ፈልግ

ሙሴ የእስራኤላዊያንን ሕዝብ ሲመራ ሙሴ የእስራኤላዊያንን ሕዝብ ሲመራ   (SVasco)

የሙሴ ጸሎት

“አትፍረዱ! ነገር ግን ብዙ ኃጢያት ለሰሩ ሰዎች አማልዱ” !

የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብ

ነገር ግን ሙሴ የአምላኩን የእግዚአብሔርን ቸርነት ፈለገ፤ እንዲህም አለ፤ “እግዚአብሔር ሆይ በታላቅ ሥልጣንህና በኀያል ክንድህ ከግብፅ ባወጣኸው ሕዝብህ ላይ ቍጣህ ለምን ይነዳል? ግብፃውያን፣ ‘በተራራዎቹ ላይ ሊገድላቸው ከገጸ ምድርም ሊያጠፋቸው ስለ ፈለገ ነው ያወጣቸው’ ለምን ይበሉ? ከክፉ ቍጣህ ተመለስ፤ ታገሥ፤ በሕዝብህም ላይ ጥፋት አታምጣ። ለባሪያዎችህ ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለእስራኤል፣ ‘ዘርህን እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛዋለሁ፤ ለዘርህም ተስፋ አድርጌ የሰጠኋቸውን ይህችን ምድር ሁሉ እሰጣቸዋለሁ፤ ለዘላለምም ርስታቸው ትሆናለች’ በማለት በራስህ የማልኸውን አስታውስ።” ከዚያም እግዚአብሔር ታገሠ፤ በሕዝቡም ላይ አመጣባቸዋለሁ ያለውን ጥፋት አላመጣባቸውም (ዘፀዐት 32 11-14)።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በጸሎት ጭብጥ ዙሪያ ላይ እያደረግነው በምንገኘው የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ “በቀላል መንገድ” ከሚጸልዩ ሰዎች  ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንዲኖረው እግዚአብሔር እንዳልፈለገ ተረድተናል። ሙሴ ከመጀመርያ ቀን ጀምሮ “ደካማ” ሊባል  የሚችል ተወያይ አልነበረም።

እግዚአብሔር ሲጠራው ሙሴ በሰውኛ አገላለጽ ለእርሱ “ውድቀት” ነበር። የዘፀአት መጽሐፍ በምድያም ምድር ውስጥ ተሸሽግ ይኖር እንደ ነበረ ይገልጻል። በወጣትነቱ ለሕዝቡ ርህራሄ አሳይቷል ፣ እናም የተጨቆኑ ሰዎችን ይከላከል እንደ ነበረ ይናገራል። ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ የፈጸመው ተግባር መልካም ዓላማዎችን የያዘ ቢሆንም ነገር ግን የፈጸመው የፍትህ ተግባር ሳይሆን ከእጁ የመጣው ኅይለኛነት ነበር። እውን ሊሆኑ የሚገባቸው የግል ሕልሞቹ ተኮላሽተዋል፣ ሙሴ ከእንግዲህ ወዲህ በስራው ሂደት ውስጥ በፍጥነት እንደሚነሳ የታሰበ ተስፋ ሰጭ ባለስልጣን አይደለም፣ ይልቁንም ዕድሎችን የሚያባክን እና አሁን የእርሱ ያልሆኑትን መንጋዎች ወደ ግጦሽ የሚያሰማራ ተራ ሰው ሆነ። ጸጥ ባለው በምድያም ምድረ በዳ ውስጥ እግዚአብሔር የሚቃጠል በሚመስል ቁጥቋጦ ተግልጦ “እኔ የአባቶችህ የአብርሃም፣ የይስሐቅ፣ የያዕቆብ አምላክ ነኝ” አለው። በዚህ ጊዜ ሙሴ እግዚአብሔርን ፊት ለፊት ማየት ስለ ፈራ ፊቱን ሸፈነ” (ዘፀ 3፡6) በእዚያን ወቅት እግዚአብሔር ለሙሴ ጥሪ አቀረበለት።

ሙሴ በፍርሃቶቹ እና በተቃውሞዎች የተነሳ የእስራኤልን ሕዝብ እንደገና እንዲንከባከበው የሚናገረውን እግዚአብሔር ለዚያ ተልእኮ ብቁ አይደለሁኝም በማለት ይቃወማል፣ የእግዚአብሔርን ስም አያውቅም ፣ በእስራኤላዊያንም የሚታመን አልመሰለውም፣ የሚንተባተብ ምላስ ነበረው። በሙሴ ከንፈሮች ላይ በብዛት የሚታየው ቃል ፣ በሚያቀርበው ጸሎት ሁሉ የሚነሳው ቃል “ለምን?” የሚለው ጥያቄ ነው። ለምን ላከኝ? ይህንን ሕዝብ ለምን ነፃ ማውጣት ፈለክህ? እነዚህን የመሳሰሉ ብዙ ጥያቄዎችን ያነሳ ነበር። በመጀመርያዎቹ አምስት የመጽሐፍ ቅዱስ የሕግ መጽሐፍት ውስጥ አንድ አስገራሚ ታሪካዊ እናነባለን፣ እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን “በእስራኤላውያን ፊት እኔን ቅዱስ አድርጋችሁ ለማክበር ስላልታመናችሁብኝ ይህን ማኅበረ ሰብ ወደምሰጠው ምድር ይዛችሁ አትገቡም” (ዘኁልቁ 20፡12) አላቸው በማለት ይናገራል።

በእነዚህ ፍርሀቶች፣ ሙሴ ብዙውን ጊዜ የምያቅማማ ልብ  ስለነበረው በዚህ ባሕሪው እኛን ይመስላል። እኛም በእርሱ ድክመቶች እና በእርሱ ጥንካሬዎች የተነሳ ተደነቅን። የመለኮታዊ አምልኮ መስራች፣ በታላቅ ምስጢሮች መካከል የሚገኝ፣ ሕጉን ለሕዝቡ እንዲያስተላልፍ በአደራ የተሰጠው፣ በዚህ ምክንያት በተለይ በፈተና እና ኃጢያት በሚፈጽሙበት ወቅት ከህዝቦቹ ጋር የጠበቀ ትብብር እንዲኖር አደረገ። ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር የጠበቀ ወዳጅነት በመመስረቱ የተነሳ ፊት ለፊት ከእርሱ ጋር መነጋገር ይችላል (ዘፀ 33፡11 ይመልከቱ)፣ እናም ለፈጸሙት ኃጢአት ምሕረት ከሚያስፈልጋቸው፣ በፈተና ውስጥ ለሚገኙ፣ በግብፅ በግዞት ላይ እያሉ ‘መልካም ኑሮ እንኖር ነበረ’ ብለው ድንገተኛ የቁጭት ስሜት ለሚሰማቸው ሰዎች እርሱ ቅርብ እና ወዳጃዊ የሆነ ግንኙነት ነበረው።

ስለሆነም ሙሴ ባለሥልጣንና አምባገነን መሪ አልነበረም፣ የኦሪት ዘኁልቁ መጽሐፍ እሱን በተመለከተ “ሙሴ በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ትሑት ሰው ነበር” (ዘኁልቁ 12፡3) በማለት ሙሴን ይገልጸዋል። ሙሴ ትልቅ ቦታ ቢሰጠውም በጉዞአቸው በእግዚአብሔር በመተማመን በሚጓዙ በመንፈስ ድሆች ከሆኑ ሰዎች ጋር አንዱ በመሆን አብሯቸው ይጓዝ ነበር።

ስለዚህ ሙሴ ያደርገው የነበረው ፀሎት የምልጃ ጸሎት ነው (የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ቁ. 2574 ይመልከቱ)። በእግዚአብሄር ላይ ያለው እምነት ሙሉ በሙሉ አንድ ነው፣ ለህዝቡ የአባትነት ስሜት እንዲኖረው አድርጎታል። ወደ እግዚአብሔር እጁን በመዘርጋት በሰማይ እና በምድር መካከል ድልድይ ሆኖ ያገለግል ነበር በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ስለእርሱ ይናገራል። በጣም አስቸጋሪ በሆኑባቸው ወቅቶች እንኳን ሳይቀር፣ ሰዎች እግዚአብሔርንና እርሱን ሙሴን ራሱ ማለት ነው መሪዎች መሆናቸውን ውድቅ በሚያደርጉበት እና በወርቅ የተሰራ ጥጃ ማምለክ በጀመሩበት ቀን እንኳን ሳይቀር ሙሴ ህዝቡን ለመተው አልፈለገም። “ስለዚህ ሙሴ ወደ እግዚአብሔር ተመልሶ እንዲህ አለው፤ “ወዮ እነዚህ ሕዝብ የሠሩት ምን ዐይነት የከፋ ኀጢአት ነው! ለራሳቸውም የወርቅ አማልክት ሠሩ። አሁን ግን አቤቱ ኀጢአታቸውን ይቅር በል፤ ያለዚያ ግን ከጻፍኸው መጽሐፍ እኔን ደምስሰኝ” (ዘፀዐት 32፡31-32)።

እውነተኛ አማኞች በመንፈሳዊ ህይወታቸው የሚያዳብሩት ጸሎት ይህ ሊሆን ይገባል። ምንም እንኳን ሰዎች ደካሞች ቢሆኑና ከእግዚአብሔር ርቀው ቢኖሩም ሙሴ በጸሎቱ አላወገዛቸውም ነበር፣ እነርሱን አልካዳቸውም ነበር። የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል በእግዚአብሔር እና በሕዝቡ መካከል “ድልድዮች” ለሆኑት ቅዱሳን የዚህ ዓይነት የምልጃ ተግባር አስፈላጊ ነው። ሙሴ በዚህ ረገድ የእኛ ጠበቃ እና አማላጅ የሆነው የኢየሱስ የመጀመርያው ታላቅ ነቢይ ነው (የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ቁ. 2577 ይመልከቱ)።

ልክ እንደ ኢየሱስ እኛም ለዓለም እንድናማልድ፣ ዓለም ድክመቶች ቢኖሩበትም እንኳን ‘አሁንም የእግዚአብሔር ነው’ ብለን እንድናስታውስ ሙሴ ኢየሱስ ባማለደው መልኩ እንዳማለደው ሁሉ እኛም በዚህ መንገድ የምልጃ ጸሎት እንድናደርግ አጥብቆ አሳስቦናል። ለጻድቃን ቡራኬ ምስጋና ይግባውና በሰው ልጆች ላይ በማንኛውም ጊዜ እና በታሪክ ሂደት ውስጥ የምሕረት ጸሎት በማድረግ ዓለም ወደ ፊት እንድትጓዝ መደገፍ እና ማገዝ ያስፈልጋል።

ምንጭ፡ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሰኔ 10/2012 ዓ.ም በቫቲካን ካደረጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ የተወሰደ።

የእዚህ አግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

14 September 2023, 16:09