የሊባኖስ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በጦርነት የተፈናቀሉትን በመደገፍ ላይ እንደምትገኝ ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የሊባኖስ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት ሲያሳስባት መቆየቱ ይታወሳል። በደቡባዊ ሊባኖስ እየጨመረ የመጣው የቦምብ ጥቃት እና ተኩስ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ዋና ከተማዋ ቤይሩት እንዲሰደዱ ማስገደዱ ተነግሯል።
በሊባኖስ የሚገኝ ካሪታስ የተሰኘ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የዕርዳታ ድርጅት ፕሬዝደንት አባ ሚሼል አቡድ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ “ሁኔታው ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ማኅበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ በምትገኝ ሊባኖስ ላይ አስፈሪ መዘዝ ማስከተሉን ይቀጥላል” ብለዋል።
የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ሕይወታቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን ለማዳን ጥረት ላይ የሚገኙት በሙሉ ማንኛውም ዓይነት ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው አባ ሚሼግ ገልጸዋል። ተፈናቃዮቹ ቤታቸውን፣ ሥራቸውን እና ዘመዶቻቸውን ጥለው ሕይወታቸውን ለማትርፍ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል። "ከየሀገረ ስብከቱ ብጹዓን ጳጳሳት እና ከሌሎች የሃይማኖት አባቶች የሚቀርበውን ድጋፍ በማሰባሰብ ተፈናቃዮቹ የሚያርፉባቸውን የእንግዳ መቀበያ ማዕከላትን በማዘጋጀት ሁሉም መሠረታዊ ፍላጎቶች እንዲደርሳቸው ማድርጋቸውን አባ ሚሼል ተናግረዋል።
ቤተ ክርስቲያኗ ቁሳቁስ ዕርዳታን ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ ድጋፍንም እንደምትሰጥ፥ በቦምብ ጥቃት የተጎዱትን ነፍሳት በማጽናናት የጸሎት እና የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ ሥርዓቶችን እያዘጋጀን እንገኛለን” ሲሉ አባ ሚሼል ገልጸዋል።
የፓትርያርክ አል-ራሂ የደቡባዊ ሊባኖስ ጉብኝት
ማሮናዊው ፓትርያርክ ብፁዕ ካርዲናል ቤቻራ ቡትሮስ አል ራሂ በሊባኖስ ደቡባዊ ክፍል የተጎዱ አካባቢዎችን በመጎብኘት ቤተ ክርስቲያን ለተጎጂዎች ያላትን ቅርበት ገልጸዋል። ብፁዕ ካርዲናል ቤቻራ ቡትሮስ አል ራሂ በደቡቡ የአገሪቱ ክፍል የሚገኙ መንደሮችን ለመጎብኘት እና የአካባቢው ነዋሪዎች ብቻቸውን እንዳልሆኑ እና ቤተ ክርስቲያን ከጎናቸው እንዳለች ለመንገር በቅርቡ ወደ ሥፍራው መጓዛቸውን የሊባኖስ ካሪታስ ፕሬዝደንት አባ ሚሼል አቡድ ገልጸዋል።
ብዙዎቹ የአካባቢው ነዋሪዎች ወደ ሰላማዊው ቦታዎች መሄድ የማይችሉ፥ በኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት በድህነት ሕይወት ውስጥ የሚኖሩ መሆናቸውን አባ ሚሼል አብራርተዋል። ሊባኖሳውያን ጦርነትን እንደማይፈልጉ፥ ጦርነትን በመቃወም በቅርቡ ድምጻቸውን ማሰማታቸውን አባ ሚሼል አስታውሰው፥ ግጭት ህመምን፣ ጭንቀትን እና ፍርሃትን ብቻ እንደሚያመነጭ በመግለጽ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ ቋጭተዋል።