የመጽሐፍ ቅዱስ መዋቅራዊ ቀኖና (ርዕስ)
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን
የትኞቹ መጻሕፍት መለኮታዊ የእውነት ቃል ይዘዋል ብለን መመርመር አለብን፤ አለበለዚያ ግን ከእግዚአብሔር ቃል ይልቅ የሰዎች ቃል ቦታ ይይዛል፡፡ በመሆኑም የትኞቹ መጻሕፍት እውነተኛውን መለኮታዊ ቃል እንደያዙ የሚጠቁሙ የመጻሕፍት ዝርዝር መዋቅር (ቀኖና) ያስፈልገናል፡፡ ቀኖና ማለት የመለኪያ መስፈርት ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የመፅሐፍ ቅዱስ ቀኖናዊ ይዘት ቤተክርስትያን ከጥንት ጀምራ የምትቀበላቸውን መለኮታዊ እውነት የሚገልጡትን መጻሕፍት ያመለክታል፡፡እነዚህ መጻሕፍት ተሰብስበው በአንድ ጥቅል "መጽሐፍ ቅዱስ" ተብለው ይጠራሉ፡፡
ብሉይ ኪዳን
የካቶሊክ መጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እና የፕሮቴስታንት መጽሐፍ ቅዱስ የብሉይ ኪዳን ክፍሎቻቸው በቁጥር የሚለያዩት በምን ምክንያት ነው?
በፍልስጤም ዙርያ ይኖሩ የነበሩ የዕብራይስጥ ቋንቋ ተናጋሪ አይሁዳውያን በዕብራይስጥ ቋንቋ የተዘጋጁ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን ይጠቀሙ ነበር፡፡ወንጌላውያን ክርስቲያኖች የሚጠቀሙበት የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ መሠረቱ ይህ የዕብራይስጡ የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ነው፡፡ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የምትጠቀምበት የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ደግሞ በግሪክ ቋንቋ የተዘጋጀውን እና በሜዲትራኒያንና በፍልስጤም ዙርያ በሚኖሩት አይሁድ ዘንድ ጥቅም ላይ የዋለውን የግሪኩን የመጻሕፍት ዝርዝር (ቀኖና) ነው፡፡
ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ250-125 ዓ.ዓ. ድረስ ከሰባ እስከ ሰባ ሁለት የሚደርሱ አይሁዳውያን ሊቃውንት በዕብራይስጥ ቋንቋ የተፃፉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በሙሉ ወደ ግሪክ ቋንቋ ተርጉመዋል፡፡ ታሪክ እንደሚያስረዳው እነዚህ ሊቃውንት ከአሥራ ሁለቱ የእሥራኤል ነገዶች መካከል ስድስት ስድስት ሆነው ከእያንዳንዱ ነገድ የተውጣጡ ነበሩ፡፡ እንግዲህ እነዚህ ሊቃውንት መጻሕፍቱን ተርጉመው ሲጨርሱ በግብፅ ሀገር በአሌክሳንድሪያ ከተማ የመጀመሪያው ዋና ቅጂ ''Septuagint'' ወይም ደግሞ "ሰባ" ቁጥር ተብሎ ተጠራ፤ ይህም ከተርጓሚዎቹ ቁጥር የተወሰደ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ሰባ ሁለቱን ለማመልከት በሀገራችንም "ሰባ ወክልኤቱ" እየተባለ ይጠራል፡፡
በኢየሱስ ክርስቶስ ዘመን በመላው የሜዲትራኒያን ዓለም የግሪክ ቋንቋ ዋነኛ የሥራ ቋንቋ ስለነበረ የግሪኩ የብሉይ ኪዳን ቅጂ በስፋት በጥቅም ላይ እንዲውል እና ተቀባይነት እንዲያገኝ አድርጎታል፡፡ በዚያን ጊዜ የዕብራይስጥ ቋንቋ በተናጋሪ ዕጦት እየጠፋ የነበረ ቋንቋ በመሆኑ (በፍልስጤም ይኖሩ የነበሩት አይሁድ የአረማይክ ቋንቋ በስፋት ይጠቀሙ ነበር) ኢየሱስና የአዲስ ኪዳን ፀሐፊዎች ከግሪኩ ትርጉም (Septuagint) እየጠቀሱ መጠቀማቸው አያስገርምም፡፡
በአዲስ ኪዳን ውስጥ ተጠቅሰው ከምናገኛቸው የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ሐሳቦች መካከል ከፍተኛውን ድርሻ የሚወሰዱት ከግሪኩ ቅጂ የተጠቀሱት ናቸው፡፡ (Archer) እና (Chirichigno) የሚባሉ የፕሮቴስታንት ደራሲዎች ራሳቸው አዲስ ኪዳን በ340 የተለያዩ ሥፍራዎች ላይ የግሪኩን ቅጂ ሲጠቅስ ለ33 ጊዜ ያህል ብቻ ከዕብራይስጡ ቅጂ መጥቀሱን ይመሰክራሉ፡፡ ይህንን ዋቢ በማድረግ የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች ከመቶ ዘጠና እጅ ያህል ከግሪኩ ቅጂ (Septuagint) መጥቀሳቸውን ማየት ይቻላል፤ መላው የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት በግሪክ ቋንቋ መሆናቸውን ልብ በል፡፡
የግሪኩ ቅጂ የያዘው 46 የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን ሲሆን የዕብራይስጡ ቅጂ ደግሞ 39 የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን ብቻ ይዟል፤ ይህ ከምን የመጣ ነው?
በሶስተኛው ክፍለ ዘመን የአይሁድ ሊቃውንት በዕብራይስጡ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ላይ መከራከር ጀመሩ፡፡ከዚህም በመነሳት በእነዚህ መምህራን የሚመራው የአይሁድ እምነት ሰባት መጻሕፍትን ከዕብራይስጡ መጽሐፍ ውጪ እንዲሆኑ ወሰነ፡፡ እነዚህ መጻሕፍት መጽሐፈ ጥበብ፣ መጽሐፈ ሲራክ፣ መጽሐፈ ዮዲት፣ መጽሐፈ ባሮክ፣ መጽሐፈ ጦቢት፣1ኛ እና 2ኛ መቃቢያ ሲሆኑ ከትንቢተ ዳንኤል እና ከመጽሐፈ አስቴር መካከል የተወሰኑትን ክፍሎች ከዕብራይስጡ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ዝርዝር ውጪ እንዲሆኑ አድርገዋል፡፡ የዚህም ዋነኛው ምክንያት በግሪኩ ቅጂ ውስጥ የተካተቱትን የእነዚህን መጻሕፍት ቅጂ በዕብራይስጥ ቋንቋ በተፃፈው ቅጂ ውስጥ ባለማግኘታቸው የተነሳ ነው፡፡ እነዚህ መጻሕፍት በግሪኩ ቅጂ ውስጥ ቢኖሩም እንኳን በዕብራይስጥ ቋንቋ ተጽፈው ባለመገኘታቸው ከዕብራይስጡ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ዝርዝር ውጪ ተደርገዋል፡፡
ክርስቲያኖች ከመጀመሪያው ይጠቀሙ የነበረው የግሪኩን ቅጂ (Septuagint) ስለነበር የአይሁዳውያንን ውሳኔ ወደ ጎን በመተው የግሪኩን ቅጂ መጠቀማቸውን ቀጥለዋል፡፡ ቤተክርስቲያን ብሉይ ኪዳንን በሚመለከት በሂፖ ጉባኤ 393 ዓ.ም እና በካርቴጁ ጉባኤ በ397 ዓ.ም በግሪኩ ቅጂ ውስጥ የተካተቱት 46ቱ መጻሕፍት ትክክለኛው የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ዝርዝሮች መሆናቸውን አውጃለች፡፡
ከዚህ ውሳኔ በኋላ ለተከታታይ 16 ክፍለ ዘመናት ክርስቲያኖች ሁሉ በግሪኩ ቅጂ ትክክለኛነት ላይ አንድ እምነት ነበራቸው፡፡ በዕብራይስጡ ቅጂ ያልተካተቱት ሰባቱ መጻሕፍትም በቤተክርስቲያን አበው ዘንድ ‹‹መጽሐፍ ቅዱስ›› ተብለው ተጠርተዋል፡፡
በ1529 ዓ.ም. ማርቲን ሉተር በዕብራይስጥ ቋንቋ የተዘጋጀውን እና 39 መጻሕፍት የያዘውን የአይሁድ ብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ለመቀበል እንቅስቃሴ ጀመረ፡፡ የሉተር ሐሳብ ልክ እንደ አይሁዳውያን ሁሉ ሰባቱ መጻሕፍት የዕብራይስጥ ቅጂ የላቸውም የሚል ነበር፡፡ ነገር ግን በሙት ባህር (Dead Sea) አካባቢ ኩምራን (Qumran) በተባለ ቦታ በቁፋሮ ከተገኙት ጥንታዊ የመጻሕፍት ቅዱስ ክፍሎች ውስጥ ከሰባቱ መጻሕፍት የተወሰኑት የዕብራይስጥ ቅጂ መገኘቱ የሉተርን ሐሳብ ተቀባይነት አሳጣው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሉተር ሰባቱን በክርስቲያን የግሪክ ቅጂ ውስጥ የሚገኙትን መጻሕፍት ላለመቀበል የፈለገው እነዚህ መጻሕፍት ሉተር ከሚፈልገው በተቃራኒው ያለውን እውነት ስለሚያስተምሩ ነው፡፡ ለምሳሌ 2ኛመቃ 12፡42-45 ያለው ሐሳብ ለሙታን ስለመጸለይ ክርስቲያናዊ ግዴታ ያስተምራል፡፡ እዚህ ላይ እውነተኛው ጥያቄ ብቅ ይላል፡- የትኛውን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ትጠቀማለህ? ኢየሱስ የጠቀሰውን፣ የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች እና የጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያን አበው የተጠቀሙበትን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ወይስ ኢየሱስን የማይቀበሉ እና ክርስትናን የሚያሳድዱ አይሁዳውያን የተጠቀሙትን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት?
ምንጭ፡ “የእምነት ቀናኢነት፣ ካቶሊካዊት እምነትን ማወቅ፣ መጠበቅ እና መንከባከብ፥ ካቶሊካዊ እምነታችንን ለሌሎች ማካፈል” በሚል አርዕስት የአዲስ አበባ ካቶሊካዊ ሰበካ የሐዋርያዊ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት በ2010 ዓ.ም ካሳተመው መጽሐፍ ከገጽ 11-13 ላይ የተወሰደ።