ፈልግ

ሄይቲያዊያን የተከሰተውን የጸጥታ ችግር በመቃወም የወጡት ሰልፍ ሄይቲያዊያን የተከሰተውን የጸጥታ ችግር በመቃወም የወጡት ሰልፍ  (ANSA)

መሳሪያ ያነገቡ ታጣቂዎች በሄይቲ ስድስት መነኮሳትን አግተው መውሰዳቸው ተነገረ

የተለያየ መሳሪያ ያነገቱ ታጣቂዎች የሄይቲ ዋና ከተማ በሆነችው ፖርት ኦ-ፕሪንስ ቢያንስ ስድስት መነኮሳትን አግተው በአውቶብስ በማሳፈር ወዳልታወቀ ቦታ መውሰዳቸው ተዘግቧል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የሄይቲ ዋና ከተማ አስተዳደር ከሁሉም የአገልግሎት መዋቅሮች ውጭ ወደ ሆኑት አጎራባች ከተሞችም ጭምር እየተዛመተ ያለውን ሁከት ለማረጋጋት እና ለመግታት እየታገለ ባለበት ወቅት ስድስት የቅድስት አኔ ማህበር መነኮሳትን ጨምሮ ሲጓዙበት የነበረውን መኪና ሹፌር እና ሌሎች ተሳፋሪዎች በታጣቂዎች ታፍነው መወሰዳቸውን የአካባቢው ምንጮች ዘግበዋል።

ታጣቂዎቹ ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲያቀና የነበረውን የተጋቾቹን ሚኒባስ በማስቆም እገታውን እንደፈፀሙ የተነገረ ሲሆን፥ እገታው የተፈፀመውም ባለፈው ጥር 10 ቀን 2016 ዓ.ም. በጠራራ ፀሐይ በዋና ከተማዋ ፖርት-ኦ-ፕሪንስ መሀል ከተማ ላይ እንደሆነም ተነግሯል።

ከአካባቢው ቤተ ክርስቲያን የቀረበ ጥሪ

የሄይቲ የሃይማኖት ጉባኤ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የተረጋገጠውን ይሄንን አፈና የአንሴ ግራ ቮው እና ሚራጎን ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ፒየር-አንድሬ ዱማስ አጥብቀው ያወገዙት ሲሆን፥ “ወጣቶችን፣ ድሆችን እና በጣም ተጋላጭ የሆኑትን ሰዎችን ለማስተማር እና ለማብቃት ራሳቸውን ሙሉ በሙሉ ለእግዚአብሔር የሰጡ እነዚህን የተቀደሱ ሴቶች ክብር በጎደለው ሁኔታ አስጸያፊ እና አረመኔያዊ ድርጊት ተፈጽሞባቸዋል” በማለት በጽኑ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ጳጳሱ ታጋቾቹ እንዲፈቱ እና የእነዚህ ‘አስጸያፊ እና ወንጀለኞች ድርጊቶች’ በአስቸኳይ እንዲቆም ጥሪ በማቅረብ፥ “ሁሉም የሄይቲ ማህበረሰብ እጅ ለእጅ ተያይዞ እውነተኛ የትብብር መንፈስ በመመስረት ታጋቾቹ ተለቀው ወደ ቤተሰቦቻቸው እና ማህበረሰባቸው በፍጥነት እና በሰላም እንዲመለሱ ተባብሮ መስራት ይገባል” ካሉ በኋላ በመጨረሻም ብጹዕ አቡነ ዱማስ እራሳቸውን በታጋቾቹ ለመቀየር ፈቃደኛ እንደሆኑ ገልፀዋል።

የሁከቱ መጨመር

ካለፈው እሁድ ጀምሮ የታጠቁ ቡድኖች የግድያ ተግባራቸውን እያጠናከሩ የመጡ ሲሆን፥ ይሄንን ህገወጥነት በመቃወም በመላ ሀገሪቱ ሰላማዊ ሰልፎች ተዘጋጅተዋል።

ሐሙስ ዕለት ከፖርት ኦ-ፕሪንስ በስተደቡብ በሚገኘው የሶሊኖ አውራጃ በተቀናቃኝ ቡድኖች መካከል የተኩስ ልውውጥ እንደተካሄደ እና እንደ አንዳንድ የዓይን እማኞች ዘገባ ከሆነ በግጭቱ ወደ ሃያ የሚጠጉ ሰዎች ህይወት ማለፉ ተነግሯል።

ካሬፎር ፔን እና ዴልማስ 24 የተባሉ ሌሎች የዋና ከተማዋ ወረዳዎችም የወሮበሎቹ ጥቃት ኢላማ እንደሆኑ እና የፖርት ኦ-ፕሪንስ ነዋሪዎችም እራሳቸውን ከጥቃት ለመከላከል የተለያዩ መከላከያዎችን እንዳዘጋጁ ተዘግቧል።

ለበርካታ ሳምንታት በፖርት ኦ-ፕሪንስ እና በዋና ዋና መንገዶች ላይ የአፈና ድርጊቶች እየጨመሩ መምጣታቸው የተነገረ ሲሆን፥ ባለፈው ሳምንት አንድ የሰላም ተሟጋች ዶክተር ታግቶ የማስለቀቂያ ክፍያ ከፍሎ እንደተለቀቀም ተዘግቧል። 

ሁከቱን በመቃወም የተዘጋጁ ሰልፎች

በተመሳሳይ ዜና በእፅ ማዘዋወር ጋር በተገናኘ ተከሰው በአሜሪካ ውስጥ የእስር ቅጣታቸውን ጨርሰው ወደ ሄይቲ የተመለሱት የቀድሞው የፖሊስ አዛዥ እና ፖለቲከኛ በሆኑት ጋይ ፊሊፕ የሚመራው ፀረ-መንግስት ሰልፎች በመላ አገሪቱ ብጥብጥ እየፈጠሩ ሲሆን፥ ፕሬዝዳንት ጆቨኔል ሞይስ እ.አ.አ. በ 2021 ከተገደሉ በኋላ በስልጣን ላይ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኤሪኤል ሄንሪ የፀጥታ እጦት በመጨመሩ እና እየተንኮታኮተ ያለውን ኢኮኖሚ ለመቋቋም በቂ ጥረት አላደረጉም በማለት ተተችተው ተቃዋሚዎች ስልጣን እንዲለቁ እየጠየቁ እንደሆነም ተገልጿል።
 

22 January 2024, 16:04