ቅዱስ ቁርባን
የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን
ከወንጌላውያን ክርስቲያኖች ጋር ስለ እምነት በምታደርገው ውይይት ላይ ቀዳሚ ርዕስ ሊሆን የሚገባው ቅዱስ ቁርባን ነው፡፡ ስለ ቅዱስ ቁርባን ለመወያየት ከመጀመርህ በፊት በሚገባ መዘጋጀት አለብህ፡፡ ስለ ቅዱስ ቁርባን የምታደርገውን ውይይት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረቱን የጠበቀ ለማድረግ የሚከተሉትን ክፍሎች አጥና፡- ዮሐ 6፣ ማር 14፡22-24፣ 1ኛቆሮ 10፡14-17፣ 1ኛቆሮ 11፡23-29፣ ማቴ 26፡26-28፣ ሉቃ 22፡17-20፣ሉቃ 24፡30-35።
በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 6 ላይ የምታደርገውን ጥናት ቃል በቃል እያንዳንዱን ዐረፍተ ነገር እያስተዋልክ በዝግታ ተመላለስበት፡፡ ውይይትህን ስትጀምር ደግሞ ዮሐ 4፡31-34 እና ማቴ 16፡5-12ን በማንበብ ጀምር፡፡ እነዚህ ክፍሎች ስለ ምግብ ምሳሌያዊ በሆነ ዘይቤ የሚናገሩ ናቸው፡፡ በእነዚህ ክፍሎች ውስጥ ደቀመዛሙርቱ ስለ እውነተኛ ምግብ እንደተናገረ አድርገው በቆጠሩ ጊዜ ጌታችን እንዴት እንዳረማቸው እና ንግግሩ ምሳሌያዊ እንደሆነ እንዳስረዳቸው አስተውል፡፡
ይህንን ክፍል ከዮሐንስ 6፡51 ጋር በንጽጽር አቅርብ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ክፍል ውስጥ ሥጋዬን ካልበላችሁ ሕይወት የላችሁም ይላል፡፡ ሕይወት ይኖረን ዘንድ የግድ የእርሱን ሥጋ መብላት አለብን፡፡ዮሐ 6፡52 ላይ አይሁዳውያን የጌታን ንግግር ቃልበቃል እንደተረጎሙት ልብ በል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተደጋጋሚ (ከቁጥር 53-56) “እውነት እውነት እላቹኋለሁ” እያለ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት የግዴታ ሥጋውን መብላት፣ ደሙን መጠጣት እንዳለብን ይናገራል፡፡
ቁጥር 55 ላይ ልዩ ትኩረት አድርግ፡- ‹‹ሥጋዬ እውነተኛ መብል፤ ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነው›› ይህ በእውነትም ምሳሌያዊ ንግግር አይደለም፡፡
በእንዲህ ዓይነት ውይይት ወቅት ወንጌላውያን ክርስቲያኖች ዮሐ 6፡35ን ይጠቅሳሉ ‹‹ የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፣ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም፣ በእኔ የሚያምን ሁልጊዜ ከቶ አይጠማም›› ወንጌላውያን ክርስቲያኖች ‹‹የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ›› የሚለውን ቃል ሲተነትኑት ‹‹ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእርሱ እንድናምን እና የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ ግብዣ እያቀረበልን ነው፤ ስለዚህ በእርሱ ባመንን መጠን በመንፈስ ያበለጽገናል፤ እንጀራ አካላዊ ጥንካሬን እንደሚሰጠን ሁሉ በክርስቶስ ባለን እምነት በመንፈስ ብልጽግና እናድጋለን›› ብለው ያስተምራሉ፡፡ ስለዚህ ለወንጌላውን ክርስቲያኖች ኢየሱስን ‹‹የምንበላው እና የምንጠጣው ወደ እርሱ በመምጣታችን እና በእርሱም በማመናችን ነው”።
ነገር ግን የዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ቀሪ ትረካ በሙሉ ማንበብ አለብን፡፡ በተለይ ከቁጥር 48-58 ያለውን የኢየሱስን ንግግር ማንበብ እና ራሱን ‹‹እንጀራ›› በማለት የጠራበትን የንግግሩን ይዘት ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ እዚህ ላይ ኢየሱስ እየተናገረ የሚገኘው ስለ መንፈሳዊ ምሳሌያዊ ምግብ ሳይሆን ስለራሱ ቅዱስ ሥጋ እና ክቡር ደም ነው፡፡ ኢየሱስ ‹‹እንጀራው›› የራሱ ሥጋ መሆኑን በግልጽ ይናገራል (ቁጥር 51) በግልጽ የተናገረውንም በግልጽ መቀበል ያስፈልጋል፡፡
ወንጌላውያን ክርስቲያኖች ከቁጥር 60-70 ያለውን ክፍል በመጥቀስ ኢየሱስ የተናገረው በምሳሌያዊ ዘይቤ ነው በማለት ያስተምራሉ፡፡ በተለይ በቁጥር 63 ላይ ትኩረት በማድረግ ‹‹ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ነው፤ ሥጋ ምንም አይጠቅምም፤ እኔ የነገርኳችሁ ቃል መንፈስ ነው ሕይወትም ነው፡፡›› የሚለውን ሐሳብ ያቀርባሉ፡፡ ይህንን ሐሳብ በሚገባ ለማስረዳት በዚህ መልኩ ዝግጁ ሁን፡
ሀ) በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 6 ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ቅዱስ ቁርባን ያደረገው ንግግር ከቁጥር 58-59 ባለው ሐሳብ ተደምድሟል፡፡ ከቁጥር 60-70 ያለው ንግግር በኋላ የመጣ እና ስለ እምነት የሚያወራ ሌላ ርዕስ ነው፡፡
ለ) ‹‹መንፈስ›› የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምሳሌያዊ ዘይቤ ለብሶ ለንግግር ሲቀርብ አናየውም፤ ስለዚህ ዮሐንስ 6 ምሳሌዊ ዘይቤ የያዘ ትረካ ነው ከሚለው ሐሳብ ጋር ይፃረራል፡፡
ሐ) በቁጥር 63 ላይ ኢየሱስ በሥጋ አካላዊ የሆነውን ሰው እና በመንፈስ የተሞላውን መንፈሳዊ ሰው ያነጻጽራል፡፡ ኢየሱስ ‹‹ሥጋ›› እያለ ሲናገር ምን እያመለከተ እንደሆነ በሚገባ ለማወቅ 1ኛቆሮ 2፡14-16 ያለውን ሐሳብ አንብብ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ኢየሱስ ስለ ቅዱስ ቁርባን ሲናገር ‹‹ሥጋየ፤ (የእኔ ሥጋ)›› ብሎ እንደተናገረ አስተውል፡፡ የጌታ ሥጋ የመዳናችን ምንጭ በመሆኑ ማንም ክርስቲያን በዮሐንስ ወንጌል 6፡63 ላይ ያለውን ሐሳብ ተመርኩዞ ‹‹የጌታ ሥጋ አይጠቅምም›› ለማለት አይችልም፡፡ ጌታ ኢየሱስ ‹‹ሥጋዬን ካልበላችሁ ሕይወት የላችሁም›› ይላል፡፡
መ) ኢየሱስ ስለ ቅዱስ ቁርባን ከተናገረ በኋላ ይህንን መቀበል የከበዳቸው ደቀመዛሙርት ከእርሱ እንደተለዩ እናነባለን፡- ‹‹ከዚህም የተነሳ ከደቀመዛሙርቱ ብዙዎቹ ወደኋላ ተመለሱ፤ ወደፊትም ከእርሱ ጋር አልሄዱም›› ዮሐ 6፡63፡፡ ኢየሱስ ከእነዚህ ደቀመዛሙርት ጋር ለሶስት ዓመታት ያህል አብሮ ቆይቷል፤ የአባቱን ምሥጢር ገልጦላቸዋል፤በምድር ላይ የእግዚአብሔር መንግሥት አምባሳደሮች አድርጎ በአህዛብ መካከል ሊልካቸው ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ ነገር ግን በቅዱስ ቁርባን ባለማመናቸው ምክንያት ከኢየሱስ ተለዩ፡፡ እርሱ የተናገረው ንግግር ምሳሌያዊ ንግግር ቢሆን ኖሮ ደቀመዛሙርቱን እስከማጣት ባልደረሰ ነበር፡፡ ንግግሩ ምሳሌያዊ መሆኑን ብቻ አስረድቶ ያንን ሁሉ የወንጌል ሠራዊት ባተረፈ ነበር፤ ነገር ግን ሥጋው እውነተኛ መብል፤ ደሙ እውነተኛ መጠጥ መሆኑን አላመኑም ነበርና ከእርሱ ተለይተው ወደ ኋላ ሲቀሩ ዝም አላቸው (የምርጫ ነፃነታቸውን ጠበቀላቸው)፡፡
ሠ) ከዚህም በላይ ኢየሱስ በቅዱስ ቁርባን ላይ እምነት የሌለውን ሁሉ ከእርሱ ለመለየት ዝግጁ ነበር፡፡ አስራ ሁለቱን ሐዋርያት በሚመለከት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ "እናንተ በአስራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ላይ ትፈርዳላችሁ" ብሎ ቃል ገብቶላቸው ነበር፡፡ ነገር ግን ሐዋርያቱ በቅዱስ ቁርባን ባለማመናቸው ወደኋላ ሲመለሱ ባየ ጊዜ፤ ወደ አስራ ሁለቱ ደቀመዛሙርቱ ተመልሶ "እናንተ ደግሞ ልትሄዱ ትወዳላችሁን?" (ዮሐ 6፡67) ብሎ ጠየቃቸው፡፡ በአስራሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ላይ ለመፍረድ ሥልጣን የተሰጣቸው ቢሆንም እንኳን በቅዱስ ቁርባን የጌታ እውነተኛ ሥጋና ደም የማያምኑ ከሆነ እነሱንም ለማሰናበት ዝግጁ ነበር፡፡
ረ) ሐዋርያት ለዚህ ጠንከር ያለ ጥያቄ ጠንከር ያለ መልስ በመስጠት እውነታውን አረጋግጠዋል፤- "ጌታ ሆይ ወደማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም የሕይወት ቃል አለህ፤ እኛስ አንተ ክርስቶስ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆንህ አምነናል አውቀናልም" (ዮሐ 6፡68-69)፡፡ በዚህ ዓይነት ሐዋርያት ከእርሱ ጋር ቀሩ፤ በቅዱስ ቁርባን አመኑ፤ እርሱም በመጨረሻው እራት ላይ ቅዱስ ቁርባን ሠርቶ አቆረባቸው፤ እንዲሁም እነርሱ ለሌሎች ቁርባን እንዲሠሩ እና እንዲያቆርቡ የክህነትን ስልጣን አስተባብሮ ሰጣቸው፡፡
ሰ) ሌላው ትልቁ ነጥብ የአይሁዳውያን አለማመን ነው፡፡ ኢየሱስ "እኔም ስለ ዓለም የምሰጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው" (ዮሐ 6፡41) ብሎ በተናገረ ግዜ ንግግሩን በግልፅ ቃል በቃል ተረድተውት ነበር፡፡ እርስ በእርሳቸውም "ይህ ሰው ሥጋውን ልንበላ ይሰጠን ዘንድ እንዴት ይችላል?" (ዮሐ 6፡42) በማለት ተከራከሩ፡፡ ኢየሱስ አይሁዳዊ ነው፤ የተናገረው አይሁድ በሚጠቀሙበት የአረማይክ ቋንቋ ነው፡፡ አይሁዳውያን በደንብ ገብቷቸዋል፤ ዛሬ እኛ በመጽሐፍ ተጽፎ ከምናነበው በላይ እነርሱ ኢየሱስ በገዛ ሀገራቸው ቋንቋ ሲናገር ሰምተውታል፤ ሥጋዬ ያለው በእውነት ሥጋው መሆኑን አውቀዋል፤ ስለዚህ "ይህ የሚያስጨንቅ ንግግር ነው፤ ማን ሊቀበለው ይችላል?" (ዮሐ 6፡50) አሉ፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ሌሎች ስለ ቅዱስ ቁርባን የሚያወሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን አጥና፡፡ በመላው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ ቅዱስ ቁርባን የሚተርኩ ክፍሎች ስለ እውነተኛ የክርስቶስ ሥጋ እና ደም ይመሰክራሉ፤ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዴት ባሉ ጠንካራ ቃላት ምስክርነቱን እንደሰጠ ተመልከት፤ "ስለዚህ ሳይገባው ይህንን እንጀራ የበላ፤ ወይም የጌታን ጽዋ የጠጣ ሁሉ የጌታ ሥጋ እና ደም ዕዳ አለበት፡፡... ሳይገባው የሚበላ እና የሚጠጣ የጌታ ሥጋ ስለማይለይ ለራሱ ፍርድ ይበላል፤ ፍርድ ይጠጣል" (1ቆሮ 11፡27)፡፡
ይህ የጌታ ሥጋ እና ደም የሚሰጠን በኅብስትና በወይን መልክ ነው፡፡ይህ ደግሞ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እራሱ በመጨረሻው እራት ላይ ያደረገው ነው፡፡ በመሠረቱ ኅብስት እና ወይን የሥጋ እና የደም ምሳሌ ሆነው በጥቅም ላይ የዋሉበት ሌላ አጋጣሚ የለም፡፡ እነዚህ ሁለቱ (ኅብሰት እና ወይን) የጌታ ሥጋ እና ደም የሚመሠረትባቸው የሆኑት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መለኮታዊ ሥልጣን ነው፡፡ ስለ መጨረሻው እራት በሚተርኩት በአራቱም የወንጌል ክፍሎች ውስጥ ጌታ በግልፅ "ይህ ሥጋዬ ነው፤ ይህ ደሜ ነው" እያለ በተደጋጋሚ ይናገራል (ማቴ 26፡26-28፤ማር 14፡22-24፤ሉቃ 22፡17-20፤ 1ቆሮ 11፡23-25)፡፡ በእነዚህ ክፍሎች ሁሉ የጌታችን ንግግር ምሳሌያዊ ተደርጎ የቀረበበት አንዳችም ክፍል የለም፡፡
የጥንታዊቷ ቤተ-ክርስቲያን አበው በሙሉ በቅዱስ ቁርባን ውስጥ ያለውን የኢየሱስ ክርስቶስን ሕልውና እውነተኛነት በሙሉ ልብ በአንድ የእምነት ምስክርነት ሲገልፁ ኖረዋል፡፡ የፕሮቴስታንት እንቅስቃሴ መሥራች የነበረው ማርቲን ሉተር ሳይቀር ከአበው ጋር አንድ እምነት ነበረው፡፡
ምንጭ፡ “የእምነት ቀናኢነት፣ ካቶሊካዊት እምነትን ማወቅ፣ መጠበቅ እና መንከባከብ፥ ካቶሊካዊ እምነታችንን ለሌሎች ማካፈል” በሚል አርዕስት የአዲስ አበባ ካቶሊካዊ ሰበካ የሐዋርያዊ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት በ2010 ዓ.ም ካሳተመው መጽሐፍ ከገጽ 3-5 ላይ የተወሰደ።