የካልካታ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቶማስ ዲ ሶዛ የኢዮቤልዩ ዓመት ቅዱስ በር መመረቃቸው ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በቅዱስ የመቁጠሪያ ካቴድራል ውስጥ በሊቀ ጳጳስ አቡነ ቶማስ ዲ ሶዛ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ ታኅሣሥ 24/2023 ዓ. ም. በመሩት የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ በሕንድ የምዕራብ ቤንጋል ግዛት ከፍተኛ ሚኒስትር አቶ ማማታ ባኔርጄ ተገኝተዋል።
3.7 ሜትር ቁመት እና 2.5 ሜትር ስፋት ያለው የካቴድራሉ ዋና መግቢያ በር አሁን በነሐስ የተሠራ ሲሆን፥ በውስጡ መልአኩ ገብርኤል ቅድስት ድንግል ማርያም በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ኢየሱስን እንደምትፀንስ ያበሰረበት የሥዕል ሥራ ያለበት እንደሆነ ተመልክቷል። በሩ ካልካታ ውስጥ በሚገኝ ወጣት ተማሪ ፓርትሃብራታ ጋንጉሊ የተቀረጸ ሲሆን፥ የወጣቱ የጥበብ ሥራ መንፈሳዊነትን የተከተለ እና የቤተ ክርስቲያኗን ሕግ እና ትውፊት ባከበረ የተቀደሰ የጥበብ ሥራ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ተመልክቷል።
“በዓለማችን ውስጥ ግጭቶች እና ዓመጾች በበዙበት በዚህ ወቅት የተሠራው የኢዮቤልዩ ዓመት ቅዱስ በር አስፈላጊነት የበለጠ ጥልቅ ትርጉም እንደሚኖረው እና በሁከት መካከልም የተስፋ፣ የእርቅ፣ የምሕረት እና የሰላም ምልክት ሆኖ እንደሚቆም የካቴድራሉ ሃላፊ አባ ፍራንክሊን ሜኔዝዝ አስገንዝበዋል።
የኢዮቤልዩ ዓመት በዓል አጀማመር
በዘሌዋውያን መጽሐፍ ውስጥ እንደተገለጸው ሁሉ፥ የኢዮቤልዩ ዓመት ወይም የቅዱስ ዓመት ሥርዓት አይሁዳዊ ወግ ያለው ሲሆን፥ እንደ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አገላለጽ በየ 50 ዓመቱ የሚከበረው ይህ የኢዮቤልዩ ቅዱስ ዓመት፥ ምድሪቱ የእህል ፍሬዋን እንድታሳድግ፥ የሰዎች እኩልነት እንዲታደስ እና በሃብታ እና በድሃ መካከል ያለውን ልዩነት በማስወገድ አገልጋዮች ነጻ እንዲያወጡ የሚያዝ እንደሆነ ተጠቅሷል።
የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቦኒፌስ ስምንተኛ፥ የኢዮቤልዩ ቅዱስ ዓመት እንዲከበር ሲያዙ በምዕራቡ ዓለም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ1300 ዓ. ም. ጀምሮ ሲከበር የቆየው ክርስትና ባሕል በየ25 እና 50 ዓመት እንደሚከበር እና አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜም ልዩ የኢዮቤልዩ ዓመት እንደሚከበር ይታወቃል።
የመጨረሻው የኢዮቤልዩ ቅዱስ ዓመት የተከበረው በቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የጵጵስና ዓመት እንደ ጎርጎሮሳውያን በ2000 ዓ. ም እንደ ነበር ይታወሳል። እንደ ጎርጎሮስውያኑ በ2015 ዓ. ም. ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከታኅሳስ 8/2015 እስከ ህዳር 20/2016 ዓ. ም. ድረስ የሚከበር ልዩ የምሕረት ዓመት አውጀው እንደ ነበር ይታወሳል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ከኢዮቤልዩ በዓል አስቀድሞ ያለው የጎርጎሮሳውያኑ 2024 ዓ. ም. ታላቅ የጸሎት ዓመት እንዲሆን እጅጉን በመመኘት፥ የኢዮቤልዩ ዓመት መሪ ቃልም "የተስፋ ነጋዲያን" እንዲሆን በመምርጥ ዓለማችን በሁከት እና በብጥብጥ ውስጥ የምታልፍበት ዓመት እንደሆነ መናገራቸው ይታወሳል።
የኢዮቤልዩ ቅዱስ ዓመት መባች ለቤተ ክርስቲያን ታላቅ መንፈሳዊነትን የሚያጎናጽፍ፥ መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ ፋይዳ ያለው እንደሆነ ሲታወቅ፥ በመላው ዓለም የቤተ ክርስቲያናት ቅዱስ በሮች የሚከፈቱት የጽንሰታ ማርያም ዓመታዊ በዓል በሚከበርበት፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በታኅሣሥ 8 እንደሆነ ይታወቃል።