ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የካቲት 2011 ዓ.ም. የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶችን ሲጎበኙ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የካቲት 2011 ዓ.ም. የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶችን ሲጎበኙ  (ANSA)

ብጹእ አቡነ ማርቲኔሊ የር. ሊ. ጳ. ፍራንቺስኮስን 5ኛ ዓመት የአቡ ዳቢን ጉብኝት አስታወሱ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አረብ ባሕረ ገብ መሬት ሐዋርያዊ ጉዞ በማድረግ፥ በአቡ ዳቢ ታሪካዊ ጉብኝት አድርገው የሰብዓዊ ወንድማማችነት ሰነድ ላይ ከፈረሙ ከአምስት ዓመታት በኋላ፥ የደቡብ አረቢያ ሐዋርያዊት አስተዳደር የሆኑት ብጹእ አቡነ ፓውሎ ማርቲኔሊ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱ 'ለመንፈሳዊ ነጋዲያን ስደተኞች ቤተክርስቲያን' ስላላቸው ቅርበት እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ ብለዋል።

 አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ከአምስት ዓመታት በኋላ የደቡቡ አረቢያ ሐዋርያዊ አገልግሎት መሪ የሆኑት ብጹእ አቡነ ፓኦሎ ማርቲኔሊ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ወደ ተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ያደረጉት ጉብኝት ትልቅ ትርጉም እንዳለው በማስታወስ፥ ብጹእነታቸው ወደ አረቢያ ባሕረ ገብ መሬት ስላደረጉት የመጀመሪያ ጉብኝት እና ለባሕረ ገቡ አከባቢ ላሉ ምእመናን ያደረግትን የመጀመሪያውን ጳጳሳዊ መስዋዕተ ቅዳሴ በማስመልከት በአጽንዖት ተናግረዋል።

“ትንቢታዊ ሰነድ” ብለው የጠሩትን፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ እና የአል አዝሃሩ ታላቅ ኢማም የሆኑት አህመድ አል ጣዬብ በጋራ በመሆን የካቲት 12 ቀን 2011 ዓ.ም. የፈረሙትን የሰው ልጅ ወንድማማችነት እና አብሮ መኖርን የሚያሳየውን ሰነድ አስፈላጊነትን በማሳየት፥ ይህ ሰነድ “በሃይማኖቶች መካከል ወደፊት ለሚደረጉት መልካም ግንኙነቶች የማዕዘን ድንጋይ ሆኖ ያገለግላል ብለዋል።

በሃይማኖቶች መሃል ለሚደረግ ውይይት ወሳኝ ጥረት

ብጹእ አቡነ ማርቲኔሊ በመልእክታቸው “ይህ ሰነድ ለሁሉም እንዲዳረስ እና እንደገና እንድታነቡት እጋብዛችኋለሁ” በማለት፥ የተለያየ ሃይማኖት ያላቸው ሰዎች መካከል ላለው የግንኙነት ታሪክ አዲስ ምዕራፍ ሆኖ፥ በክርስቲያናዊ ምሥረታ ውስጥ ጥቅም ላይ እንዲውል ሐሳብ አቅርበዋል።

አቡነ ማርቲኔሊ በማከልም እንደተናገሩት “ትምህርት የበለጠ ሰብአዊነት ያለው፣ በጋራ አብሮ የሚኖር ማህበረሰብ ለመፍጠር ቀዳሚው መንገድ ነው። እነዚህን ወሳኝ እሴቶች ለተሻለ ማህበረሰብና ለጋራ ጥቅም ይሆን ዘንድ ለአዲሱ ትውልድ ማስተላለፍ አለብን” ብለዋል።

ከግማሽ አስርት ዓመታት በኋላ ብጹእ አቡነ ማርቲኔሊ፥ ሃዋሪያዊ አስተዳደራቸው እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ ‘በጥልቀት የተዳሰሱበትን ልዩ ክስተቶች’ በማስታወስ፥ “በሃይማኖቶች መካከል ውይይት ለማድረግ ወሳኝ ተነሳሽነት አምጥተዋል” ካሉ በኋላ፥ “የእነዚያ ቀናት ትውስታ አሁንም ልባችንን በአመስጋኝነት ይሞላል፥ እንዲሁም ለቤተክርስቲያን እና ለመላው ዓለም ላለን ጥልቅ የሃላፊነት ስሜት ያነቃቃናል” ብለዋል።

በአረቡ ባሕረ ገብ መሬት የመጀመሪያ የሆነው ጳጳሳዊ ጉብኝት እና ጳጳሳዊ ቅዳሴ

ብጹእ አቡነ ማርቲኔሊ “የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ወደ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናችን መምጣት፥ እራሳችንን እንደ አንድ የክርስቶስ ቤተክርስቲያን አካል እንድንገነዘብ እና በአረብ ባሕረ ገብ መሬት አውድ ውስጥ ትሑት እና ታማኝ ክርስቲያናዊ ምስክርነት ለመስጠት ቃል ኪዳናችንን የምናድስበት አጋጣሚ ነበር” ሲሉ በአጽንዖት ተናግረዋል።

የካቲት 12 ቀን 2011 ዓ.ም. በዛይድ ስፖርት ከተማ፥ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የተካሄደው መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተሳተፉት ሰዎች የነበራቸውን ጥልቅ የደስታ ስሜትን ወደ ኋላ በማስታወስ ገልፀዋል።

ብጹእ አቡነ ማርቲኔሊ፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ “የቤተ ክርስቲያናችንን ልዩ ባሕርይ ይገነዘባሉ” ካሉ በኋላ፥ ቤተክርስቲያኒቱ ከተለያዩ መቶ ሃገራት ባህሎች፣ ቋንቋዎች፣ ወጎች እና ሥርዓቶች የመጡ ምዕመናን የተዋቀረች መሆኗን አስረድተዋል። በማከልም “ለማሳካት የተጠራንበት ቅላፄ ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለመላው ቤተክርስቲያንም ጭምር ሃላፊነት አለብን” ብለዋል።

የመንፈሳዊ ነጋዲያን ስደተኞች ቤተ ክርስቲያን

“በልዩነት ውስጥ አንድነትን ማጣጣም የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ተቀዳሚ ተግባር ነው” ያሉት ሃዋሪያዊ ጳጳሱ፥ “እኛ የስደተኞች ቤተክርስቲያን ነን፣ እኛ የመንፈሳዊ ነጋዲያን ቤተክርስቲያን ነን ፤ ስለዚህ ስጦታዎቻችንን፣ ተሰጥኦዎቻችንን፣ ባህሎቻችንን እና ትሁፊቶቻችንን በማካፈል እርስ በርሳችን ለማበልጸግ ልዩ እድል አለን” ካሉ በኋላ፥ ‘ቤተክርስትያን እና ዓለም’ ብዝሃነት ችግር ወይም እንቅፋት ሳይሆን ለሁሉም የሚጠቅም፥ ከእግዚአብሔር የሚገኝ ባለጠግነት መሆኑን በውስጣችን ማየት አለባቸው” ብለዋል።

የሰብዓዊ ወንድማማችነት ሰነድ እና የአብርሀም ቤተሰብ መኖሪያ

በመጨረሻም ብጹእ አቡነ ማርቲኔሊ እንደገለጹት፥ በሰብዓዊ ወንድማማችነት ላይ ያለው ሰነድ ባለፈው ዓመት የካቲት 9 ላይ የተመረቀውን እና ሶስት የአምልኮ ቦታዎችን ማለትም መስጊድ፣ ምኩራብ እና የካቶሊክ ቤተክርስትያን አንድ ላይ የሚያጣምረውን ‘የአብርሃም ቤተሰብ መኖሪያ’ መጀመርን ያነሳሳ መሆኑን አስታውሰዋል።

በአብርሃም ቤተሰብ መኖሪያ የሚገኘው ቤተክርስቲያን፥ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን፥ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ያበረከቱት ስጦታ እንደሆነ እና ለአሲሲው ቅዱስ ፍራንቺስኮ መታሰቢያ የተሰጠ ነው ተብሏል።

“በእርግጠኝነት ሃሳቡን የምንደግፈው የአብረሃም ቤተሰብ መኖሪያ ቤት በሚያፈልቃቸው ውጥኖች ላይ ምዕመኖቻችን እንዲሳተፉ በድጋሚ እጋብዛለሁ” ካሉ በኋላ፥ “ከተለያዩ እምነት ካላቸው ሰዎች ጋር በጋራ መመላለስ፣ ለሰላም መስራት እና የበለጠ ወንድማማችነትን ማስፈን እንደሚቻል ለዓለም ጥሪያችንን ማሰማት እንፈልጋለን” ብለዋል።

ብጹእ አቡነ ማርቲኔሊ ሲያጠቃልሉ ለቅዱስ አባታችን ያላቸውን ታላቅ ፍቅር እና ‘ስለ ውድ አስተምህሮአቸው እና ለአባትነታቸው’ ያላቸውን ምስጋና በመግለጽ፥ ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ዘወትር ጸሎት እንደሚያደርጉ ከልብ አረጋግጠዋል።
 

05 February 2024, 13:12