ፈልግ

የየካቲት 3/2016 ዓ.ም 4ኛ ሳምንት የእለቱ ንባባት እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የየካቲት 3/2016 ዓ.ም 4ኛ ሳምንት የእለቱ ንባባት እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ  (©khanchit - stock.adobe.com)

የየካቲት 3/2016 ዓ.ም 4ኛ ሳምንት የእለቱ ንባባት እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

በሚያፈቅረን በእግዚአብሔር ላይ ያለንን እምነት ለሌሎች ለመመስከር እንውጣ!

የእለቱ ንባባት

1.    ኦሪት ዘዳግም 18፡15-20

2.    መዝሙር 94

3.    1 ቆሮንጦስ 7፡32-35

4.    ማርቆስ 1፡21-28

 

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ከዚያም ወደ ቅፍርናሆም ሄዱ፤ ኢየሱስም ወዲያው በሰንበት ቀን ወደ ምኵራብ ገብቶ ማስተማር ጀመረ። እንደ ጸሐፍት ሳይሆን፣ እንደ ባለ ሥልጣን በማስተማሩ ሕዝቡ በትምህርቱ ተገረሙ። በዚያን ጊዜ በምኵራባቸው ውስጥ የነበረ ርኩስ መንፈስ ያደረበት አንድ ሰው እንዲህ በማለት ጮኸ፤ “የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፤ ከእኛ ምን ትሻለህ? ልታጠፋን መጣህን? እኔ ማን እንደ ሆንህ ዐውቃለሁ፤ አንተ የእግዚአብሔር ቅዱስ ነህ!”

ኢየሱስም፣ “ጸጥ በል፤ ከእርሱም ውጣ!” ብሎ ገሠጸው። ርኩሱም መንፈስ ሰውየውን በኀይል ካንፈራገጠው በኋላ እየጮኸ ወጣ። ሕዝቡ በሙሉ በመገረም፣ “ይህ ነገር ምንድን ነው? ሥልጣን ያለው አዲስ ትምህርት መሆኑ ነው! ርኩሳን መናፍስትን እንኳ ያዝዛል፤ እነርሱም ይታዘዙለታል!” እያሉ እርስ በርስ ተጠያየቁ። ወዲያውም ዝናው በገሊላ ዙሪያ ባሉ ስፍራዎች ሁሉ ተዳረሰ።

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶች፣ እንደምን አረፈዳችሁ! ዛሬ ባቀረብነው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ የተነበበው ቅዱስ ወንጌል ኢየሱስ ክርስቶስ በአገልግሎት ላይ መሆኑን ያሳየናል። በእርግጥም ኢየሱስ ስብከቱን እንደጨረሰ ከምኩራብ ከወጣ በኋላ ወደ ስምዖን ጴጥሮስ ቤት ሄዶ አማቱን ፈውሷል። በመሸም ጊዜም ወደ ከተማይቱ በሮች በመሄድ በዚያም ብዙ ድውያንንና በሽተኞችን አግኝቶ ፈውሷቸዋል። በማለዳም ተነስቶ ለጸሎት ወጥ ወዳለ ሥፍራ ሄደ። እንደገናም ወደ ገሊላ ማዶ ሄደ (ማር. 1፡29-39)። ስለ እግዚአብሔር አብ ጠቃሚ ነገር የሚነግረንን እና በእምነታችን እንድናሰላስል የሚያደርገንን፥ ቀጣይነት ያለውን የኢየሱስ ክርስቶስ እንቅስቃሴ እንመልከት።

ኢየሱስ ክርስቶስ በኃጢአት ወደ ቆሰለው የሰው ልጅ ዘንድ በመሄድ እግዚአብሔር አብን ያሳየናል። ምናልባት በውስጣችን ከእምነት የራቅን፣ ለእግዚአብሔርም ደንታ እንደሌለን ሊሰማን ይችላል። በተቃራኒው ቅዱስ ወንጌል እንደሚናገረን፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በምኩራብ ካስተማረ በኋላ የሰበከው ቃል ሰዎችን እንዲደርሳችው፥ እንዲዳስሳቸው እና እንዲፈውሳቸው ለማድረግ መውጣቱን እንመለከታለን። ይህን በማድረጉ እግዚአብሔር ከእኛ የራቀ ሳይሆን ነገር ግን ከላይ ሆኖ የሚናገረን አምላክ እንደሆነ ገልጦልናል። እርሱ በፍቅር የተሞላ አባት፥ ራሱን ወደ እኛ የሚያቀርብ፣ የሚጎበኘን፣ የሚያድነን እና ነጻ የሚያወጣን፣ ከማንኛውም የአካል እና የመንፈስ ህመም የሚፈውሰን አባት ነው። እግዚአብሔር ለእኛ ዘወትር ቅርብ ነው። እርሱ ለእኛ ያለን አመለካከት በሦስት ቃላት ሊገለጽ ይችላል። ቅርብ፣ ርኅሩኅ እና ለጋስ በሚሉት ቃላት መግለጽ እንችላለን። እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ሊሆን፣ ርኅራኄውን ሊገልጥልን እና ይቅር ሊለን ቀረበን። እርሱ ለእኛ ያለንን የመቅረብ፣ የርኅራሄ እና የለጋስነት አመለካከት መርሳት የለብንም።

ኢየሱስ ክርስቶስ ሳያቋርጥ ከቦታ ቦታ የሚያደርገው ጉዞ ራሳችንን እንድንጠይቅ ያደርገናል። እግዚአብሔር የምህረት አባት እንደሆነ እናውቃለን? ወይንስ ለእኛ ግድ የሌለው የሩቅ አምላክ እንደሆነ እንመሰክራለን? በውስጣችን ያለው እምነት የማያቋርጥ ጉዞን እንድንጓዝ ያደርገናል ወይንስ ተጽናንተን እንድንረጋጋ ያደርገናል? ጸሎታችን የውስጥ ሰላም ለማግኘት ነው ወይንስ የምንሰማው እና የምንሰብከው ቃል የእግዚአብሔርን አጽናኝነት በመመስከር እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ እኛም ወደ ሌሎች እንድንሄድ ያደርገናል? እነዚህን ጥያቄዎች እራሳችንን ብንጠይቅ መልካም ነው።

እንግዲያውስ የኢየሱስ ክርስቶስን ጉዞ በመመልከት ማከናወን ያለብን የመጀመሪያው መንፈሳዊ ተግባራችን በቅዱስ ቃሉ ራሱን በገለጠልን በኢየሱስ ክርስቶስ ዕለት በዕለት በመለወጥ፥ እግዚአብሔር አብ የፍቅር እና የርህራሄ አባት መሆኑን እናስተውል። እግዚአብሔር አብ ለእኛ ቅርባችን፣ ርኅሩህ እና ለጋስ አምላክ ነው። የእርሱን እውነተኛ መልክ ስናውቅ እምነታችን ይጎለብታል። ከእንግዲህ ወዲያ በቤተ ክርስቲያን የቅዱሳት ዕቃዎች ማስቀመጫ ክፍሎች ወይም የቃል ክርስቲያኖች ብቻ ሆነን አንቀርም። ይልቁንም የእግዚአብሔርን ተስፋ እና ፈውስ አብሳሪዎች እንድንሆን የተጠራን መሆናችን ይሰማናል።

የእግዚአብሔርን ቅርብነት፣ ርኅራሄውን እና ለጋስነቱን የምንመሰክር ሰዎች እንድንሆን በክርስትና ጉዞአችን ከእኛ ጋር ያለች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ታግዘን።” 

ምንጭ፡ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጥር 19/2016 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ካደረጉት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የተወሰደ።

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

 

 

10 February 2024, 14:44