ፈልግ

በሄይቲ የተቀሰቀሰው የጸረ መንግሥት አመጽ በሄይቲ የተቀሰቀሰው የጸረ መንግሥት አመጽ   (ANSA)

የሄይቲ ካቶሊክ ጳጳሳት፥ ጠቅላይ ሚኒስትር ሄንሪ ስልጣናቸውን እንዲለቁ ሃሳብ አቀረቡ

የሄይቲ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጠቅላይ ሚኒስትር አርዬል ሄንሪ በአገሪቱ በተቀሰቀሰው ሁከት እና ተቃውሞ የተነሳ ስልጣን በመልቀቅ አገሪቱን የሚጠቅም ጥበብ የተሞላበት ውሳኔ እንዲያደርጉ ጠይቀው፥ የሄይቲ ሕዝብም አመጽ እንዲያቆም አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የሄይቲ ካቶሊክ ጳጳሳት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በሐምሌ ወር 2021 ዓ. ም. ፕሬዝደንት ጆቬኔል ሞይስ ከተገደሉ በኋላ በስልጣን ላይ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኤሪዬል ሄንሪ ከስልጣን እንዲወርዱ በመጠየቅ በተቀሰቀሰው ሁከት ላይ ያላቸውን ጥልቅ ስጋት ገልጸዋል። በሁከቱ እስካሁን አምስት ሰዎች ሞተው በርካቶች መቁሰላቸው ሲነገር፥ በወንበዴዎች በተመሰቃቀለች ሄይቲ ውስጥ የተቀሰቀሰው የቅርብ ጊዜ ብጥብጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሄንሪ ከስልጣን እንዲወርዱ በማለት ጠይቀዋል።

በጥር 29/2016 ዓ. ም. ምርጫ እንደሚካሄድ ይጠበቅ ነበር

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በታህሳስ 2022 ዓ. ም. በተደረሰው የፖለቲካ ስምምነት መሠረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥር 29/2016 ዓ. ም. ምርጫ ማካሄድ የነበረባቸው ቢሆንም የብሔራዊ አንድነት መንግሥት ለመመስረት በሚል ምክንያት በስልጣን ላይ መቆየትን መርጠዋል። ይህ ቀን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 1986 ዓ. ም. የዱቫሊየሮች አምባገነናዊ ሥርዓት ያበቃበት ዓመታዊ በዓል የሚከበርበት በመሆኑ በሄይቲ ውስጥ ከፍተኛ ክብር የሚሰጠው እንደሆነ ይታወቃል።

ከዓለም ድሃ አገሮች አንዷ የሆነችው ሄይቲ ለዓመታት በብጥብጥ ውስጥ የምትገኝ ስትሆን፥ የታጠቁ ባንዳዎች ዋና ከተማዋን ጨምሮ ሰፊ የደሴቲቱን ክፍል በመቆጣጠር ጭካኔ የተሞላበት ጥቃት እየፈጸሙ ይገኛሉ። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2021 ዓ. ም. በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሞይስ ላይ የተፈጸመው ግድያ አገሪቱን የበለጠ ትርምስ ውስጥ እንደከተታት እና ከ 2016 ዓ. ም. ጀምሮ ምርጫዎች መካሄዳቸው ይታወሳል።የሄይቲ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ሐሙስ ጥር 30/2016 ዓ. ም. በሰጡት ጠንከር ያለ መግለጫ የአገሪቱ ባለሥልጣናት የሄይቲን ሕዝብ ስቃይ በአስቸኳይ እንዲያስቆሙ አሳስበዋል።

"ባለፉት ሦስት ዓመታት በተፈጸሙ ግድያዎች፣ አፈና እና አስገድዶ መድፈር ብዙ ደም እና እንባ ፈስሷል" ሲሉ ጳጳሳቱ በመግለጫቸው ገልጸዋል። "እናት አገራችን አደጋ ላይ ነች" ያሉት ብጹዓን ጳጳሳቱ ለጠቅላይ ሚኒስትር ሄንሪ በቀጥታ ባስተላለፉት መልዕክት፥ የጉዳዩን አሳሳቢነት እንዲገነዘቡ እና ለመላው አገሪቱ ጥቅም ሲባል ከሥልጣን ወርደው ጥበብ የተመላበት ውሳኔን እንዲወስዱ አሳስበዋል።

ጥቃትን መቃወም እንደሚገባ

የሄይቲ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳቱ “በቅርብ ጊዜ በተከሰቱት ክስተቶች ለተጎዱት ቤተሰቦች ያላቸውን ቅርበት እና ልባዊ ሐዘን ገልጸው፥ ሄይቲውያን አመጽን እና ጥቃትን በመቃወም ጉልበታቸውን በማስተባበር ለሄይቲ የተሻለ የወደፊት ሕይወት ለመገንባት እንዲያተኩሩ አሳስበዋል። "ክብራችንን በሚረግጥ፣ ሰብዓዊነታችንን በሚያበላሽ እና የሀገራችንን ገጽታ በሚያጎድፍ የአመፅ እና የወንድማማቾች ትግል ወጥመድ ውስጥ እንዳትገቡ" በማለት መክረው፥ ያለንን ኃይል ሁሉ በማንቀሳቀስ እራሳችንን በጋራ እና በቁርጠኝነት፣ ያለ ግፍ ሁላችንም ወደምንፈልጋት አዲሷ ሄይቲ የሚያደርሰንን መንገድ እንገንባ!" ብለዋል።

የሄይቲ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት በኤኮኖሚ ቀውስ እና በፖለቲካዊ አለመረጋጋት ለዓመታት የተሰቃየች እና በወሮበሎች ጥቃት እና አፈና ስትታመስ የቆየችው የሄይቲ የደህንነት ሁኔታ ወደ ነበረበት እንዲመለስ በማለት ደጋግመው ተማጽነዋል።ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሁድ ጥር 12/2016 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተገኙት ምዕመናን ጋር የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ባቀረቡበት ወቅት ከጳጳሳቱ ጎን መሆናቸውን ገልጸው፥ ከዚያ በኋላም በፖርት-አው ፕሪስ ውስጥ የታፈኑት ስድስት መነኮሳት ከእስር መለቀቃቸው ይታወሳል።

ይህ በንዲህ እንዳለ የወቅቱን ብጥብጥ ተከትሎ ከሄይቲ ጋር በድንበር የምትዋሰን ዶሚኒካን ሪፑብሊክ ረቡዕ ጥር 29/2016 ዓ. ም. ባወጣችው መግለጫ በተጠንቀቅ እንደምትገኝ አስታውቃ ከሄይቲ ጋር በሚያዋስናት ድንበር አካባቢ የሚገኘውን የጸጥታ ኃይል ማጠናከሯን ገልጻለች።

 

10 February 2024, 16:31