በፊሊፒንስ የሚገኙ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ውቅያኖሶች ጥበቃ እንዲደረግላቸው ጠየቁ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በፊሊፒንስ የሳን ካርሎስ ሀገረ ስብከት ጳጳስ አቡነ ጄራርዶ አልሚናዛ በፊሊፒንስ ሚንዶሮ ደሴት የባሕር ዳርቻ የደረሰው የነዳጅ ዘይት መፍሰስ አደጋ በሺዎች የሚቆጠሩ የአካባቢው ዓሣ አጥማጆች ሕይወት ያናጋ እና የአካባቢ ውድመት ያስከተለ በመሆኑ ለተጎጂዎቹ ፍትህ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
አደጋው የተከሰተበትን የመጀመሪያ ዓመት ያስታወሱት አቡነ አልሚናዛ፥ በፊሊፒንስ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ሥር የ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” መርሃ ግብር ከፍተኛ አስተባባሪ በመሆን ከሌሎች መሪዎች ጋር ሆነው የተጎዱትን ለመርዳት እና ይህን መሰል አደጋ እንደገና እንዳይከሰት ለማድረግ ርብርብ እንዲደረግ ጠይቀዋል።
የውቅያኖሶች ብዝሃ ሕይወትን ከጉዳት መጠበቅ
በቨርዴ ደሴት መተላለፊያ ዙሪያ ያሉ የበካይ ኢንዱስትሪዎች መስፋፋት ለመገደብ እና የተፈጥሮ ሃብትን ሕልውና በሚያስከብረው የፊሊፒንስ ሕግ መሠረት ደኅንነቱ የተጠበቀ የባሕር ገጽታን ለማስተዋወቅ ጥረት እየተደረገ መሆኑ ታውቋል። በፊሊፒንስ የ “ካሪታስ” ካቶሊካዊ የፍቅር ሥራ ድርጅት የቀድሞ ዳይሬክተር አባ ኤድዊን ጋሪጌዝ በዚሁ አካባቢ የሚገኝ ብዝሃ ሕይወትን ከጉዳት ለመጠበቅ የሚሠሩ የአካባቢ እና ብሔራዊ ማኅበራት እና ማኅበረሰቦች ቡድን ቃል አቀባይ ሲሆኑ፥ የባሕር ዳርቻ የዓሣ አጥማጆች ህልውናም በአካባቢው የብዝሃ ሕይወት ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ታውቋል።
“የአማዞን ውቅያኖስ” ተብሎ በሚታወቀው በዚሁ አካባቢው 900,000 ሊትር የኢንዱስትሪ ዘይት የጫነ መርከብ የካቲት 22/2016 ዓ. ም. ሰጥሞ ይዘቱ በመፍሰሱ በአካባቢው ከፍተኛ አደጋ መከሰቱ ይታወሳል።
አባ ጋሪጌዝ ፊደስ ከተሰኘ የዜና ወኪል ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ “በአካባቢው ያለው የውሃ ጥራት የተቀመጠውን የውሃ ጥራት መስፈርትን አያሟላም” ሲሉ ገልጸው፥ አስከፊው ተጽኖ አሁንም ጤናን አደጋ ላይ ከመጣል በተጨማሪ በአካባቢው የዓሣ ምርት ኢንዱስትሪ እና ኢኮኖሚ ላይ ከባድ አደጋ ማስከተሉን አስረድተዋል። ጊዜው ከመሄዱ በፊት የብዝሃ ሕይወትን ከጉዳት ለመጠበቅ እና ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ የዓሣ አስጋሪ ማኅበረሰቦችን ለመርዳት በአካባቢው ኦፊሴላዊ የሕግ ጥበቃ እንዲደረግላቸው ጥሪ አቅርበዋል።
የፊሊፒንስ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለአደጋው ተጠያቂ የሆኑት በሙሉ ሃላፊነትን እንዲወስዱ እና በዓሣ አጥማጅ ማኅበረሰቦች ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት በትክክል ያገናዘበ በቂ እና ወቅታዊ ካሳ እንዲከፍሉ ጠይቀዋል።
የአካባቢው ማኅበረሰቦች በአካባቢው ሊደረጉ የታቀዱ የማዕድን ቁፋሮ ሥራዎችን እና የተፈጥሮ ጋዝ ማጠራቀሚያዎች ግንባታን በተመለከተ ሌላ ስጋት እንዳይፈጥሩ አስጠንቅቀዋል። የ "ውዳሴ ላንተ ይሁን" መርሃ ግብር መሪዎች የፊሊፒንስ የመንግሥት ባለስልጣናት እነዚህን ፕሮጀክቶች እንደገና በማጤን ቅድሚያ ለሚሰጣቸው የተፈጥሮ ሃብቶች እና የአካባቢው ተወላጆች ጥበቃን እንዲያመቻቹላቸው ጠይቀዋል።
በሰዎች አንድነት የተገኘ ተስፋ
በተመሳሳይም ፊደስ የዜና ወኪል እንደዘገበው፥ አደጋውን ለመቋቋም የተደረጉ አንዳንድ አወንታዊ ውጤቶችን ገልጾ፥ የአካባቢው ማኅበረሰቦች ለተጎጂዎች ዕርዳታ ማድረጋቸውን እና አጋርነታቸውን ማሳየታቸውን ከፊሊፒንስ ብጹዓን ጳጳሳት ያገኘውን መረጃ በመጥቀስ ተናግሯል።