በቡርኪናፋሶ በተፈጸመ የሽብር ጥቃት 15 ካቶሊኮች መሞታቸው ተዘገበ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የጅሃዲስት ቡድኖች በብዛት በሚንቀሳቀሱባት ቡርኪና ፋሶ እሁድ ዕለት በተፈጸመ የሽብር ጥቃት ቢያንስ 15 ካቶሊኮች በሥርዓተ ቅዳሴ ላይ እያሉ መገደላቸውን የአከባቢው የቤተክርስቲያን ምንጮች ዘግበዋል።
ጥቃቱ የተፈፀመው በሀገሪቱ ሰሜን ምስራቅ ኦውዳላን ግዛት ውስጥ በሚገኘው ከማሊ እና ከኒጀር ጋር በምትዋሰነው በኤስካኔ መንደር የዶሪ የካቶሊክ ሀገረ ስብከት ውስጥ እንደሆነም ተገልጿል።
ብጹእ አቡነ ሎረን ቢርፉዎሬ ዳቢሬን በመወከል የሀገረ ስብከቱ ምክትል አስተዳዳሪ የሆኑት አባ ዣን ፒየሪ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ፥ 12 ምእመናን ጥቃቱ በተፈጸመበት ቦታ ወዲያው ሕይወታቸውን ሲያልፍ፣ ሦስቱ ደግሞ ቆስለው በህክምና ላይ እያሉ ሕይወታቸው እንዳለፈ፥ እንዲሁም ሁለቱ አሁንም ሆስፒታል ውስጥ በህክምና ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ለሞቱት ሰዎች እና ሞትን እያደረሱ ላሉት ጸሎት
አባ ዣን ፒየር በሰጡት አጭር ጋዜጣዊ መግለጫ ምዕመናን “በእምነት ለሞቱት፣ ለቆሰሉት ፈውስ እና ሐዘን ላይ ለሚገኙ መጽናናት እንዲሆንላቸው” በትጋት እንዲጸልዩ ጋብዘዋቸዋል።
ካህኑ በማከልም “በአገሪቱ ላይ ሞትና ውድመት እያደረሱ የሚገኙት” ወደ ክርስትና እንዲመለሱ ጸሎት እንዲደረግላቸው ከጠየቁ በኋላ፥ “በዚህ የተባረከ የዐብይ ጾም ወቅት የንሰሃ እና የጸሎት ትጋታችን ለሀገራችን ቡርኪናፋሶ ሰላምና ደህንነትን እንዲያመጣልን ነው” ብለዋል።
በሳህል ክልል ውስጥ ያለው የሰብአዊ እና የደህንነት ሁኔታ እያሽቆለቆለ ነው
ማሊን እና ኒጀርን በሚያካትተው በሰፊው የሳህል ክልል ውስጥ ከሚንቀሳቀሱት ከ አይ ኤስ እና አልቃይዳ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ከሚነገረው በኢስላማዊ አሸባሪ ቡድን፥ የካቲት 17 ቀን 2016 ዓ.ም. እሁድ ዕለት የደረሰው ጥቃት አሸባሪው ሲያደርሳቸው ከነበሩት ተከታታይ ጥቃቶች የቅርብ ጊዜው እንደሆነ እና ባለፉት 16 ዓመታት ውስጥ ሽብርተኝነት ከ2,000 በመቶ በላይ በመጨመር በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች መፈናቀል ምክንያት መሆኑ ይነገራል።
በ 2003 ዓ.ም. በሊቢያ የእርስ በርስ ጦርነት ከተካሄደ በኋላ፣ በ2004 ዓ.ም. እስላማዊው ቡድን ሰሜን ማሊን ተቆጣጥሮ የነበረ ቢሆንም፥ የማሊ መንግስት በ2005 ዓ.ም. በፈረንሣይ ጦር ድጋፍ አሁን ላይ በኢስላመዊው ቡድን ስር ያሉትን አብዛኛውን ግዛቱን ተቆጣጥሮ ነበር።
በ 2013 ዓ.ም. ወታደሮች በመፈንቅለ መንግስት ሥልጣን ከያዙ በኋላም የጂሃዲስቶች አመጽ ተጠናክሮ በመቀጠል አሁንም ድረስ በወታደራዊ ጁንታዎች እየተመሩ በሚገኙት ወደ ጎረቤት ሃገራት ኒጀር እና ቡርኪናፋሶ ተዛምቷል።
ሽብርተኝነት በቡርኪናፋሶ ቤተክርስቲያን ላይ ስለሚያሳድረው አስከፊ ተጽእኖ
በ2015 ዓ.ም. የቡርኪናፋሶ እና የኒጀር የጋራ ጳጳሳት ጉባኤ ሊቀ መንበር የሆኑት ብጹእ አቡነ ቢርፉኦሬ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ቤተክርስትያናትን የሚረዳው ‘ኤ. ሲ. ኤን.’ ለተባለው የካቶሊክ ፋውንዴሽን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት የዚህ የሽብር ማዕበል ቤተክርስቲያን ላይ የሚያስከትለው መዘዝ ከባድ መሆኑን ገልጸው ነበር።
እነዚህ አሸባሪ ድርጅቶች አንዳንድ ጊዜ አብያተ ክርስቲያናትን ከማጥቃት በተጨማሪ አሸባሪዎቹ የውጭ አገር ሚሲዮናውያንን፣ ካህናትን፣ የስነመለኮት ተማሪዎችን፣ ገዳማዊያንን እና ምዕመናንን ስለሚያግቱ፥ ይሄንን ጥቃት በመስጋት ምዕመናን ወደ አቢያተ ክርስቲያናት ስለማይመጡ፥ ቁጥራቸው እየጨመረ የነበሩ ደብሮችም ባዶ እየሆኑ መምጣታቸው ተነግሯል።
ጳጳሱ የሃገሪቷን ግማሹን ግዛት በመላ ሀገሪቱ ላይ እስልምናን ለመጫን በሚፈልጉ ጂሃዲስት ቡድኖች ቁጥጥር ስር መሆኑንም ያረጋገጡ ሲሆን፥ “አሸባሪዎቹ ሙስሊሞችን ጨምሮ ይህን ማህበረሰብ እና አንድ አይነት የእስልምና ስም የማይናገሩትን ሁሉ ለማጥፋት ይፈልጋሉ፥ ይህ ማለት አሸባሪው አሁንም በህብረተሰቡ ላይ ያነጣጠረ ነው” ብለዋል።
በመቀጠልም “የእስልምና እና የሙስሊሞች ድጋፍ ሰጪ ቡድን” በሚል መጠሪያ የሚታወቀው የጂሃዲስት ቡድን በምዕራብ አፍሪካ ህዝቦች ውስጥ በጣም ዝነኛ መሆኑን ገልፀው “የቡድኑ ትክክለኛ ዓላማ የተለያዩ ሃይማኖቶች ባለቤት የሆነውን የዛሬውን ህብረተሰብ መጨቆን ነው” ብለዋል።
በሳህል ክልል ከሽብርተኝነት ጋር የተገናኘ የሞት መጠን ከአጠቃላይ ሞት 43 በመቶ ይሆናል
በ2015 ዓ.ም. ጂ.ቲ.አይ በተባለው ዓለም አቀፍ የሽብርተኝነት መረጃ ጠቋሚ ተቋም ዘገባ መሠረት በሳህል ክልል ከሽብርተኝነት ጋር የተዛመዱ የሞት ብዛት በ2014 ዓ.ም. በዓለም አቀፍ ደረጃ ከደረሰው የሞት መጠን 43 በመቶውን እንደሚሆን ዘግቧል።
በቡርኪናፋሶ ያለው ብጥብጥ በመስፋፋት ወደ ጎረቤት ሀገራትም በመዛመት ቶጎ እና ቤኒን በተቋሙ ከተመዘገቡት የሞት መጠኖች ከፍተኛውን ነጥብ አስመዝግበዋል።
ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ላይ ከኒጀር፣ ከማሊ፣ ከቡርኪናፋሶ፣ ከአይቮሪ ኮስት እና ከጋና የተውጣጡ 10 የምዕራብ አፍሪካ የካቶሊኮች እና የሙስሊም ሃይማኖቶት መሪዎች የልዑካን ቡድን ከአሜሪካው የሕግ አውጭዎች ጋር በመገናኘት “በሳህል ክልል እያሽቆለቆለ ስለመጣው የሰብአዊ እና የጸጥታ ሁኔታን” አስመልክቶ እንደተወያዩ የአሜሪካ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ የሰብአዊ ዕርዳታ አካል የሆነው ‘የካቶሊክ የእርዳታ አገልግሎት’ (ሲ.አር.ኤስ.) ዘግቦ ነበር።