ፈልግ

2019.12.27 Dio, uomo, creazione

ጌታሆይ ሰውን ታስበው ዘንድ ምንድነው?

ዘማሪው ዳዊት እግዚአብሔር ለሰው ፍጥረት ያደረገው ገርሞት ጌታ ሆይ “በዐሳብህ ስፍራ ትሰጠው ዘንድ ሰው ምንድን ነው? ትጠነቀቅለትም ዘንድ የሰው ልጅ ምንድን ነው? ከመላእክት በጥቂት አሳነስኸው፤ የክብርንና የሞገስን ዘውድ አቀዳጀኸው። በእጆችህ ሥራ ላይ ሾምኸውሁሉንም ከእግሩ በታች አስገዛህለት፣ በጎችንና ላሞችን ሁሉ፣ የዱር አራዊትንም፣ የሰማይ ወፎችንና የባሕር ዓሦችን፣ በባሕር ውስጥ የሚርመሰመሱትንም ሁሉ አስገዛህለት” (መዝሙር 8፡4/7) ይላል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

እግዚአብሔር ለእኛ ብዙ ትላልቅና የሚያስደንቁ ነገሮችን አደረገልን፡፡ ከሁሉም በኋላ ተፈጥረን ሳለ ከመላእክት በስተቀር ከሌሎች ፍጥረቶች ሁሉ በላይ ከፍ አደረገን፣ ከግዙፍ ፍጥረታት ሁሉ በላይ አድረጐናል፡፡

ሌሎች ፍጥረቶች በቃሉ “ይሁን» እያለ ፈጠራቸው፣ እኛን ግን በእጆቹ ሠርቶ ከእስትንፋሱ ሕይወት ሰጥቶ በአምሳሉ ፈጠረን፡፡ ከዚህ በኋላ ደስታና መልካም ነገር ሁሉ ባለበት ሥፍራ በገነት አስቀመጠን፡፡ እኛ ግን ክብራችንን ጣልን፣ የአምላክ ወዳጅነትና መልካም ዕድላችንን አጠፋን፡፡ ከአምላክ ጋር ተጣላንና መከራ ላይ ወደቅን፡፡ እግዚአብሔር በመጀመሪያ በኃጢአታችን ቀጣን፣ ሰጥቶን የነበረውን ሥጋዊና መንፈሳዊ ሀበት ወስዶ ከገነት አውጥቶ በመከራና በሐዘን ላይ ጣለን፣ በሚያስከፍው አኗኗራችን ራርቶልን ምሕረቱንና ፍቅሩን በማሳየት መድኃኒት የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ላከልን፡፡

እግዚአብሔር እኛን እንደዚህ ሲያፈቅረን በልዩ ሁኔታ ሲያስታውሰን እኛ ግን ብዙ ጊዜ ጸጋዎቹን፣ ፍቅሩን፣ ምሕረቱን ረስተን እናሳዝነዋለን፡፡ ስላደረገልን መልካም ነገር ወሮታ ሳንመልስለት ዝም እንላለን፡፡ ሁሉም ፍጡሮች ሰማያውያንና ምድራውያን ቀጥ ብለው ይታዘዙለታል፡፡ በበኩላቸው ያከብሩታል፣ ሁሉም ያስደስቱታል፡፡ እኛ ገን ከእርሱ ትልቅ ከብርና ፍቅር ተቀብለን ሳለ ማድረግ የሚገባነን ምሰጋናና የአምልኮ ሥራ ከመፈጸም ቸል እንላለን፡፡ ትዕዛዞቹን እናፈርሳለን ፈቃዱን መፈጸም እምቢ እንላለን፣ ከፍጥረቶች ሁሉ እግዚአብሔርን የምንበድል እኛ ነን፡፡

እኛ ምን ስለሆንን ነው አምላክ ያለመጠን የሚወደንና የሚያከብረን? እንደማንም ዓይነት ፍጥረታት ነን። አፈር ነን ምን አድርገንለት ነው ሁልጊዜ የሚያስታውሰን? ተጨንቆ የሚጠብቀን? የምንወደውና የምናፈቅረውን እንወቅ፡፡ ዘወትር የሚያስታዋሰንና የሚያስብልንን አምላክ እናሰታውሰው እናመስግነው፡፡ ጥሩ ላደረገልን ጥሩ ማድረግ የሚያስታውሰንን ማስታወስ፣የሚያፈቅረንን ማፍቀር የተገባ ነው፡፡ ቸል ባይነትና ክፋትን እንተው፡ እግዚአብሔርን እናመስግነው፡፡

 

07 December 2023, 11:36