ፈልግ

ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ዕለት ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ዕለት   (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

የሕንዳዊት ሰማዕት የብፅዕት ራኒ ማርያ ፊልም ለዕይታ መቅረቡ ተገለጸ

በኅብረተሰቡ መካከል የደሄዩትን እና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙትን ለመርዳት ሕይወቷን የሰጠች ሕንዳዊት ሰማዕት የእህት ራኒ ማርያ ሕይወት እና ትሩፋት የሚያሳይ አዲስ ፊልም ለዕይታ ቀረበ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“Face of the Faceless” በሚል ርዕሥ ሕንድ ውስጥ ተሠርቶ ኅዳር 3/2016 ዓ. ም. የተለቀቀው ፊልሙ፥ የብፅዕት ራኒ ማርያ የሕይወት ታሪክ የሚገልጽ እንደሆነ ተነግሯል። ቤተ ክርስቲያን የእህት ራኒ ማርያ ሕይወት በማጤን ያወጣችውን ሠነድ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጋቢት 14/2009 ዓ. ም. ካጸደቁ በኋላ ጥቅምት 25/2015 ዓ. ም. ብፅዕናዋ መታወጁ ይታወሳል።

“Face of the Faceless” በሚል ርዕሥ የተሠራው ፊልሙ የመነኩሴዋን ሕይወት እና የሰው ልጆችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ያደረገችውን ተግባር የሚያሳይ እና ከሁለት ሰዓት በላይ የሚፈጀው ፊልሙ በሕንድ ከ16 ግዛቶች በተውጣጡ ተዋናዮች ተሳታፊነት የተሠራ እንደሆነ ታውቋል። ሃማኖታዊ ይዘት የሌለው ነገር ግን እህት ራኒ ማርያ ሕንድ ውስጥ በአስከፊ የኑሮ ሁኔታዎች ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን ለማገልገል ያደረገቻቸውን ተግባራት ከመግለጹ በተጨማሪ ዛሬም በኅብረተሰቡ በተገለሉ ሰዎች መካከል ያለውን ብዝበዛ የሚያሳይ እንደሆነ ታውቋል።

እህት ራኒ ማርያ በሕንድ ኢንዶሬ ማዲያ ፕራዳሽ በሚባል አካባቢ በማኅበረሰብ ከተገለሉ ሰዎች ጋር የኖረች ስትሆን፥ በዚህ ወቅትም ለነዋሪው ቀጣይነት ያለው መልካም ሕይወትን፣ የሥራ እና የትምህርት ዕድሎችን ለማመቻቸት ስትጥር የነበረች እና በዚህ ምክንያት የአካባቢው ነዋሪዎች፥ "ኢንዶር ኪ ራኒ" ወይም "የኢንዶር ንግሥት" በማለት በኩራት እንደሚያስታውሷት ታውቋል።

እህት ራኒ ማርያ፥ ከሃይማኖታዊ ሥነ-ምግባር ባሻገር ሁሉ አቀፍ አንድነትን በመገንዘብ ችግረኛ ሴቶችን በመርዳት እና ሁሉንም በፈገግታ የምታስተናግድ ገዳማዊት እንደነበረች በሕይወት ታሪኳ ላይ ተገልጿል። በሰማዕትነት የሞተችው እህት ራኒ ማርያ፥ ታሪኳ በዚህ ብቻ ሳያበቃ ቤተሰቦቿም ገዳዩዋን ከፈጸመው አሰቃቂ ወንጀል በኋላም ይቅር ብለው እንደ ወንድማቸው እንደተቀበሉት እና ይቅርታቸውም በሰዎች መካከል ያለውን ልዩነት በመቀበል ሥር ነቀል የይቅርታ መልዕክት ለማስተላለፍ የሚፈልግ እንደሆነ ታውቋል።

ፊልሙ በመጀመሪያ የሕንድ ብሔራዊ ቋንቋ በሆነው ሂንዲ የተሠራ ሲሆን፥ ከዚያም በማላያላም እና እንዲሁም አሁን በፈረንሳይኛ እና በስፓኒሽ ቋንቋዎች መዘጋጀቱን የፊልሙ ዳይሬክተር ገልጸዋል።  ከሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ የፊልም ማኅበረሰብ ሰፊ ዕውቅናዎችን እና ሽልማቶችን ያገኘው ፊልሙ፥ በአጭር ጊዜ ውስጥ ቅጂዎች ከፍተኛ ቁጥር ታትሞ ለተመልካች መሰራጨቱ ታውቋል።

አንድ የፊልም ሃያሲው እንደገለጸው፥ “ብዙውን ጊዜ ጫጫታና ትርምስ በበዛበት ዓለም ውስጥ የእህት ራኒ ማርያ የማይናወጥ መንፈሳዊ ተጋድሎ እና ጉዞ፥ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ መሥዋዕትነት የሚከፈልበት እና የማያወላውል የእምነት ጎዳና የመረጡ ሰዎች የሚታወሱበት ያልተነገሩ ታሪኮችን የሚገልጽ ነው” ብለዋል።

ከር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ጋር መገናኘት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሳምንታዊ ጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ባቀረበበት ዕለት ኅዳር 23/2016 ዓ. ም. የፊልሙ ዳይሬክተር ሻይሰን ፒ. ኦሴፍ እና ፕሮዲዩሰር ሳንድራ ዲሱዛ ራና ከቅዱስነታቸው ጋር ተገናኝተው እንደ ነበር ይታወሳል።

የፊልም ባለሙያዎቹ፥ “Face of the Faceless” የተሰኘውን አዲሱን ፊልም በማስመልከት ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አጭር ገለጻ ካደረጉ በኋላ እንዲመለከቱትም ጋብዘው ለፊልሙ ስኬታማነት ቡራኬያቸውን ጠይቀዋል።

 

07 December 2023, 13:12