ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በ ላክ ስቴ አኔ፥ አልበርታ፣ ካናዳ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በ ላክ ስቴ አኔ፥ አልበርታ፣ ካናዳ  (Vatican Media)

የካናዳ ቤተ ክርስቲያን ከአገሬው ነባር ተወላጆች ጋር በአንድነት የጸሎት ቀንን አከበረች

በካናዳ የምትገኘው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በጉዋዳሉፔ እመቤታችን በዓል ላይ ከአካባቢው ተወላጆች ጋር የአንድነት ዓመታዊ ብሔራዊ የጸሎት ቀን አክብራለች።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ከአገሬው ተወላጆች ጋር በመተባበር ብሔራዊ የጸሎት ቀን የተከበረ ሲሆን፥ የካናዳ ጳጳሳት፡ ምእመናን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ሐምሌ 2014 ዓ.ም. በብሔረሰቡ ተወላጆች መካከል ተገኝተው በካናዳ ያደረጉትን የስድስት ቀናት የንስሐ ጉዞ፥ በተለይም በ ‘ላክ ስቴ አኔ’ ከተማ ላይ ያቀረቡትን የጸሎት ቃላቶቻቸውን እንዲያስታውሱ ጠይቀዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ካናዳ ውስጥ በሚገኘውና በርካታ ካቶሊካዊ መፈሳዊ ነጋዲያን ተጓዦች ወደ ሚጎበኙዋት እና ለአገሪቱ ተወላጆች መንፈሳዊ ጠቀሜታ ወዳለው የላክ ስቴ አኔ ከተማን ወደ ካናዳ በመጡ በሁለጠኛው ቀን ማለትም ሃምሌ 19 ቀን 2014 ዓ.ም. ጎብኝተዋል።

በነባሩ የናኮታ ሲኦክስ ህዝቦች 'የእግዚአብሔር ሐይቅ' ተብሎ የሚጠራው እና በክሪ ህዝቦች ደግሞ 'የመንፈስ ሐይቅ' የሚባለውን የላክ ስቴ አኔ ሃይቅ ስያሜውን ያገኘው እ.አ.አ. በ1842 በአልበርታ ከተማ የመጀመሪያው የካቶሊክ ተልእኮ ያቋቋመው የመጀመሪያው ሚስዮናዊ ካህን በአባ ዣን ባፕቲስት ቲቦልት እንደሆነም ተነግሯል። ይህ ቦታ ቀድሞውኑ ለዘመናት የተቀደሰ ሥፍራ ተደርጎ እንደሚታሰብ እና በአገሬው ተወላጆች ዘንድም እንደ የፈውስ ቦታነት ይታወቃል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በስቴ አኔ ቤተ መቅደስ በአብዛኛው የአገሬው ተወላጆች ከሆኑት ጋር የቅዱስ ቃሉን መስዋዕተ ቅዳሴ ያሳረጉ ሲሆን፥ አንድ ሳህን የሐይቁን ውሃ ባርከዋል። በዕለቱ ባደረጉት ንግግራቸውም “ውድ የአገሬው ተወላጆች ወንድሞችና እህቶች፣ ለእኔና ለቤተ ክርስቲያን ምን ያህል ውድ እንደሆናችሁ ልነግራችሁ መጥቻለሁ” ብለዋል።

ብሔራዊ ቀን

እ.አ.አ. ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ የሚከበረው እና በካናዳ ካቶሊካዊ የአገሬው ተወላጆች ምክር ቤት የተቀናጀ ብሔራዊ የጸሎት ቀን በመላው የካናዳ አህጉረ ስብከቶች ተከብሮ ውሏል።

ታኅሣሥ 2፣ የአሜሪካ ጠባቂ የሆነችው የጓዳሉፔ እመቤታችን እ.አ.አ. በ1531 በሜክሲኮ ለትሑቱ የሃገሬው ተወላጅ ጁዋን ዲዬጎ የታየችበት ቀን የሚከበርበት በዓል ነው።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጸሎት

ከዚህ ቀጥሎ የቀረበው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በ ላክ ስቴ አኔ ያቀረቡት ጸሎት ነው፡-

“ጌታ ሆይ፣ በገሊላ ባህር ዳርቻ ያሉ ሰዎች ለሚፈልጉት ነገር ወደ አንተ ለመጮህ እንዳልፈሩ ሁሉ፥ ስለዚህም ጌታ ሆይ እኛም በውስጣችን የተሸከምነውን ሥቃይ ሁሉ ይዘን ወደ አንተ እንመጣለን። ድካማችንን እና ትግላችንን፣ በአገሬው ተወላጆች ወንድሞች እና እህቶች ላይ የደረሰውን ጥቃት ቁስል ወዳንተ እናቀርባለን። በዚህ የተባረከ፣ መግባባት እና ሰላም በነግሰበት ቀን፥ የልምዶቻችን አለመግባባት፣ የቅኝ ግዛት አስከፊ ተፅእኖ፣ የብዙ ቤተሰቦች፣ አያቶች እና ልጆች የማይረሳ ስቃይን ወደ አንተ ይዘን መጥተናል። ጌታ ሆይ ከቁስላችን እንድንፈወስ እርዳን። ጌታ ሆይ፣ ይህ በእኛ በኩል ጥረትን፣ እንክብካቤን እና ተጨባጭ እርምጃዎችን እንደሚፈልግ እናውቃለን። እኛ ግን ይህንን ብቻችንን ማድረግ እንደማንችል እናውቃለን። በአንተ እና በእናትህ እና በአያትህ ምልጃ እናምናለን። አዎን ጌታ ሆይ፣ እናቶች እና አያቶች የልባችንን ቁስል ለማዳን ይረዳሉና በእናትህ እና በአያትህ ምልጃ ራሳችንን አደራ እንሰጣለን”
 

14 December 2023, 14:56