የአባ ጁሴፔ ፑሊዬዚ የሰማዕትነት ደም ፍሬ የተገኘበት እንደሆነ ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
አባ ጁሴፔ ፑሊዬዚ በደቡብ ጣሊያን ፓሌርሞ ግዛት በማፊያዎች እጅ የተገደሉት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ መስከረም 15/1993 ዓ. ም. በበጋው ወራት መገባደጃ ላይ እንደ ነበር ሲታወስ፥ ዕለቱ የ56 ዓመታቸው የልደት ቀን እንደ ነበር ታውቋል። አባ ጁሴፔ በዕለቱ ልደታቸውን ከማክበር ይልቅ በሚኖሩበት ብራንካቾ አውራጃ ውስጥ ዘራፊዎች በበዙበት አካባቢ ትምህርት ቤት ለመክፈት የሚያስችል ፍቃድ ለማግኘት ማዘጋጃ ቤት ውለው ይመለሱ እንደ ነበር ይታወሳል።
አባ ጁሴፔ በዚያ ምሽት ሁለት የማፊያ አለቆች ውጭ ቆመው እንደሚጠብቋቸው ባወቁ ጊዜ፥ በጥይት ተመትተው ከመገደላቸው በፊት የገዳዮቻቸውን መልክ ለይተው ለማየት በቂ ጊዜ ነበራቸው። የአባ ጁሴፔ ሞት ከፍተኛ መልዕክት ያለው እና ሥራቸውም ቀጣይነት ያለው እንደ ሆነ ታውቋል። ቤተ ክርስቲያን የአባ ጁሴፔን ብጽዕና እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በግንቦት 25/2013 ዓ. ም. ይፋ ማድረጓ የሚታወስ ሲሆን፥ የሕልፈተ ሕይወታቸው ሰላሳኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በሮም የሚገኝ “ሉምሳ” የተሰኘ ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ እና በብፁዕ ካርዲናል ሳልቫቶሬ ደ ጆርጂ ስም የተቋቋመ የቫቲካን ፋውንዴሽን ተባብረው በዩኒቨርሲቲው ባዘጋጁት በዓል "የደም ድምፅ" በሚል ርዕሥ ጉባኤ ተካሂዷል።
ከህልፈተ ሕይወታቸው ወዲህ በርካታ የሰላም ሥራዎች ተከናውነዋል
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለዩኒቨርሲቲው አስተዳዳሪ ለአቶ ፍራንስኮስ ቦኒኒ እና ከጉባኤው ተካፋዮች መካከል አንዱ ለነበሩት፥ በቅድስት መንበር የቅድስና ጉዳዮች ጳጳሳዊ ምክር ቤት አስተባባሪ ለሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ማርቼሎ ሰመራሮ በላኩት መልዕክት አማካይነት በጉባኤው ለመገኘት የነበራቸውን ፍላጎት ገልጸዋል።
በጉባኤው ላይ በቀድሞው የፓሌርሞ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ሳልቫቶሬ ደ ጆርጂ የተጻፈ “የብፁዕ ጁሴፔ ፑሊዬዚ የደም ድምጽ” በሚል ርዕሥ የተጻፈ መጽሐፍ እና የአባ ጁሴፔ ህልፈተ ሕይወት በማስታወስ ብፁዕ ካርዲናል ሳልቫቶሬ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ ያሰሟቸው የአምስት ዓመታት ስብከቶችን ያካተተ መጽሐፍ ለንባብ ቀርቧል። “አባ ጁሴፔ ከተገደሉ ከአምስት ዓመታት በኋላ ለብጽዕና የበቁበትን እና ለግድያ ያበቃቸውን ምክንያት ይፋ አድርጌአለሁ” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ሳልቫቶሬ ደ ጆርጂ፥ የአባ ጁሴፔ ሰማዕትነትን እና በካህናት ሁሉ ፊት በጎ አርአያ ሆነው መገኘታቸውን በየዓመቱ በሚያቀርቡት የመታሰቢያ መስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ማስታወሳቸውን ገልጸዋል።
“የአባ ጁሴፔ ብጽዕና አጠቃላይ ሂደትን ለመከታተል ከመቻሌ በተጨማሪ ብጽዕናቸው የታወጀበት ሰኔ 28 (እ.አ.አ) የክህነት ማዕረግ ከተሰጠኝ ቀን ጋር የሚገጣጠመ እና የብጽዕናቸውን አዋጅ ከመፈረም ጋር ተዳምሮ ታላቅ የጸጋ ምስጢር ነበር” በማለት ገልጸዋል። የብጽዕናቸው ዜና የተሰማበት እና ወደ ፓሌርሞ የመጡበት ቀን ግንቦት 2/2013 (እ.አ.አ) እንደ ነበር ያስታወሱት ብፁዕ ካርዲናል ሳልቫቶሬ ደ ጆርጂ፥ ከሰማይ ሆኖ ለሁላችን የሚጸልይ ብፁዕ አባ ጁሴፔ ዘወትር የሚረዳቸው መሆኑን በማመን ምስጋናቸውንም አቅርበዋል።
ቀጣይነታ ያለው የብጹዕ ጁሴፔ ሥራ
የብጹዕ ጁሴፔ ፑሊዬዚ ቅዱስ አጽም በፓሌርሞ ካቴድራል ውስጥ በክብር እንደተቀመጠ እና በርካታ ምዕመናን ወደ ሥፍራው መንፈሳዊ ንግደት በማድረግ በመካነ መቃብሩ ፊት ጸሎታቸውን እንደሚያቀርቡ የፓሌርሞ ካቴድራል መሪ ካኅን አባ ፊሊፖ ሳሩሎ ገልጸው፥ አክለውም ወደ ካቴድራሉ የሚመጡ ብዙ ቱሪስቶች ለአጭር ጊዜ ያህል መካነ መቃብሩን ቢጎበኙት መልካም እንደሚሆን አስረድተዋል። የብጹዕ ጁሴፔ ንዋያተ ቅድሳት በካቴድራሉ ውስጥ በክብር ተቀምጠው እንደሚገኙ የገለጹት አባ ፊሊፖ ሳሩሎ፥ ከአሥር ዓመት በፊት አጽማቸው ወደ ካቴድራሉ ሲዛወር በቦታው እንደ ነበሩ እና ሰውነታቸው ሳይበላሽ ማግኘታቸው ልብ የሚነካ እንደ ነበር አስታውሰዋል። “አባ ጁሴፔን የገደለ ማንም አላሸነፈም” ያሉት አባ ፊሊፖ፥ ምክንያቱም የአባ ጁሴፔ ሥራዎች በሙሉ ዛሬም እያበቡ እና የበለጠ እያደጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።