የኮንጎ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ለምስራቁ የሃገሪቱ ክፍል ሰላም እንዲመጣ እንጸልያለን አሉ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የሚገኙ ካቶሊኮች በሀገሪቱ ምስራቃዊ ክፍል በርካቶችን ለሞት የዳረገው የአማጽያን ጥቃት እንዲቆም እና ሰላም እንዲሰፍን ጸሎት እያቀረቡ እንደሆነ ተነግሯል።
ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ ወደ 6 ሚሊዮን የሚጠጉ ንፁሀን ዜጎች በአማፂያን እና በአሸባሪ ቡድኖች በማያባራ ሁከት ህይወታቸውን አጥተዋል።
ከየካቲት 10/2016 ዓ.ም. ጀምሮ በሃገሪቷ በሚገኙ የካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት የሚደረጉ ሥርዓተ ቅድሴዎች ፍፃሜ ላይ ለተከሰተው የሰላም መደፍረስ ጸሎት እንዲደረግ ተወስኗል።
የዚህ የጸሎት መርሃ ግብር ውጥን በኮንጎ ብሔራዊ የጳጳሳት ጉባኤ የሚመራ ሲሆን፥ ይሄም የካቶሊክ ጳጳሳት ለሰላም ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳያል ተብሏል።
የኪንሻሳ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ፍሪዶሊን አምቦንጎ መጪው ቅዳሜ፣ የካቲት 16 በዋና ከተማዋ በሚገኘው የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ካቴድራል ለታላላቅ ሃይቆች ባለቤት ለሆነው ክልል ‘ሰላምና ፀጥታ’ ለመጸለይ ሥርዓተ ቅዳሴውን እንደሚመሩት ለማወቅ ተችሏል።
በቅዳሴው ወቅት፣ ካርዲናል አምቦንጎ “የግፉ ሰለባ ለሆኑት” እና ለበርካታ አስርት ዓመታት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት በቀጠፈው የጸጥታ እጦት ሲሰቃዩ የነበሩትን የኮንጎ ዜጎችን ሁሉ እግዚአብሔር እንዲያጽናናቸው ይጸልያሉ ተብሎም ይጠባቃል።
ጎማ 'የጥይት ሳጥን'
የሰሜን ኪቩ ግዛት ዋና ከተማ በሆነችው ጎማ ዙሪያ ባለው አካባቢ ‘የማርች 23 ወይም (M23) ንቅናቄ’ን ጨምሮ በታጣቂ ቡድኖች መካከል ከፍተኛ ግጭት ተፈጥሯል።
ጎማ ሃገሪቷን ከሩዋንዳ ከሚያዋስነው ድንበር አጠገብ ያለች ሲሆን፥ ድንበር በማቋረጥ ከሩዋንዳዋ ጊሴኒ ከተማ ጋር ከፍተኛ የንግድ ልውውጥ እንደሚደረግም ተገልጿል።
የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ባለስልጣናት እንደሚሉት የሩዋንዳ መንግስት ‘ኤም 23’ የተባለውን አማፂ ቡድንን ይደግፋሉ ብለው ተደጋጋሚ ክስ ቢያቀርቡም፥ ሩዋንዳ ለቀረበባት ክስ እስካሁን ምንም አይነት ምላሽ አልሰጠችም።
የጎማ ከተማ ጳጳስ የሆኑት ብጹእ አቡነ ዊሊ ንጉምቢ ንጌሌ እንዳሉት “የኤም 23 ጦርነትን ተከትሎ፥ የጎማ ከተማ ከመጠን በላይ የወታደራዊ ሃይል የበዛባት ከተማ እንደሆነች እና በተለይ በተለምዶ "ዋዛሌንዶ" በመባል የሚታወቁት ታጣቂ ቡድኖች በብዛት እንደሚገኙ በመግለጽ፥ “ይህንን ጉዳይ በጥንቃቄ ካልያዝነው፥ የጎማ ከተማ በማንኛውም ጊዜ ሊነሳ በሚችል የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ልትገባ ትችላለች” በማለት አስጠንቅቀዋል።
የሰብአዊ አደጋ ስጋት
ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ነዋሪዎች ያሏት የጎማ ከተማ፣ ለዓመታት በዘለቀው ግጭት ምክንያት ከተለያዩ አከባቢዎች የተፈናቀሉ 850,000 የሚጠጉ ሰዎችን እያስተናገደች ትገኛለች።
ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ የኮንጐ መንግስት በከተማዋ ዙሪያ ባቋቋማቸው ሰባት ካምፖች ውስጥ በርካቶች ተጠልለው እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል።
ብጹእ አቡነ ንጉምቢ እንደተናገሩት የሃገር ውስጥ ተፈናቃዮች “በሩዋንዳ የሚደገፈው የ ኤም 23 ንቅናቄ ታጋቾች መሆናቸውን በርካታ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ሌሎች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኤጀንሲዎች ዘግበዋል” በማለት ገልጸዋል።
ጳጳሱ በማከልም ከተማዋ የዐብይ ጾምን በጀመረች ማግስት “የኤም 23 ወታደሮች ከጎማ በስተ ምዕራብ 30 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ወደምትገኘው ሳኬ ከተማ ከገቡ በኋላ ጎማ ሙሉ በሙሉ ውጥረት ውስጥ ገብታለች” ብለዋል።
የሳኬ ከተማ ሶስት ዋና ዋና የኢኮኖሚ መስመር የሆኑ መስቀለኛ መንገዶችን ያሏት ስትራቴጂካዊ ቦታ ስትሆን፥ በበአካባቢው በበላይነት እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው የኤም 23 ንቅናቄ፥ የአቅርቦት ፍሰት ላይ አደጋ ሊጥሉ እንደሚችሉ እየተነገረ ይገኛል።
በአሁኑ ሰዓት ይላሉ ብጹእ አቡነ ንጉምቢ፥ “በጎማ ረሃብ ሊከሰት እንደሚችል እና ሰዎች በምግብ እጦት መሞት ሊጀምሩ የሚችሉበት ትክክለኛ ስጋት አለ” በማለት አስጠንቅቀዋል።
ኤም 23 ሁሉንም የአቅርቦት መንገዶችን ሊዘጋ እንደሚችል ጠቁመው፥ ይህ እርምጃው ደግሞ ሰዎች በረሃብ እንዲሞቱ ያደርጋል ብለዋል።
የጎማ ከተማ ጳጳስ በመጨረሻም “ያኔ ፤የሰብአዊ አደጋ በሚከሰትበት ጊዜ ያለ ምንም እርዳታ እንመለከተዋለን” በማለት በጊዜ የሰላም ጥረት እንዲደረግ አሳስበዋል።