የካሜሩን ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት በሰሜኑ የአገሪቱ ክልሎች የሚካሄደውን ሁከት ተቃወሙ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የካሜሩን ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት በናይጄሪያ አዋሳኝ ሰሜናዊ ክልል እና ግጭት ውስጥ በሚገኙ የአንግሊፎን ክልሎች ውስጥ እየተካሄደ ባለው ሁከት ሰለባ ለሆኑት ተጎጂዎች ያላቸውን ቅርበት በጸሎት ገልጸው፥ ተገንጣዮች እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ 2017 ዓ. ም. ጀምሮ በፍራንኮ ፎን ቁጥጥር ስር ያለውን ማዕከላዊ መንግሥት ሲዋጉ መቆየታቸው ይታወቃል።
የካሜሩን ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ያለፈው ቅዳሜ ጥር 4/2016 ዓ. ም. በማሩዋ-ሞኮሎ ሀገረ ስብከት በተካሄደው ዓመታዊ ስብሰባ መዝጊያ ላይ ባወጡት መግለጫ፣ ከጎረቤት ናይጄሪያ የመጡ ቦኮ የሃራም እስላማዊ አሸባሪዎች የፈጸሙትን አሰቃቂ ድርጊቶችን ተቃውመዋል።
የቦኮ ሃራም የሰሜኑ ጥቃት
የቦኮ ሃራም የአሸባሪ ቡድን ጥቃት በናይጄሪያ ቦርኖ ግዛት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ2009 ዓ. ም. ጀምሮ ወደ ጎረቤት ሀገራት ካሜሩን፣ ቻድ እና ኒጀርን ጨምሮ በድንበር አካባቢዎች ሽብር በመዝራት የቆየ ሲሆን፥ ጥቃቱ በሰሜን ካሜሩን ከ320,000 በላይ ሰዎች አካባቢውን ለቀው እንዲሰደዱ ማድረጉ ተነግሯል።የካሜሩን ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት በሰሜን-ምዕራብ እና በደቡብ-ምዕራብ ክልሎች የአንግሊፎን ተገንጣዮች በፈጸሙት ግፍ የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸዋል።
በሰሜን-ምዕራብ እና በደቡብ-ምዕራብ ክልሎች ውስጥ ያለው የአንግሊፎን ቀውስ
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2016 ዓ. ም. በካሜሩን የእንግሊዘኛ ተናጋሪ ማኅበረሰብ መገለል በመቃወም፥ ሀገሪቱን ከነጻነት ጀምሮ በስልሳዎቹ መጀመሪያ ላይ ሲመሩ በነበሩት የፍራንኮፎን ልሂቃን ማዕከላዊ መንግሥትን የሚቃወሙ ሰልፎችን ባካሄደበት ወቅት የአንግሊፎን ቀውስ መፈጠሩ ይታወሳል።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2017 ዓ. ም. ውጥረቱ በፍጥነት ወደ መገንጠል የፖለቲካ ግጭት ተለወጦ፥ ተገንጣዮች በየትኛውም ሀገር እውቅና ያልተሰጣት “አምባዞንያ” የምትባል ነፃ ሀገር ማቋቋማቸው ይታወሳል። በነዚህ አካባቢዎች ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸው የተለመደ ሲሆን፥ በሕዝብ ሕይወት ላይ የሚፈጸሙ እገታዎች በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍሎች በመጨመሩ ወደ እውነተኛ ንግድ መለወጡ ታውቋል።
ለሰላም የመሥራት አስፈላጊነት
የካሜሩን ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት በስብሰባቸው ማጠቃለያ ላይ “በተልዕኮ ላይ ያለች ሲኖዶሳዊ ቤተ ክርስቲያን” በሚለው መሪ ሃሳብ ላይ በማትኮር ባወጡት መግለጫ፥ በአገሪቱ ውስጥ ያሉትን ሁሉንም ዓይነት ብጥብጦች በመቃወም፥ መከራ ውስጥ የሚገኙትን በሙሉ በማያቋርጥ አባታዊ ጸሎት እንደሚያስታውሷቸው ገልጸዋል። ብጹዓን ጳጳሳቱ በተጨማሪም በሕዝቡ መካከል እያደገ ያለው ድኅነት እንዳሰጋቸው ገልጸው፥ የበለጠ ፍትህ፣ አንድነት፣ ጠንክሮ መሥራት እና በእግዚአብሔር ላይ ጽኑ እምነት እንዲኖር በማለት ተማጽነዋል።
ባለፈው ሳምንት በተጀመረው ስብሰባ መክፈቻ ላይ የካሜሩን ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝደንት እና የባሜንዳ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ አንድሪው ፉአንያ ንኪያ፣ ለካቶሊክ የዜና ወኪል እንገለጹት፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2024 ዓ. ም. ሁሉም ዜጎች እውነተኛ ሰላም በመላ አገሪቱ እውን እንዲሆን ይተባበሩ ዘንድ አሳስበው፥ የደህንነት ተግዳሮቶች እየጨመሩ በሄዱበት ወቅትም ተስፋ እንዳይቆርጡ አደራ ብለዋል።
ሊቀ ጳጳስ አቡነ አንድሪው በመጨረሻም፥ “ሁሉም የካሜሩን ሕዝቦች ሰላምን በመውደድ ለሰላም እንዲሠሩ እና ካሜሩን ሰላማዊ መሆኗን ለማረጋገጥ ልባቸውን ለፍቅር ክፍት እንዲያደርጉ እናስባለን" ብለዋል።