ፈልግ

የራባት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ክሪስቶባል ሎፔዝ ሮሜሮ - የፋይል ፎቶ የራባት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ክሪስቶባል ሎፔዝ ሮሜሮ - የፋይል ፎቶ 

የሰሜን አፍሪካ ጳጳሳት በሲኖዶሳዊነት ላይ እንደመከሩ ተነገረ

ክልላዊው የሰሜን አፍሪካ ጳጳሳት ጉባኤ (CERNA) ከጥር 2 እስከ 6 ድረስ በሞሮኮ፣ ራባት ከተና ውስጥ ሲያካሂዱ የነበረውን ጉባኤ ውጤት በህትመት መልክ ማውጣታቸው ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

እንደ ጎረጎሳዊያኑ አቆጣጠር በ 1965 የተመሰረተው እና የአልጄሪያ፣ ሊቢያ፣ ሞሮኮ፣ ቱኒዚያ እና ምዕራባዊ ሳሃራ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳሳዊ ጉባኤ ህብረት የሆነው ክልላዊ የሰሜን አፍሪካ ጳጳሳት ጉባኤ (Conférence Episcopale Régionale du Nord de l'Afrique) ለአንድ ሳምንት ያክል በሞሮኮዋ ራባት ከተማ የጉባኤው ዋና ማዕከል ሲያካሂድ የነበረውን ጉባኤውን ማጠናቀቁ ተገልጿል።

ይህ የሰሜን አፍሪካ ጳጳሳት ጉባኤ ሴካም ተብሎ የሚጠራው አህጉራዊ የአፍሪካ እና የማዳጋስካር ጳጳሳት ጉባኤ ሲምፖዚየም አንዱ ክልላዊ ጉባኤ አካል እንደሆነም ተገልጿል።

የራባት ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ስፔናዊው የዚህ ክልላዊ ጉባኤ ፕሬዝዳንት ብፁዕ ካርዲናል ክሪስቶባል ሎፔዝ ሮሜሮ ከሌሎች ጳጳሳት ወንድሞቻቸው ጋር ሆነው ስለ አጠቃላይ ጉባኤው በሰጡት መግለጫ ውይይቱ በሦስት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እንደነበረና፥ እነዚህም በሲኖዶሳዊነት ላይ እየተካሄደ ባለው ሲኖዶሳዊ ሂደት ላይ፣ የመግሪብ አብያተ ክርስቲያናት ተብለው በሚጠሩት የሰሜን አፍሪካ ቤተክርስቲያናት ሕይወት ላይ ሥነ መለኮታዊ አስተንትኖ መስጠት እንዲሁም በቅርቡ ከቅድስት መንበር የጳጳሳዊ የእምነት አስተምህሮ ጽ/ቤት ‘የቡራኬ ሃዋሪያዊ ትርጓሜ’ ብሎ ያስተላለፈውን ሰነድ ስለመቀበል አስፈላጊነት ላይ ሲመክር እንደነበረ አብራርተዋል።

ጉባኤው በተጨማሪም የሞሮኮ ታንጋይር ሊቀ ጳጳስ እ.አ.አ. ከ1836-1896 ድረስ የኖሩትን እና በጽሑፎቻቸው፣ በበጎ አድራጎት ተነሳሽነታቸው እንዲሁም የሞሮኮ ሙስሊሞች እና ክርስቲያኖች ዓለም መካከል ባህላዊ እና ማህበራዊ ህይወትን ለማቀራረብ በሠሩት ሥራ ከፍተኛ እውቅና ያተረፉ እና በሀገረ ስብከቱ ላይ በጎ አሻራቸውን የጣሉትን የአባ ጆሴ ማሪያ ለርቹንዲ ቅድስና ለማረጋገጥ ያነሱትን ቅድመ ሃሳብ ለመደገፍ መወሰኑን አስታውቋል።

ቀጣዩ ጉባኤም ‘አድ ሊሚና’ ተብሎ የሚታወቀውን ክልላዊ ጉባኤዎች ዓመታዊ የቅድስት መንበርን ጉብኝትን ምክንያት በማድረግ ጥቅምት 2017 ዓ.ም. በሮም እንደሚያካሂድ ተገልጿል።

 

17 January 2024, 15:04