ፈልግ

ሎሬንዞ ዲ ቺያቾ ከሥራ ባልደረቦቹ ጋር - የሪዳጄ ግቦች ሰዎችን ከመንገድ ላይ በማንሳት ማሰልጠን፣ ማዋሃድ፣ ክብርን በስራ መመለስ፣ መንከባከብ ነው ሎሬንዞ ዲ ቺያቾ ከሥራ ባልደረቦቹ ጋር - የሪዳጄ ግቦች ሰዎችን ከመንገድ ላይ በማንሳት ማሰልጠን፣ ማዋሃድ፣ ክብርን በስራ መመለስ፣ መንከባከብ ነው 

‘ሪዳጄ’ የተባለው ተቋም ቤት አልባ ሰዎችን አትክልተኞች እንዲሆኑ ረድቷቸዋል

ጣሊያናዊው የኮምፒዩተር መሐንዲስ ሎሬንዞ ዲ ቺያቾ በአንድ ትልቅ ኩባንያ ውስጥ ተቀጥሮ ይሠራበት የነበረውን ሥራውን ትቶ በተከፈለው የስንብት ክፍያ በመጠቀም “ሪዳጄ” የተባለውን ድርጅት ከፍቷል። ድርጅቱ ቤት አልባ የሆኑ ሰዎችን የተረሱ የሮም አረንጓዴ አካባቢዎችን መልሶ በማልማት ሥራ ላይ በማሰማራት እራሳቸውን እንዲጠብቁ ብሎም አከባቢውንም እንዲንከባከቡ የሚያደርግ ተቋም ነው። ይህንንም በማስመልከት “ማንም ሰው እራሱን ማዳን አይችልም፥ ነገር ግን የእኛ ተልእኮ በአንድ ጊዜ የአትክልት ቦታውን እና የሰውን ህይወት ማዳን እና መለወጥ ነው” ብሏል ሎሬንዞ።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

“ዳጄ!” (ና!) ይህ ቃል ሮማውያን አንድን ሰው ለማበረታታት፣ ጥንካሬን ለመስጠት እና ተስፋ ላለመቁረጥ ሲሉ በልበ ሙሉነት የሚናገሩት ቃል ነው። እንዲሁም የሚወዱት ቡድን ነጥብ ሲያስቆጥር ወይም የጓደኛን ስኬት ሲያከብሩ ደስታቸውን የሚገልፁበት ነው። በዚህ አግባብ “ሪዳጄ” የሚለው ቃል ደግሞ እንደገና የመጠናከር ወይም የመደራጀትን ትርጉም ያመለክታል። በመሆኑም የሎሬንዞ ዲ ቺያቾ ተቋም እንደገና ሁለተኛ ሕይወትን የሚሰጥ እና በሮም ጎዳናዎች ላይ ለሚኖሩ በጣም ብዙ ቤት የሌላቸው ሰዎችን የመቤዠት ዕድል ይሰጣል።

ከአሥር ዓመታት በፊት፣ የጎኤታ ከተማ ነዋሪ የሆነው የ38 ዓመቱ የኮምፒዩተር መሐንዲስ ሎሬንዞ ጥሩ ደመወዝ የሚያገኝበትን ቋሚ ሥራውን በመተው ቤተክርስቲያን እና የተለያዩ የበጎ አድራጎት ቤተ ክርስቲያን ድርጅቶች ሁል ጊዜ ለመፍታት የሚሞክሩትን ማኅበራዊ ጉዳይ ለመፍታት ራሱን ለመስጠት ወሰነ። በርግጥ ሎሬንዞ ‘ሪዳጄ’ን ከመመስረቱ በፊትም ባገኘው የስንብት ክፍያ ‘ፔድየስ’ የሚባለውን መስማት የተሳናቸውን ሰዎች የሚያግዝ መተግበሪያ በማጠናከር በ አይ ቲ ስራው ወደ ማህበራዊ ስራ ፈጣሪነት ተቃርቦ ነበር። ይህንን በማስመልከት እንዲህ ሲል ይናገራል፥ “አደጋ ደርሶበት መስማት የተሳነው ስልሆነ ብቻ አምቡላንስ መጥራት ስላልቻለ አንድ ጋብሪኤሌ ስለሚባል ታዳጊ ልጅ የሚገልጽ የቴሌቭዥን ታሪክ አየሁ። ይህ ሁኔታ በጣም ገረመኝ፥ ስለ መፍትሄውም ማሰብ ጀመርኩ፣ የመስማት ችግር ያለባቸው ሰዎች በድንገተኛ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በሌላም ጊዜ ስልክ እንዲደውሉ የሚያስችለውን ሶፍትዌር የማበልፀግ ሃሳብ መጣልኝ። እንደዚህ አይነት ችግር ያለበትን ሰው አላውቅም ነበር። ገብርኤሌ የመጀመሪያ መስማት የተሳነው ጓደኛዬ ሆነ።

ፔዲየስ አሁን በ14 የዓለም ሀገራት እየሰራ ሲሆን አጠቃላይ ካፒታሉን በ700,000 ዩሮ አሳድጓል። ደንበኞቹም ጣሊያን ውስጥ ያሉ እንደ ኢጣሊያ ባንክ ፣ ቴሌኮም እና ኢነል ያሉ ትላልቅ ድርጅቶችን ያጠቃልላል። ግን ሎሬንዞ አሁንም የበለጠ ለመስራት በመፈለጉ ጉዳዩን ወደ ቤት እጦት ጉዳይ ጋር በማያያዝ አስፍቶታል። “ለ12 ዓመታት በብዙ ተግባራት እና ግዴታዎች መካከል በካሪታስ በበጎ ፈቃደኝነት መስራት ችያለሁ። የእኔ ተግባር የነበረው በዋና ከተማው ውስጥ ከገና እስከ ፋሲካ ድረስ የሚያገለግለው እና በበረዶ ወቅቶች መጠለያ የሚሆኑ ከብዙ የአደጋ ጊዜ መጠለያዎች አንዱን መክፈት እና መዝጋት ነበር” ብሏል ሎሬንዞ።

ማህበራዊ ስራ ጥሩ ንግድ ነው

“በእነዚህ በካሪታስ የሚተዳደሩትን መጠለያዎች በር የሚያንኳኩት ሁሌም አንድ አይነት ፊቶች፣ አንድ አይነት ሰዎች፣ የበለጠ የተዳከሙ፣ ያረጁ፣ የተሸበሩ እና የታመሙ መሆናቸውን ባለፉት ዓመታት ለመገንዘብ ችያለሁ ። ለራሴ እንዲህ አልኩ: 'ታዲያ የምተኛበት አልጋ እና የምበላው ትኩስ ምግብ ከመንገድ ላይ አያስወጣኝምን? በዓለም ላይ ያሉ ታላላቅ ከተሞችን ጭምር የሚያጠቃውን ይህን አሳዛኝ ሁኔታ ለመቅረፍ ምን ማድረግ እችላለሁ?’ በማለት ራሴን ጠየኩ። ይህ በእንዲህ እያለ ግን ስለ ፔዲየስ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ያጋጠመኝን ነገር ገለጽኩላቸው፤ ከሉይስ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጋር ከተደረጉት ስብሰባዎች በአንዱ ሉካ ሞንጄሊ የተባለ ተመራማሪ አገኘሁ። ይህ ተመራማሪ የተገለሉ ሰዎች በተለይም እስረኞች የቅጣት ፍርዳቸውን እንደጨረሱ የማህበራዊ እና የጉልበት ውህደትን ለመለየት የሚሞክሩትን ማበረታታት የሚቻልባቸውን መንገዶች ያጠና ነበር” ይላል ሎሬንዞ።

ከዚያም በኋላ ሎሬንዞ እና ሉካ የንግድ ሞዴል ፈጥረው አብረው መሥራት ጀመሩ። ለሮም ከተማ ትልቅ ችግር ከሆኑት ውስጥ የአረንጓዴ ቦታዎች፣ መናፈሻ ቦታዎች፣ የተተው እና የተበላሹ ቪላዎች ላይ በማተኮር ሥራቸውን መስራት ጀመሩ።

“ለራሳችን እንዲህ እንል ነበር፡- ‘ኩባንያዎች እና ዜጎች ስለተበላሹ የከተማ አከባቢዎች ቅሬታቸውን ለማቆም ፈቃደኞች ከሆኑ እና የበለጠ ንጹህ ቦታ እንዲኖር የተወሰነ ነገር ከከፈሉ የሆነ መንገድ ማግኘት እንችላለን’ በማለት ሃሳብ አቀረብን፥ ሀሳቡን ወደዱት፥ ከዛም ሥራችን ቅርፅ መያዝ ጀመረ። ይሄም ሥራ በላውዳቶ ሲ' (አካባቢያችሁን ስትንከባከቡ አካባቢው መልሶ እናንተን ይንከባከባል) ውስጥ ያሉትን አጠቃላይ እውነታዎችን እና እስካሁን የተካፈልናቸው ታሪኮችን ይዞ ወጣ" ብሏል ሎሬንዞ።

ሁለቱ ሰዎች ከኩባንያዎች፣ ግለሰቦች እና ሱቆች ጋር ስምምነት አድርገዋል። “ብዙውን ጊዜ ለትርፍ እና የትርፍ ያልሆኑ መካከል ግልጽ የሆነ ልዩነት ለመፍጠር እንሞክራለን፣ ትርፍ ክፉ ነገር ተደርጎ መታሰብ ዬለበትም” ይላል ሎሬንዞ። “ነገር ግን በሪዳጄ ለማሳየት የምንፈልገው ነገር ማህበራዊ ስራ ንግድ ሊሆን እንደሚችል እና የካፒታሊስት የገበያ ቦታ እንደሆነ ያለውን እውነታ፥ እንዲሁም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ እንዳብራሩት ለሰው ልጅ ክፍት ቦታ መስጠት የሚቻለው እሱን ወይም እሷን ወደ መሃል አስጠግቶ በማስቀመጥ ስለሆነ ያንን ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ነው” ብሏል።

ጥናቶች እንደሚያሳዩት በሀገሪቱ ከሚገኙት 70,000 ቤት የሌላቸው ሰዎች መካከል 80 በመቶው በትልልቅ ከተሞች እንዲሁም ከ20 በመቶ በላይ የሚሆኑት በሮማ ጎዳናዎች እንደሚኖሩ ያመላክታል፥ ይህም በአውሮፓ ካሉት ከተሞች ከፍተኛ አረንጓዴ አካባቢዎች ያላት ከተማ ሆና እያለ ነገር ግን እነዚህን አረንጓዴ አከባቢዎች ለመንከባከብ ከ200 ያነሱ አትክልተኞች ብቻ እንዷላት ነው።

ሪዳጄ ባጭሩ ምን እየሰራ ነው?

ሪዳጄ ከሮም ከተማ ማህበራዊ አገልግሎቶች፣ ከካሪታስ፣ከሳንት ኤጂዲዮ ማህበረሰብ እና ከትንንሽ ድርጅቶች ጋር በስነ-ልቦና ባለሙያዎች ድጋፍ ሰራተኞችን ለመምረጥ የሚረዱ ስምምነቶች አሉት። እርዳታ ከሚያስፈልጋቸው ሰዎች መካከል በአልኮል ወይም በአደገኛ ዕፅ ሱሰኝነት የሚሰቃዩ ሰዎችም ስላሉ እነሱን ወደ ሥራ ቦታ ከማስገባቱ በፊት የመልሶ ማገገሚያ መንገድ አስፈላጊ ነው። ዲ ቺያቾ ይሄንን ሲገልፅ “አብዛኞቹ መሥራት የሚችሉ ቢሆኑም መረጋጋትና ቀጣይነት ግን የላቸውም” በማለት ተናግሯል። ከጎዳና ህይወት መውጣት የቻሉት በዝግታ ግን በተረጋጋ ሁኔታ ስለሚንቀሳቀሱ ጥቂት ስህተቶችን የሚያደርጉ ናቸው። በርግጥ ከችግሮቹ አንደኛው ከመጠን በላይ መነሳሳት ወይም የጉጉት ስሜታቸው ከፍተኛ መሆኑ ነው። በአራተኛ ማርሽ የሚጀምሩ፣ በጣም ጠንካራ አሽከርካሪ የሆኑ ሰዎች በተወሰነ ደረጃ ይወድቃሉ።

የመምረጫ ሂደት ደረጃው ስስ እና ጥንቃቄ የሚፈልግ ቢሆንም፥ ነገር ግን አስፈላጊ ሂደት ነው፤ በሪዳጄ በስድስት ወራት ውስጥ አስር ሰዎችን ለመምረጥ ሲባል አንድ መቶ ያህል ቃለመጠይቆች ተካሂደዋል፥ 40 ሰዓታት የሚፈጀውን የአትክልተኝነት ኮርስ ከንድፈ ሃሳባዊ ክፍል እና የማሽኖች አጠቃቀም ስልጠናን ጨምሮ ተግባራዊ ክፍል ጋር የሚማሩ ሰዎችን ለመምረጥ የሚያስችል ነው። ከእነዚህ አስር ሰዎች መካከል ሁለቱ ብቻ በትርፍ ሰዓት ውል በኩባንያው ውስጥ እየሰሩ ይቀጥላሉ፥ ሆኖም ግን የተረጋጋ ህይወት እንዲኖሩ እና ሌላ ሥራ ለመፈለግ የሚሆናቸው ዋስትና ይሰጣቸዋል።

የሪዳጄ ሰራተኞችም የመልሶ ማልማት የሚያስፈልጋቸውን አረንጓዴ ቦታዎችን የማዘጋጀት ሃላፊነት አለባቸው። የካርታ ስራው የሚሰራው በከተማ አስተዳደሩ እና በዜጎች ጥቆማ ሲሆን በሪዳጄ ድረ-ገጽ በኩል አረንጓዴ ቦታዎች ለማልማት የሚውለውን መግዛት ይችላሉ። ቀጥሎም ግምት ከተሰራ በኋላ ስራው ይጀምራል፥ ከዛም ቡድኖች ተደራጅተው ወደ ስፍራው ይላካሉ። እስካሁን ድረስ 50 ቤት የሌላቸው ሰዎች በስልጠናው ተካፍለዋል፥ 16 ቱ ደግሞ ከሪዳጄ ጋር ሰርተዋል። ከእነዚህ ውስጥ ስምንቱ ከሌሎች ኩባንያዎች ጋር እንደ አትክልተኛ በመሆን ሌሎች ስራዎችን አግኝተዋል።

በአንድ ታሪክ ውስጥ ያለ ሌላ ታሪክ

“ከጥቂት ጊዜያት በፊት” ይላል ሎሬንዞ፥ “በጣም ታዋቂ በሆነ የህግ ድርጅት ቢሮ ውስጥ ነበርኩ፥ እና ከፊት ለፊቴ የነበረው የድርጅቱ ባለቤት ከደንበኞቹ ውስጥ ከአንዱ ጋር በስልክ ሲያወራ እንደሰማውት በዚያ በጣም ሀብታም በሆነው የሮም አካባቢ ያሉ አትክልተኞች ሥራቸውን በአግባቡ እንዳልሰሩ እና ለድርጅቱ ምንም አስተዋፅኦ እንዳላደረጉ ቅሬታውን ሲያቀርብ ነበር። ስለዚህ አልኩት፥ ከፈለግክ አትክልተኞችን እልክላችኋለሁ! ስለው እንደ እብድ አየኝና ከፊል ቁምነገር ባለው አኳሃን ድምፁን ከፍ አድርጎ፡ ‘ቤት የሌላቸውን በዚህ ሰገነት ላይ ማምጣት ትፈልጋለህ?’ አለኝ፥ ከዚያ በኋላ ግን ከፔዲየስ ጋር ያለኝን ሥራ ስለሚያውቅ ለአጋሮቹ ምንም ነገር እንደማይጠቅስ እና የሆነ ነገር ከተፈጠረ ግን እራት እንደምጋብዘው ነግሮኝ ሃሳቤን ተቀበለው። እናም ነገሮች ተሳኩ፥ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ለአከባቢው ለዓመታት አስፈላጊውን እንክብካቤ ሁሉ ስናረግለት ነበር።

እንደ አጋጣሚ ሆኖ፣ እዚያ እያለን በሮም ውስጥ አንድ ትልቅ እና የታወቀ አደባባይ ላይ ከሰገነቱ ላይ ሆነው ሲመለከቱ ከነበሩት አትክልቶቻችን አንዱ በስሜት እያየኝ እንዲህ አለኝ፡ 'ጎዳና ላይ እያለሁ የነበርኩበትን አግዳሚ ወንበር እየው። ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ጎዳና ስወጣ የተኛሁበት ወንበር ነው፥ ያኔ በተሳሳተ አመለካከት ቦታው ለመተኛት የሚመች እና ስፍራው ታሪካዊ ቦታ በመሆኑ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የሚገኝ እና ጥቂት ገንዘብ ሊተውልኝ በሚችሉ ቱሪስቶች የተሞላ መስሎኝ ነበር፥ ነገር ግን ከጥቂት ቆይታ በኋላ ጨርሶውኑ የማልታይ መሆኔ ገባኝ። በዙሪያዬ ሌሎች ወንበሮች ላይ ወይም መሬት ላይ ካርቶን አንጥፈው የሚተኙ ሌሎች ቤት የሌላቸው ሰዎች ነበሩ። በአከባቢው የቲበር ወንዝ ስላለ የማይመች እና እርጥብ ነበር። ከጥቂት ጊዜ በኋላ በሳንባ ምች በሽታ ተያዝኩ። አሁን ከላይ ወደ ታች ስመለከት የአሸናፊነት ስሜት ይሰማኛል፥ ወደ ፊት እንደተጓዝኩም ይሰማኛል፣ እንዳሸነፍኩ ይሰማኛል’ በማለት በልዩ ስሜት አጫውቶኛል” በማለት ተናግሯል ሎሬንዞ።

የአትክልት ስፍራን በማስዋብ ዓለምን መለወጥ

ከሪዳጄ ጀርባ ካለው የማህበራዊ ስራ ፈጠራ በተጨማሪ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍርንቺስኮስ በላውዳቶ ሲ' የገለጿቸው እና በላውዳቴ ዲየም ሃዋሪያዊ ማሳሰቢያቸው የሚያጠናክሩት ብዙ ዓለም አቀፋዊ ሀሳቦች እና እሴቶች አሉ። በመጀመሪያ ደረጃ፥ አረንጓዴ ቦታን በመንከባከብ ሰዎች እራሳቸውን ይንከባከባሉ። ሎሬንዞ ሃሳቡን ሲያጠቃልል “አካሄዳችን የቴራፒዮቲክ ወይም ህመምን የመፈወስ ጥበብ ዓይነት ነው፥ ምድርን በመንከባከብ ክብርን ታገኛላችሁ፣ እንደገና መታየት ትችላላችሁ። ማንም ሰው ከጎዳና ላይ በጉልበት ሊያነሳህ አይችልም፥ ብቸኛው ኃይል ፍቅር እና ጥሩነት ነው። እንደዚህ አይነት ፍቅር እንደገና እንዲስፋፋ እናግዛለን። ትሥሥርን እንገነባለን፥ ምክንያቱም ቅዱስ አባታችን እንዳሉት ማንም ብቻውን አይድንም። ላውዳቶ ሲ' የተግባራዊ ጥናቶቻችን ማረጋገጫ ሲሆን ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ እንደምንሄድ ተስፋ ይሰጠናል።

ሪዳጄ ዛሬ በፕሮጀክቱ ውስጥ ኢንቨስት ለሚያደርጉ በኩባንያው ውስጥ አክሲዮኖችን በመሸጥ ወደ ማፋጠን ፕሮግራም ገብቷል ። የጣሊያንን የባቡር መንገድ ፌሮቪ ዴሎ ስታቶ የተባለውን 'ኦፐን ኢኖቬሽን’ ጨረታን አሸንፏል። እስካሁን ከ 50,000 ካሬ ሜትር በላይ አረንጓዴ ቦታን አስውቧል፥ እና አሁን በተፈጠረው በህዝብ የገንዘብ ድጋፍ ዘመቻ ኩባንያው ትላልቅ ትዕዛዞችን ለመውሰድ በዝግጅት ላይ ነው። ከሁሉም በላይ ሁሉም ሰው ጥሩ ስሜት እንዲሰማው የሚፈልገውን ቤት ለሌላቸው ቤት ለመግዛት እና 'አስተማማኝ ቦታ' እንዲኖራቸው ታቅዷል። “የእኛ ተልእኮ የአረንጓዴ ቦታን በማልማት ዓለምን ወደ ተሻለ ሁኔታ መለወጥ ነው፥ ትርፍ ለማግኘት ከማሰብ ይልቅ የግለሰቦችን ደስታ እና ደህንነት ላይ የሚያተኩር ስነ-ምግባር እንዲኖረን ማድረግ ነው፥ በትምህርት ቤቶች እና ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እየተነጋገርን ያለነው ይሄንን ነው፥ ስለ ማህበራዊ ስራ ፈጠራ እና ስለ ሰፋፊ መዋቅሮች ስንነጋገር ነበር” በማለት መሐንዲስ ሎሬንዞ ዲ ቺያቾ ሃሳቡን አጠቃሏል ።

 

13 December 2023, 09:28