ፈልግ

ሰዎች ኬራላ ግዛት ውስጥ በምትገኘው በቲሩቫናንታፑራም ከተማ ውስጥ መጓጓዣ እየጠበቁ ሰዎች ኬራላ ግዛት ውስጥ በምትገኘው በቲሩቫናንታፑራም ከተማ ውስጥ መጓጓዣ እየጠበቁ   (AFP or licensors)

500 ሺህ የሚሆኑ የህንድ ካቶሊኮች አስከፊ የኑሮ ሁኔታን በማስመልከት የፊርማ ማሰባሰብ ዘመቻ አደረጉ

የህንድ ግዛት በሆነችው ኬራላ በካቶሊክ ኮንግረስ የተዘጋጀው እና “የህልውና ጉዞ” የሚል መጠሪያ የተሰጠው የፊርማ ማሰባሰብ ዘመቻ፥ ከዱር እንስሳት ጥቃት እስከ ስራ አጥነት የመሳሰሉ በአካባቢው ህዝብ ላይ መጥፎ የህይወት ተጽዕኖ የሚያሳድሩ በርካታ ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንደሚሰጥ ተነግሯል።

 አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በደቡብ ምዕራብ ህንድ፥ ኬራላ ግዛት ውስጥ የሚገኙ ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ ካቶሊኮች፥ መንግስት በኑሮ ሁኔታዎች ላይ የማሻሻያ እርምጃ እንዲወስድ የፊርማ ማሰባሰብ ዘመቻ አድርገዋል።

ይህ ‘ዩ ሲ ኤ ኒውስ’ በተባለ የሚድያ ተቋም የተዘገበው የፊርማ ማሰባሰብ ዘመቻ፥ ከኬራላ ከተማ ሳይሮ-ማላባር ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጋር ግንኙነት ካለው የካቶሊክ ምእመናን ማህበር በሆነው በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምክር ቤት የተዘጋጀ እንደሆነም ተገልጿል።

የዕለት ተዕለት ትግል

“የህልውና ጉዞ” በሚል ርዕስ የቀረበው የፊርማ ማሰባሰብ ዘመቻ አዘጋጆች፥ አብዛኛዎቹ ኮሚኒስት በሆኑ ግራ ዘመም ዲሞክራሲያዊ ግንባር የሚመራው የኬራላ ግዛት መንግስት፥ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ህዝቦች ዘርፈ ብዙ የሆኑ ችግሮቻቸውን እንዲፈቱላቸው ነው አቤቱታውን ያቀረቡት።

ከነዚህም ችግሮች ውስጥ፥ የመንግስት የጡረታ አበልን በወቅቱ አለመክፈል፣ ለገበሬዎች በቂ የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ፣ የዱር እንስሳትን ጥቃቶች መከላከል እና በግዛቱ ውስጥ በቂ የስራ ዕድል እንዲኖር ማረጋገጥ የሚሉት ይገኙበታል።

የካቶሊክ ኮንግረስ ፕሬዝዳንት የሆኑት ቢጁ ፓራያኒላም ስለ ጉዳዩ ሲገልጹ “ይህ ግማሽ ሚሊዮን በሚሆኑ ካቶሊኮች የተፈረመው እና የህዝቡን ህይወት ለማሻሻል የቀረቡ ጥያቄዎች ዝርዝር የያዘውን የፊርማ ሰነድ ከፍተኛ ሚኒስተር ለሆኑት አቶ ፒናራይ ቪጃያን ሰጥተናል” ሲሉ ለዩ ሲ ኤ ኒውስ ተናግረዋል።

ዘመቻው የደረሰበትን አስመልክተው ሲናገሩ “ሚኒስትሩ ችግሮቻችን በጣም እንደሚያሳስባቸው እና ጉዳዩንም በትኩረት እንደሚመለከቱ ገልፀውልናል” ብለዋል።

ይሁን እንጂ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን መሪዎች፥ በዱር እንስሳት ጥቃት ርዕሰ ጉዳይ ላይ በክልሉ መንግስት ዋስትና ከተሰጠበት ጊዜ ጀምሮ ሁኔታው እየባሰበት መሄዱን በመግለጽ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

የቅዱስ ቶማስ ክርስቲያኖች

በህንድ ደቡብ-ምእራብ የባህር ጠረፍ ላይ ባለው አነስተኛ መሬት ላይ የምትገኘው ኬራላ፥ ከጥንት ጀምሮ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የክርስቲያኖች መኖሪያ እንደሆነች እና በዚያ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት መነሻቸው ከሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ እንደሚመዘዝ ይነገራል።

ዛሬ ላይ በአከባቢው የሚገኙ ክርስቲያኖች ከአጠቃላይ ሕዝብ 20 በመቶውን እንደሚሸፍኑ እና አብዛኞቹ ደግሞ የሂንዱ እምነት ተከታዮች እንደሆሙ መረጃዎች ያመላክታሉ። እነዚህ ክርስቲያኖች ከሮም ካቶሊክ ጋር ህብረት ካላት የሱ-ጁሪስ የሳይሮ-ማላባር ምስራቃዊ ቤተክርስቲያን አባላት እንደሆኑም ተነግሯል።

የሳይሮ-ማላባር ቤተ ክርስቲያን የጳጳሳት ሲኖዶስ በቅርቡ ባደረጉት ምርጫ፥ የቀድሞ የሻምሻባድ ጳጳስ የሆኑትን ብጹእ አቡነ ራፋኤል ታቲልን እንደ አዲስ መሪ አድርገው መሾማቸው ይታወቃል።
 

08 February 2024, 16:35