ፈልግ

አባ ኢብራሂም ፋልታስ አባ ኢብራሂም ፋልታስ 

አባ ፋልታስ፡ ‘ልክ እንደ መጥምቁ ዮሐንስ ወደ ሰላም የሚወስደውን መንገድ መጠቆም አለብን’ አሉ

በኢየሩሳሌም የሚገኙት የቅድስት አገር ተንከባካቢ ካህን የሆኑት አባ ኢብራሂም ፋልታስ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ላቀረቡት የሰላም ጥሪ አመስግነው፥ ክርስቲያኖች ሠላም እንዲመጣ የሰላም ልዑል ወደሆነው ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲጠቁሙ ጋብዘዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ እሑድ ጥር 5 ቀን 2016 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ባደረጉት ንግግር የትጥቅ ግጭቶች እንዲቆሙ ልባዊ ጥሪያቸውን በማቅረብ፥ ጦርነት “በሰው ልጅ ላይ የሚፈጸም ወንጀል” ነው በማለት አበክረው ማውገዛቸው ተነግሯል።

“ጦርነት ራሱ በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸም ወንጀል ነው። ህዝብ ሰላም ያስፈልገዋል። ዓለም ሰላም ትፈልጋለች” ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ እሑድ ጥር 5 ቀን 2016 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር ሆነው ባደረጉት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ላይ ተናግረዋል። ብጹእነታቸው አክለውም የመልአከ ጸሎት ከማሰማታቸው ከደቂቃዎች በፊት በኢየሩሳሌም የሚገኙት የቅድስት አገር ተንከባካቢ የሆኑት አባ ኢብራሂም ፋልታስ በጣሊያን የቴሌቭዥን ጣቢያ በእንግድነት የቀረቡበትን ፕሮግራም መከታተላቸውን ጠቅሰዋል።

በዚህ ዝግጅት አባ ኢብራሂም ፋልታስ “ስለ ሰላም ማስተማር” አስፈላጊነትን ተናግረው እንደ ነበር ተገልጿል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ከካህኑ ሃሳብ ጋር እንደሚስማሙ በመግለጽ፥ የፍራንቺስካዊያኑን ካህን ጥሪ እንደገና በማስተጋባት፥ “ስለ ሰላም ማስተማር አለብን” ብለዋል። በመቀጠልም እንደተናገሩት “እያንዳንዱን ጦርነት ለማስቆም የሚያስችል በቂ ትምህርት ያለን አይመስልም፥ ስለዚህ ስለ ሰላም ለማስተማር የሚያስችለንን ፀጋ እንድናገኝ ሁሌም ተግተን እንፀልይ” ብለዋል።

አባ ፋልታስ ‘ኢየሱስ ፍትሕና ሰላም ነው’ ማለታቸው

በምላሹም አባ ፋልታስ በእስራኤል እና በሐማስ ጦርነት ምክንያት በቅድስት ሀገር ለሚሰቃዩ ሰዎች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ላሳዩት ቅርበት በማመስገን የቪዲዮ መልእክት ለቫቲካን ዜና ልከዋል።

“አሁን” ይላሉ አባ ፋልታስ በላኩት አጭር የቪዲዮ መልዕክታቸው፥ “እንዴት ለሠላም መጮህ እንዳለብን እና ዬትኛውን መንገድ መከተል እንደሚገባን ለማሳየት ከመጥምቁ ዮሐንስ መማር አለብን” ብለዋል።

ካህኑ በማከልም “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መንገድ፣ ይቅርታ፣ ፍትህ፣ ፍቅር እና ሰላም ነው” ካሉ በኋላ፥ “ኢየሱስን ከተከተልን በእውነት ሰላም ይኖረናል፥ ጦርነትም አይኖርም” ብለዋል።

አባ ፋልታስ በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ ከ60 የሚበልጡ ጦርነቶች እየተካሄዱ እንዳሉ ገልጸው፥ አሁን ያለውን የዓለም አቀፉን ሁኔታ “ፍፁም ግራ መጋባት” ሲሉ ገልፀዋል።

አባ ፋልታስ ሃሳባቸውን ሲያጠቃልሉ፥ “በሰላም መኖር እንፈልጋለን፥ኢየሱስ ክርስቶስን መከተል ከቻልን በዓለም ዙሪያ ሰላምን እናገኛለን” በማለት ደምድመዋል።
 

16 January 2024, 14:16