በአፍሪካ እና በአውሮፓ የቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሳዊነት ላይ ውይይት ተካሄደ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የአፍሪካ እና የማዳጋስካር ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ሲምፖዚዬም (SECAM) እና የአውሮፓ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤዎች ምክር ቤት (CCEE) ተወካዮች ሰባተኛውን የጋራ ሴሚናር በዚህ ሳምንት ለማካሄድ በኬንያ መዲና ናይሮቢ ይገኛሉ።
በአፍሪካ እና በአውሮፓ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያናት መካከል ያለውን ጥልቅ መግባባት እና አንድነት የሚያጎለብቱ ሴሚናሮችን ማካሄድ የጀመሩት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2004 ዓ. ም. እንደ ነበር ይታወሳል።የአፍሪካ እና የማዳጋስካር ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ሲምፖዚዬም ዋና ጸሐፊ አባ ራፋኤል ሲምቢነ ጁኒየር ከሴሚናሩ አስቀድመው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተናገሩት፥ “ሲምፖዚዬሙ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ኅብረት ለጋራ ውይይት እና መግባባት ወሳኝ መድረክ ሆኗል” ብለዋል።
ወጣቶችን በማዳመጥ ላይ ማትኮር
ከጥር 14-17/2016 ዓ. ም. ድረስ የሚካሄደው ሴሚናሩ፥ “አፍሪካ እና አውሮፓ ሲኖዶሳዊ ጉዞን አብረው ይጓዛሉ” በሚል መሪ ሃሳብ ላይ የተዘጋጀ ሲሆን፥ በሁለቱም አህጉራት የሚገኙ ወጣቶች ድምፅ በማዳመጥ እና የቤተ ክርስቲያንን የወደፊት ዕቅድ በመቅረጽ ላይ ያላቸውን ወሳኝ ሚና በመገንዘብ ልዩ ትኩረት የሚሰጥ ነው ተብሏል።
አባ ራፋኤል በመግለጫቸው፥ ስብሰባቸው በቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ መካከል ያሉ አዳዲስ አድማሶችን በመመልከት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመጣው “ግሎባላይዜሽን” አውድ ውስጥ የታዩ ፍሬያማ ውይይቶች የሚካሄድበት እንደሆነ አስገንዝበዋል። ስብሰባውን ረቡዕ ጥር 15/2016 ዓ. ም. በንግግር የከፈቱት የናይሮቢ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፊሊፕ አርኖልድ ሱቢራ አንዮሎ ሲሆኑ፥ የመግቢያ ንግግር ያደረጉት የአፍሪካ እና የማዳጋስካር ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ሲምፖዚዬም ዋና ጸሐፊ አባ ራፋኤል ሲምቢነ ጁኒየር ናቸው።
ውይይት የተደረገባቸው ርዕሦች እና ዋና ተናጋሪዎች
በሴሚናሩ ውይይት ከሚደረግባቸው ዋና ዋና ርዕሠ ጉዳዮች መካከል፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስ ፍራንችስኮስ ‘ወንጌልን ስበኩ’ በሚል ርዕሥ በቅድስት መንበር ለሚገኙ ከፍተኛ ጳጳሳዊ ምክር ቤቶች ያስተዋወቁት ሐዋርያዊ ደንብ በዓለም ዙሪያ ለምትገኝ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ከሚሰጠው አገልግሎት አኳያ በሂደት ላይ የምትገኝ ቤተ ክርስቲያንን ለመገንዘብ የሚረዱ ልዩ ልዩ ንግግሮች እና ውይይቶች እንደሚቀርቡ ታውቋል። የሴሚናሩ ተካፋዮች በተጨማሪም በአህጉር ደረጃ ግንዛቤን ለማስጨበጥ ሲካሄድ የቆየው እና እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2023 ዓ. ም. በሮም በተጠናቀቀው የመጀመርያ ዙር የሲኖዶስ ጉባኤ ላይ ግንዛቤን ለመጨበጥ እንደሚጥሩ ታውቋል።
በሴሚናሩ ላይ ንግግር የሚያደርጉ እንግዶች፥ በዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ኮንጎ የኪንሻሳ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ፍሪዶሊን አምቦንጎ ቤሱንጉ፣ የሉክሰምበርግ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ዣን ክላውድ ሆሌሪች፣ በሊጡዌኒያ የቪልኒየስ ከተማ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጊንታራስ ግሩሳስ፣ በሞዛምቢክ የዛይ-ዛይ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሉሲዮ አንድሪስ ሟንዱላ፣ በፈረንሳይ የሬኔስ ከተማ ሊቀ ጳጳስ አቡነ አሌክሳንደር ጆሊ እና በታንዛኒያ የኮንዶዋ ጳጳስ አቡነ በርናንዲን ፍራንሲስ ምፉምቡሳ ናቸው።
የሴሚናሩ ተካፋዮች በሁለተኛ ቀን ውሎአቸው “ቤተ ክርስቲያን በሲኖዶሳዊ ሂደት አንፃር በአፍሪካ እና በአውሮፓ የሚገኙ ወጣቶችን እንዴት ማድመጥ እንደምትችል” በሚል መሪ ሃሳብ ላይ የሚወያዩ ሲሆን፥ በሴሚናሩ ማጠቃለያ ቀን መግለጫን በማውጣት ዓርብ ጥር 17/2016 ዓ. ም. የመዝጊያ መስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት እንደሚያሳርጉ ታውቋል።
የአፍሪካ እና የአውሮፓ ጳጳሳት ለሲኖዶሳዊነት ያላቸው ቁርጠኝነት
የአፍሪካ እና የማዳጋስካር ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ሲምፖዚዬም ዋና ዋና ጸሐፊው አባ ራፋኤል ሲምቢነ በመግለጫቸው፥ "ሴሚናሩ በአፍሪካ እና በአውሮፓ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ባለው የሲኖዶሳዊነት መንፈስ የጋራ ዕድገት ቀጣይነት ያመለክታል" ብለዋል። "በሁለቱም አውድ ውስጥ የቀረቡትን ልዩ ተግዳሮቶች እና ዕድሎች ለመረዳት እና ለመፍታት በመፈለግ በአህጉራት ውስጥ የውይይት እና የትብብር ኃይል እንደ ማሳያ ይቆማል" ብለዋል።
አሁን ካለው ዓለም አቀፋዊ አሳሳቢ ሁኔታ አንጻር ይህ ትብብር ከሁሉም በላይ አስፈላጊ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተው፥ “ዓለማችን ከዚህ በፊት ታይተው የማያውቁ ለውጦችን እና ፈተናዎችን እየተጋፈጠ በሚገኝበት ወቅት፥ ፍትሕን፣ ሰላምን እና አንድነትን በማስፋፋት ረገድ ቤተ ክርስቲያን የምትጫወተው ሚና ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ወሳኝ ይሆናል” በማለት ተናግረዋል። "ይህ ሴሚናር ያንን ሚና ያቀፈ፣ ለጋራ ትምህርት መድረክን የሰጠ እና በሁሉ አቀፍ ቤተ ክርስቲያን አካላት መካከል ትብብር አስፈላጊ ነው" በማለት አስገንዝበዋል።
ያለፈው የ 2021 (እ. አ. አ) ምናባዊ ስብሰባ
የናይሮቢ ሴሚናር መጀመሪያ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2021 ዓ. ም. ሊካሄድ የታቀደ ቢሆንም፥ ነገር ግን የአፍሪካ እና የአውሮፓ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ተወካዮች በኮቪድ-I9 ወረርሽኝ ምክንያት መገናኘት ባለመቻላቸው በአውታረ መረብ አማካይነት ብቻ መካሄዱ ይታወሳል።
የሴሚናሩ ተካፋዮች በመግለጫቸው ማጠቃለያ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” በማለት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2020 ዓ. ም. ይፋ ባደረጉት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ላይ እንደተገለጸው፥ ለዓለም አቀፍ ወንድማማችነት፣ ወዳጅነት እና በሰላም አብሮ የመኖር ጥሪን በማክበር በአኅጉሮቻቸው በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ውይይት እንዲካሄድ አበረታትተዋል።