላይ በማድረግ በተቻለ መጠን ውጤታማ የሚዲያ ቋንቋዎችን ተጠቅመው ሰዎችን ለመድረስ ጥረት እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቫቲካን ዜና አገልግሎት አካል የሆነው የቫቲካን መገናኛ ጉዳዮች መምሪያ አስተዳዳሪዎች፣ አባላት እና አማካሪዎች የመገናኛ ብዙኃን መሣሪያዎች ማምረቻ ተቋማትን ጎብኝተዋል። ከጎብኚዎቹ መካከል አንዱ የነበሩት ክቡር አባ ጄምስ ማርቲን፣ ቤተ ክርስቲያን እንዴት በይበልጥ ውጤታማ በሆነ መንገድ የወንጌል መልዕክትን ወደ ምዕመናን ማድረስ የምትችልበትን መንገድ ከልምዳቸው በመነሳት ያላቸውን ሃሳብ አካፍለዋል። ክቡር አባ ማርቲን ተቀማጭነቱ ኒውዮርክ በሚገኝ የአሜሪካ ካቶሊካዊ ሚዲያ በኩል ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን፣ እምነቷን እና ባሕሏን አስመልክተው የሚታተሙ ጽሑፎች ርዕሠ አንቀጽ ዋና አዘጋጅ መሆናቸው ታውቋል። 

ሁሉን አቀፍ እና እውነተኛ ግንኙነት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቫቲካን መገናኛ ባለሙያዎችን ቅዳሜ ኅዳር 4/2015 ዓ. ም. በሐዋርያዊ አዳራሽ ተቀብለው መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት የመገናኛ ባለሙያዎች ዘወትር እውነትን እንዲፈልጉ፣ የጥላቻ ንግግርን እንዲታገሉት እና ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ እንዲሆኑ ተናግረው፣ የእግዚአብሔር ድምጽ በሥራቸው ውስጥ ማስተጋባት እንዳለበት ማሳሰባቸው ይታወሳል። ቅዱስነታቸው በዕለቱ ለአባላቱ ባደረጉት ንግግር፣ "መጸለይን መማር” በሚል ርዕሥ በአባ ማርቲን የተጻፈ መጽሐፍ ለሁሉ ሰው መመሪያ እንዲሆን የተዘጋጀ በመሆኑ እንዲያነቡት አደራ ብለዋል። ቅዱስነታቸው በዕለቱ ባደረጉት ንግግር፣ የሚዲያ ባለሙያዎች ወደ ታዳሚዎቻቸው ዘንድ እንዲሄዱ፣ ሊያጋጥሟቸው የሚችሉ አደጋዎች ቢኖሩም ማኅበራዊ ሕይወትን በተጨባጭ እየኖሩ ከእውነታዎች ጋር የሚጓዙ እና የሚከታተሉ፣ ክርስቲያናዊ እና ሰብዓዊ እሴቶችን ከሌሎች ጋር እንዲጋሩ ማሳሰባቸው ይታወሳል።

በዛሬ ዓለም ወንጌልን ለሌሎች ማካፈል

በቫቲካን መገናኛዎች ጠቅላላ ስብሰባ ላይ በዛሬው ዘመን ቅዱስ ወንጌልን እንዴት በተሻለ መንገድ ለሌሎች ማስተላለፍ እንደሚቻል አስመልክቶ የተደረገውን ውይይት ያስታወሱት ክቡር አባ ማርቲን፣ በመሠረታዊነት ሁሉም የሐሳብ ልውውጥ በኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት ላይ ያተኮረ መሆን እንዳለበት፣ በተለይም በዛሬው ዘመን በሚቀርቡ ውስጣዊ የፖለቲካ ጥያቄዎች እና ክርክሮች የተነሳ የቅዱስ ወንጌል ዋና መልዕክት ስርጭት የመቀነስ አዝማሚያ ሊኖር እንደሚችል ተናግረዋል። "በኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት ላይ ማትኮር አስፈላጊ ነው" ያሉት አባ ማርቲን፣ ይህም ሰዎች እምነታቸውን እንዲያሳድጉ ወይም እንዲያድሱ ሊያደርጋቸው እንደሚችል ገልጸው፣ ይህ ጥረት ከወገናዊ ልዩነቶች ለመውጣት እንደሚያግዝ አስረድተዋል።

ሰዎችን ወደሚኖሩበት ሥፍራ ሄዶ ማግኘት

በመገናኛ ብዙኃን አንጻር አማኞችን ሆነ ያማያምኑትን መድረስ ወይም ማግኘት ማለት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በአገልግሎቱ እንዳደረገው ሁሉ፣ ሰዎችን በሚኖሩበት ሥፍራ ሄዶ ማግኘት እንደሆነ ተናግረዋል። ዛሬ በዲጂታሉ ዓለም በፌስቡክ ወይም በትዊተር አማካይነት ከሚደረግ ግንኙነት ይልቅ የሚዲያ ባለሞያዎች ሰዎችን በአካል እንዲያገኟቸው በማለት ክቡር አባ ማርቲን ምክራቸውን ለግሰዋል።

ሌላው እና ሁለተኛው ነጥብ በንግግርም ሆነ በመገናኛ ብዙሃን የሰው ልጅ መስተጋብር አዳዲስ ባህሎችን የፈጠሩ የጋራ መግባቢያ ቋንቋዎችን በመጠቀም ከሌሎች ጋር መነጋገር እና መወያየት እንደሚያስፈልግ አባ ማርቲን አሳስበዋል። ኢየሱስ አናጺ ቢሆንም በአሳ አጥማጆች ቋንቋ መናገሩን ያስታወሱት አባ ማርቲን፣ ለመረዳት ቀላል የሆኑ ቃላትን፣ ምሳሌዎችን እና ታሪኮችን መጠቀም እንደሚያስፈልግ፣ በካቶሊክ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎችም ሰዎችን ከሚኖሩበት ሥፍራ ደርሰው በቋንቋቸው የሚያነጋግሯቸው ከሆነ ስህተት የማያጋጥማቸው መሆኑን አስረድተዋል።

15 November 2022, 17:00