ፈልግ

የኢትዮጲያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባሄ አባላት የኢትዮጲያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባሄ አባላት  

የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት 56ኛ መደበኛ ጉባኤ እየተካሄደ ይገኛል

በኢትዮጵያ ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ - ኢኩስታ ቅጥር ጊቢ ውስጥ በሚገኘው የጳጳሳት መኖሪያ አዳራሽ ውስጥ ከዛሬ ታህሳስ 10 እስከ 12/ 2016 ዓ.ም. ድረስ የሚቆየው የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት 56ኛ መደበኛ ጉባኤ እየተካሄደ ሲሆን፥ በዚህም ጉባኤ ላይ ከአዲግራት ሃገረ ስብከት ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ተስፋስላሴ በስተቀር የአስራ አንዱ ሃገረ ስብከቶች ብጹአን ጳጳሳት እና የቅድስት መንበር ተወካይ የሆኑት ብጹእ አቡነ አንቱዋን ካሚሌሪ እንደተገኙ ለማወቅ ተችሏል።

 አዘጋጅ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ   

የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ በዓመት ሁለት ጊዜ ማለትም በታህሳስ ወር እና በሓምሌ ወር የሚደረግ ሲሆን ፥ በዚህኛው ጉባኤ ላይም ዋና አጀንዳ ተደርጎ ለውይይት የሚቀርበው በአስር ዓመቱ የቤተክርስቲያ ዕቅድ አፈፃጸም ላይ እንደሆነ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ጸሃፊ የሆኑት ክቡር አባ ተሾመ ፍቅሬ ስለ ጉባኤው አስመልክተው በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል። ክቡር አባ ተሾመ እንደተናገሩት ከዚህን ጉባኤ ቀደም ብሎ ማለትም በትናንትናው ዕለት ቤተክርስቲያኒቷ ለመላው ዓለም በይፋ ያስተዋወቀችውን የአስር ዓመት ዕቅዶች በሁሉም የቤተክርስቲያኒቷ መዋቅሮች ላይ ተግባር ላይ የሚውልባቸውን አቅጣጫዎችን እንደሚያመላክት አብራርተዋል።

በዚህ ጉባኤ ላይ ከብጹአን አባቶች የተሰበሰቡ አጀንዳዎች ላይ ውይይት የሚደረግ ሲሆን፥   

ክቡር አባ ተሾመ አክለው እንደተናገሩት ጉባኤው በቀጣይነትም በጥቅምት 2017 ዓ.ም. በሮም ለሚካሄደው የሲኖዶስ ጉባኤ ዝግጅት ሂደት ላይ የሚወያዩ ሲሆን በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ቤተክርስቲያን ደረጃ የሚደረጉ ዝግጅቶች ላይ አቅጣጫ እንደሚሰጡ ተገልጿል።  

ጉባኤው ከዚህም በተጨማሪ የፊታችን ሰኔ 2016 ዓ.ም. በየአምስት ዓመቱ የሚካሄደውን እና በላቲኑ ቋንቋ ‘አድ ሊሚና’ የተሰኘውን የብፁዓን የኢትዮጵያ ጳጳሳት ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጋራ ተገናኝተው ውይይት እና የስራ ጉብኝት እንደሚያደርጉ እና ከቅድስት መንበር ጋር ያላቸውን ኅብረት እንደሚያድሱ ተገልጿል። በዚህም ጉብኝት ብጹአን ጳጳሳት በቅዱስ ጴጥሮስ መቃብር ቦታ ተገኝተው ለኢትዮጵያ እና ለዓለም የሚጸልዩ ሲሆን የሁሉንም ሀገረስብከቶች ሐዋርያዊ ሥራዎች በዝርዝር ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት እና አብረው ለሚሰሩ ብጹዓን አባቶች እንደሚያቀርቡ እና ለዚህም ቅድመ ዝግጅት የሚያስፈልጉ ጉዳዮች ላይ ብጹአን ጳጳሳት በ56ኛው ጉባኤ ላይ እንደሚወያዩ ተገልጿል።

አጀንዳዎቹ በዋናነት ባለፉት ስድስት ወራት የቤተክርስቲያኒቷ ሃዋሪያዊ እንቅስቃሴ እንዴት እንደነበር እና በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ምን ይጠብቀናል ፥ ምንስ መሰራት አለበት በሚለው ሃሳብ ዙሪያ እንደሚወያይም ተገልጿል።

ይህ ጉባኤ ለሶስት ተከታታይ ቀናት ተካሂዶ መቋጫውን ታህሳስ 12 ቀን 2016 ዓ.ም. እንደሚያደርግ የተነገረ ሲሆን፥ ክቡር አባ ተሾመ ፍቅሬ በጉባኤው ማጠቃለያ ላይ ብፁዓን ጳጳሳት የሚያስተላልፉትን መልዕክት ለምዕመናን እንደሚያስተላልፉ ገልጸው መላው ካቶሊካውያን እና በጎ ፍቃድ ያላቸው ሁሉ ጉባኤው የተሳካ እንዲሆን በጸሎት እንዲተባበሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

     

 

 

21 December 2023, 09:32