ፈልግ

ውርጃ በልጆች እና በእናቶች ላይ የሚያስከትለውን አደጋ መከላከል ውርጃ በልጆች እና በእናቶች ላይ የሚያስከትለውን አደጋ መከላከል   (©unlimit3d - stock.adobe.com)

የአሜሪካ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውርጃን የሚቃወም የዘጠኝ ቀናት ዓመታዊ የጸሎት መርሃ ግብር አዘጋጀች

ወርጃን በመቃወም በጸሎት ወደ ንስሐ ለመመለስ በሚል እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1973 ዓ. ም. ውሳኔ የተሰጠበት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፍርድ 51ኛ ዓመት ለማክበር በሰሜን አሜሪካ የምትገኝ ካቶሊክ ቤተ ክስቲያን ዓመታዊ የዘጠኝ ቀናት የጸሎት መርሃ ግብር ይፋ አድርጋለች። የአገሪቱ ብጹዓን ጳጳሳት በዚህ መርሃ ግብር በኩል ሕፃናትን እና እናቶቻቸውን ከውርጃ አስከፊነት ለመከላከል ቀጣይነት ያለው ጥረት እንደሚያስፈልግ በድጋሚ ተናግረዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በመላው ሰሜን አሜሪካ የሚገኙ ካቶሊክ ምዕመናን ውርጃን በመቃወም ዘንድሮ ጥር 7/2016 ዓ. ም. በሚጀምር የዘጠኝ ቀናት የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ ለመገኘት ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ታውቋል። የጸሎት መርሃ ግብሩን በሰሜን አሜሪካ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ሥር የሚገኝ የሕይወት እንክብካቤ መምሪያ ያስተባበረ ሲሆን፥ ዘጠኝ ቀናቱን የሚወስድ የጸሎት ሥነ-ሥርዓት የሚካሄደው  የአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ 1973 ዓ. ም. ውርጃን ህጋዊ ያደረገበትን የሮ ቪ ዋድ ብይን በማስታወስ ለሕጻናት ህጋዊ ጥበቃ እንዲደረግላቸው ዓመታዊ ጸሎት ከሚቀርብበት ቀን ቀደም ብሎ ጥር 13/2016 ዓ. ም.  ቀን እንደሆነ ታውቋል።

የመጀመሪያው የዘጠኝ ቀናት የጸሎት ሥነ-ሥርዓት የተካሄደው በ 2013 (እአአ) ነበር

ውርጃን በመቃወም ለዘጠኝ ቀናት የሚቆይ የጸሎት ሥነ-ሥርዓት የተጀመረው የአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ 1973 ዓ. ም. ውርጃን ህጋዊ ያደረገበት ውሳኔ 40 ኛ ክብረ በዓል ላይ፥ ማለትም እንደ ጎሮጎሮሳውያኑ በ 2013 ዓ. ም. እንደ ነበር ሲታወስ፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ 1974 ዓ. ም. ጀምሮ በዋሽንግተን ዲሲ እና ከዚያም በመላው የአሜሪካ ግዛቶች ውስጥ ውርጃን በመቃወም ሕይወትን የሚደግፍ የእግር ጉዞ ሲካሄዱ ቆይተዋል።

ዘንድሮ በሚካሄደው የጸሎት መርሃ ግብር እያንዳንዱ ዘጠኙ ቀናት የሕይወት ባህልን ለመገንባት የሚያግዙ አስተንትኖ የሚደረግባቸው፥ በዕለታዊ ሥራዎች የታጀቡ ትምህርት ሰጭ መረጃዎች የሚቀርቡባቸው እንደሆነ ታውቋል። የጸሎቱ ተሳታፊዎች የሕይወት ድጋፍ ምስክራቸውን ለሌሎች ጓደኞቻቸው በማካፈል እና የማህበራዊ ድረ ገጾቻቸው ተከታዮች በ#9DaysforLife ማህበራዊ ሚዲያ ሃሽታግ አማካይነት እንዲጸልዩ ጋብዘዋል።

የ “ሮ” እና “ዋድ” ብያኔን የቀለበሰ የ 2022 ዓ. ም. የጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ

ለ12ኛ ጊዜ የተዘጋጀው የጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ፥ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በሰኔ 2022 ዓ. ም. “ሮ” እና “ዋድን” በመላው የሀገሪቱ ግዛቶች የሚገኙ የህግ አውጭዎች ፅንስን ማቋረጥ የመገደብ ወይም የመከልከል ስልጣንን ከሻረበት ከሁለት ዓመት ገደማ በኋላ እንደሆነ ታውቋል። ውሳኔው ውርጃን ለመከላከል የሚያስችል አንድ እርምጃ ቢሆንም፥ የሰሜን አሜሪካ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ልጆችን እና እናቶቻቸውን ውርጃ ከሚያስከትለው አደጋ ለመጠበቅ ቀጣይነት ያለው ጥረት እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፥ የዘጠኝ ቀናት ጸሎት ዋና ዓላማም ፅንስ ማስወረድን ሙሉ በሙሉ እንዲቆም ለማድረግ እንደሆነ ተናግረዋል።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከሰኔ 2022 ዓ. ም. ጀምሮ 14 የአሜሪካ ግዛቶች በጠቅላላ ፅንስ ማስወረድን የሚከለክሉ ሕጎችን ሲያወጡ፥ ሁለት ግዛቶች፥ የጆርጂያ እና የደቡብ ካሮላይና ግዛቶች ላለፉት ስድስት ሳምንታት ፅንስ ማቋረጥን አግደዋል። ይሁን እንጂ ሌሎች ግዛቶች ፅንስ ማቋረጥን የሚከለክሉ ሕጎችን አውጥተዋል ወይም የድምፅ መስጫ ህዝበ ውሳኔ አካሂደዋል። እስካሁን ሰባት ግዛቶች ፅንስ ማስወረድ ላይ በቀጥታ ድምጽ የሰጡ ሲሆን የሁለቱ ግዛቶች ህግ አውጪዎች የፅንስ ማቋረጥ መብት ህገ-መንግሥታዊ ማሻሻያዎችን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2024 ዓ. ም. ድምጽ እንዲሰጥበት ያደረጉ ሲሆን፥ በሌላ በኩል ቢያንስ በዘጠኝ ግዛቶች ውስጥ የሚገኙ የፅንስ ማስወረድ ተሟጋቾች በምርጫው ላይ ተመሳሳይ እርምጃዎችን ለመውሰድ በዜጎች የሚመሩ ጥረቶችን እያደረጉ ይገኛሉ።

የማሕጸን ኪራይን በተመለከተ የወጣ መግለጫ

ከዘጠኝ ቀኑ የጸሎት መርሃ ግብሩ ቀደም ብሎ የሰሜን አሜሪካ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ማሕጸን ለሌላ ሰው በኪራይ ማቅረብን በጽኑ ማውገዛቸውን በመደገፍ፥ “ይህ ተግባር በሰው ሕይወት ክብር ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ነው” ሲሉ ገልጸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የዓለምን ሁኔታ በማስመልከት በቅድስት መንበር ሥር ለሚገኙ የውጭ አገራት አምባሳደሮች እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ዘንድሮ ጥር 8 ባደረጉት ዓመታዊ ንግግር፥ ማሕጸን ለሌላ ሰው ማከራየት የሚያሳዝን እንደሆነ ገልጸው፥ “ተተኪ እናት እየተባለ የሚጠራው” የብዝበዛ ተግባር በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲታገድ ጠይቀዋል። ይህም የእናትን ቁሳዊ ፍላጎቶች በመበዝበዝ ላይ የተመሠረተ የሴቷን እና የሕፃኑን ክብር መጣስን የሚያመለክት ነው ብለዋል። “ልጅ ሁል ጊዜ ስጦታ እንጂ ለንግድ የሚቀርብ አይደለም” ሲሉ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አሳስበዋል።

የሰሜን አሜሪካ ካቶሊክ ጳጳሳት በመልዕክታቸው፥ “እናትን በሌላ እናት የመተካት ልምምድ ከሥነ ምግባር አኳያ የማይፈቀድ ነው” ሲሉ ተናግረው፥ ይልቁንስ በሁሉም ደረጃ እና የሕይወት ሁኔታዎች ውስጥ የእያንዳንዱን ሰው ጥልቅ ክብር ለመጠበቅ መጸለይ እና መሥራት ይገባል ብለዋል።

ፅንስ የማስወረድ ዛቻን መጋፈጥ የአሜሪካ ካቶሊክ ጳጳሳት ቅድሚያን የሚሰጡበት ጉዳይ ነው

የአሜሪካ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ በቅርቡ፥ “ሕሊና ያላቸውን ታማኝ ዜጎችን ማፍራት” በሚል ርዕሥ አሻሽለው ባዘጋጁት የ 2024 ዓ. ም. የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሠነድ፥ ፅንስን የማስወረድ ስጋት ብጹዓን ጳጳሳቱ ቅድሚያን የሰጡበት ጉዳይ እንደሆነ አረጋግጠው፥ ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑትን እና ድምጽ የሌላቸውን ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን በቀጥታ የሚያጠቃ መሆኑንም አስገንዝበዋል። በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ በጽንስ ማስወረድ ተግባር በዓመት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሕይወት እንደሚጠፋ ታውቋል።

 

11 January 2024, 13:35