ፈልግ

በኳታር የመጀመሪያ በሆነው ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎታቸውን አቀረቡ

የሰሜን አረቢያ ሐዋርያዊ አስተዳዳሪ የሆኑት ብጹዕ አቡነ አልዶ ቤራርዲ፥ በኳታር መዲና ዶሃ በሚገኝ የመጀመሪያው የክርስትና አምልኮ ሥፍራ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎትን መርተዋል። በዶሃ ከተማ ውስጥ በሚገኘው የመቁጠሪያ እመቤታችን ማርያም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በቀረበው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ በርካታ ካቶሊካዊ ምዕመናን ተገኝተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በኳታር የምትገኘው ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ከተለያዩ አገራት ለመጡ ካቶሊክ ማኅበረሰቦች የተስፋ እና የአንድነት ምልክት እንዲሆን የታሰበ ታላቅ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት አቅርባለች። በኳታር መዲና ዶሃ በሚገኝ የመቁጠሪያ እመቤታችን ማርያም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በቀረበውን መስዋዕተ ቅዳሴ የሰሜን አረቢያ ሐዋርያዊ አስተዳዳሪ የሆኑት ብጹዕ አቡነ አልዶ ቤራርዲ መርተዋል። ብጹዕ አቡነ ቤራርዲ ፊደስ ለተሰኘ የቫቲካን የዜና ወኪል እንደተናገሩት፥ በአዲሱ ዓመት መባቻ ላይ በቀረበው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ወደ 30,000 የሚጠጉ ምዕምናን ተካፋይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በኳታር የምትገኝ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን

በኳታር የምትገኝ የመጀመሪያዋ የመቁጠሪያ እመቤታችን ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እንደ ጎርጎሮሳዊው በ 2006 ዓ. ም. የተመሠረተች ሲሆን፥ በአገሪቱ ውስጥ ከ7ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ የመጀመርያዋ የክርስቲያን የአምልኮ ሥፍራ መሆኗ ታውቋል። በአገሪቱ ቤተ ክርስቲያንን ለማነጽ መንግሥት ፍቃድ እንዲሰጣቸው ጥያቄያቸውን ያቀረቡት በኳታር የሚገኙ የበርካታ አገራት አምባሳደሮች በተለይም የፈረንሳይ አምባሳደር መሆናቸው ይታወሳል።

በወቅቱ የኳታር አሚር የነበሩት ሃማድ ቢን ካሊፋ አል ታኒ ቤተ ክርስቲያኑ የሚታነጽበት መሬት ሲለግሡ  በቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ የነበሩት ብፁዕ ካርዲናል ኢቫን ዲያስ፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ መጋቢት 15/2008 ዓ. ም. ሥፍራውን መባረካቸው ይታወሳል። ብጹዕ አቡነ አልዶ ቤራርዲ ቤተ ክርስቲያኗ ግዙፍ እና በአዲሱ አየር ማረፊያ አቅራቢያ የታነጸች፣ የፕሮቴስታንትን፣ የህንዱ እና የኮፕትን ጨምሮ የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት በሚገኙበት አካባቢ እንደምትገኝ ገጸዋል።

በግቢው ከታነጹት የእምነት ሥፍራዎች መካከል ትልቁን ቦታ የወስደው ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መሆኑን ብጹዕ አቡነ አልዶ ቤራርዲ ጠቅሰው፥ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ተጨማሪ ቤተ ክርስቲያኖችን ለማነጽ ፍላጎት መኖሩን ገልጸዋል። “በየሳምንቱ ዓርብ አስደናቂ ነው” ያሉት ብጹዕ አቡነ ቤራርዲ፥ እንደ ኦርቶዶክሶች፣ ኮፕቶች፣ ፕሮቴስታንቶች እና የሕንድ አብያተ ክርስቲያናት፥ በርካታ ካቶሊክ ምዕመናንም የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት እንደሚሳርጉ ገልጸው፥ በአካባቢው የሕንድ እና የፊሊፒንስ ትምህርት ቤቶች በስፋት መገንባታቸውንም አስረድተዋል።

ብጹዕ አቡነ አልዶ ቤራርዲ በገለጻቸው፥ በሰሜን አረቢያ ሐዋርያዊ አስተዳደር ውስጥ በሚገኙ አገራት ውስጥ ማለትም በባህሬን፣ በኳታር እና በኩዌት ጨምሮ በሳውዲ አረቢያ ያለውን ሁኔታ አብራርተው፥ እነዚህ አገራት በህግ፣ በባህል፣ በጎሳ ተጽእኖ እና በሙስሊም የእምነት ዝንባሌዎች የሚለያዩ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ለኳታር ባለ ስልጣናት የቀረበ ምስጋና

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አዲስ የገባውን የ 2024 ዓ. ም. ምክንያት በማድረግ በቀረበ የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ ሥር ዓት ላይ፥ የመቁጠሪያ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቁምስና መሪ ካህን አባ ዛቪዬር ዲ’ሱዛ  አቡነ አልዶ ቤራርዲን አመስግነው፥ ማኅበረሰቡን ለመምራይ ያላሰለሰ ጥረት ማግረጋቸውንም አስረድተዋል። አባ ዲሶዛ በተጨማሪም የኳታርን ኤሚርን፣ የአገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትርን፣ ንጉሣዊ ቤተሰብን እና ግለሰቦችን፥ አስፈላጊ የሆኑ መገልገያዎችን እና ማረጋገጫዎችን በመስጠት ለተባበሩት የመንግሥት እና የጸጥታ ኃይሎች አመስግነው፥ የአገልግሎት ድጋፍ እንዲያገኙ ለረዱት ለዋና ጸሐፊው የአገልግሎት ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ምክትል ዳይሬክተር ወ/ሮ ማርያም ናስር አል ሃይል ልዩ ምስጋና አቅርበዋል።

11 January 2024, 15:43