የሃይማኖት መሪዎች በኮፕ28 ምድራችንን ለመታደግ የጋራ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ጥሪያቸውን አቀረቡ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በኮፕ28 ስብሰባ ወቅት በተለያዩ የሀይማኖት አባቶች የተፈረመው የጋራ ሰነድ መሰረቱን ቁርጠኝነት እና ተስፋ ላይ በማድረግ ነው የወጣው ተብሏል። በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የተፈረመው ሰነዱ እ.አ.አ በ2030 የምድርን የሙቀት መጠን በ1.5 ዲግሪ የመቀነስ ግቡን ለማሳካት አስፈላጊ የሆኑትን አንድነትን፣ የጋራ ኃላፊነትን እና ወንድማማችነትን አጉልቶ ያሳያል። በተጨማሪም የሃይማኖት መሪዎቹ በአየር ንብረት ለውጥ ለተጎዱ ማህበረሰቦች ያላቸውን ድጋፍ አረጋግጠዋል።
በዚህ ስብሰባ የተለያዩ የሃገር በቀል እምነቶች እና ባህላት ተወካዮች፣ የሃይማኖት ምሁራን፣ ምሁራን፣ የሴቶች ድርጅቶች፣ ወጣቶች፣ የሲቪክ ማህበራት፣ የንግድ መሪዎች እና የአካባቢ ፖሊሲ አውጭዎች በአቡ ዳቢ ተሰባስበው በዓለማችን እየሆነ ባለው ነገር ማዘናቸውን ገልጸዋል። ተሰብሳቢዎቹም “በአየር ንብረት ለውጥ፣ በስደት፣ በግጭት እና በሃይማኖት ሰዎች መካከል ያለውን ትስስር እንዲሁም እንደ 'አካባቢያዊ ሰላም ፈጣሪዎች' በመሆን በግጭቶች ውስጥ የርህራሄ እና የሽምግልና መንገዶችን ለመቅረጽ የሚጫወቱትን ሚና ተገንዝበው እውቅና ሰጥተዋል።
ለተግባራዊነት የተደረገ ጥሪ
ሰነዱ “እኩልነት እና ፍትህን” የሚያረጋግጥ የኃይል አቅርቦት ሽግግርን ለማፋጠን አስቸኳይ ምላሾች እንዲኖሩ እና “ሰዎች ከተፈጥሮ ጋር የሚስማማ ሚዛናዊ እና የተከበረ ህይወት” እንዲኖሩ ፍትሃዊ አኗኗርን እንዲቀበሉ ይጋብዛል።
በተጨማሪም ሰነዱ የንግድ ተቋማት የሃይል ምንጮቻቸውን ከቅሪተ አካል ጋዞች ወደ ንፁህ የኃይል ምንጮች እንዲቀይሩም በማበረታታት፥ መንግስታት ለምግብ ዋስትና እና ለሥነ-ምህዳር ጥበቃ ሙሉ ዋስትና በመስጠት ዘላቂ የሆነ ግብርናን እንዲያበረታቱ ይመክራል። ይህንንም ሲያጠናክር “ማንም ሰው ወደ ኋላ መቅረት የለበትም" ሲል አጽንዖት በመስጠት “የሁሉም ሰዎች፣ በተለይም ህጻናት፣ ለአደጋ እና ግጭት ተጋላጭ የሆኑ ማህበረሰቦች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች እና ነባር ህዝቦች እንዲሁም እንስሳት እና ተፈጥሮ ፍላጎቶች እንዲሟሉ የጥረታችን ማዕከል አድርገን መስራት አለብን” ይላል ሰነዱ።
መጪው ጊዜ ጥሩ እንዲሆን ከምድራችን ጋር ተስማምቶ መኖር
የሀይማኖት መሪዎቹ የፍጆታ ዘይቤያቸውን ለመቀየር እና ዘላቂ የሆኑትን ለማስተዋወቅ ቃል ገብተዋል። በተጨማሪም የብዝሃ ህይወት ጥበቃ እና የዱር አራዊት ጥበቃ፣ የእኩልነት እና የአገሬው ተወላጆች ‘ከምድር ደህንነት ጋር የተጣበቀውን የአባቶቹን ጥበብ የመጠበቅ’ መብቶቻቸውን ለመደገፍ ድምፃቸውን ከፍ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል።
“በታሪክ ገደል አፋፍ ላይ ቆመን ባለንበት በአሁኑ ወቅት በጋራ የሚያጋጥሙንን ተግዳሮቶች ክብደት ግምት ውስጥ በማስገባት ለትውልድ የምንተወውን ትሩፋት እያስታወስን እንኖራለን” ካለ በኋላ “በ COP28 ላይ የተሰበሰቡ ሁሉም ውሳኔ ሰጪዎች ይህንን ወሳኝ ጊዜ እንዲጠቀሙ እና በአስቸኳይ እርምጃ እንዲወስዱ እንዲሁም ጥልቅ በሆነ ሀላፊነት እንዲሰሩ በአክብሮት እንጠይቃለን” ሲል ይገልፃል።
በመጨረሻም ሰነዱ “የቆሰለውን ዓለም ለመፈወስ እና የጋራ ቤታችንን ደህንነት ለመጠበቅ” ፈጣን፣ የተባበረ እና ቆራጥ እርምጃ እንዲወሰድ ይጠይቃል። በማከልም "በሂደት ለወደፊት ትውልዶች ተስፋን ማምጣት አለብን፥ በጋራ በመሆን ለሁሉም እጆቻችንን ከፍተን በመዘርጋት ወደፊት ወደ በጽናት፣ በመስማማት እና በምድር ላይ ያሉ ህይወቶች ሁሉ አብበው ወደሚኖሩበት በሚወስደው መንገድ ሰዎች ጉዞ እንዲጀምሩ እንጋብዛለን” በማለት ያጠቃልላል።