ሞዛምቢክ ውስጥ ታጣቂዎች በከፈቱት ጥቃት ሚስዮናውያን ለሽሽት መዳረጋቸው ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የሞዛምቢክ መከላከያ ሠራዊት (ኤፍኤዲኤም) እና የደቡብ አፍሪካ ልማት ማኅበረሰብ (ሳዲሲ) ኃይሎች በመተባበር የተወሰነ መረጋጋት ካመጡት በኋላ በቅርቡ በእስላማዊ መንግሥት (ዳኢሽ) የሚመራው አማፂ ቡድን በሞዛምቢክ ካቦ ዴልጋዶ ግዛት እንደገና ጥቃት ማድረሱ ታውቋል።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2017 (እ.አ.አ) በሰሜናዊው ግዛት የተቀሰቀሰው ዓመጽ ወደ አጎራባች ግዛቶችም የተዛመተ ሲሆን፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ 2024 መጀመሪያ ጀምሮ አዲስ ጥቃት መጨመሩ ተገልጿል።የአካባቢው ምንጮች ለካቶሊክ በጎ አድራጎት ድርጅት (ACN) እንደተናገሩት፥ ጥቃቱ የክርስቲያን ማህበረሰቦችን ጨምሮ ካኅናት፣ መነኮሳት እና ሌሎች የቤተ ክርስቲያን ሠራተኞች በተፈናቃይ ቤተሰቦች ወደተያዙ ከተሞች እንዲሸሹ መገደዳቸውን ገልጸዋል።
የሚሲዮን ቤቶች ወደ አመድ ተለወጠዋል
በቅርቡ በተፈጠረው ጥቃት በፔምባ ሀገረ ስብከት ማዜዜ የሚገኘው የአፍሪካ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን እና ቢሮዎች በየካቲት 4/2016 ዓ. ም. የጠቅላይ ግዛት ዋና ከተማ በሆነችው የወደብ ከተማ ላይ በተፈጸመው የሽብር ጥቃት በእሳት መጋየታቸው ተነግሯል።
የቁምስናው ካኅን ከቤይራ ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከት የሬድዮ ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ጥቃቱ እንደተፈጸመ ማረጋገጣቸውን እና በሰው ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት እንዳልደረሰ መናገራቸውን የካቶሊክ በጎ አድራጎት ድርጅት የአፍሪካ ተወካይ ጽሕፈት ቤት ዘግቧል። ካህኑ በቃለ ምልልሳቸው እንደገለጹት ከእሳት አደጋው ማትረፍ የቻሉት ቅዱስ ቁርባንን እና ይዘው የመጣጧቸው የቅዱስ ቁርባን፣ የጥምቀትና የጋብቻ ምስጢራት መጻሕፍት ብቻ እንደሆኑ ገልጸዋል።
የካቲት 1/2016 ዓ. ም. መኖሪያ ቤቶች እና አብያተ ክርስቲያናት ወድመዋል
የካቶሊክ በጎ አድራጎት ድርጅት የአፍሪካ ቅርንጫፍ በዘገባው፥ የካቲት 1/2016 ዓ. ም. አሸባሪዎች በግዛቲቱ መንደሮች ውስጥ የሚገኙ በርካታ መኖሪያ ቤቶችን እና አብያተ ክርስቲያናትን በእሳት እንዳጋዩዋቸው ተናግሯል። የአካባቢው ምንጮች እንደሚሉት አማፂዎቹ በአብዛኛው አካባቢ በሙስሊሞች እና በክርስቲያኖች መካከል አድሎ ባያደርጉም ነገር ግን በተለይ በክርስቲያን ማኅበረሰቦች ላይ ጥቃት እና ግድያ መፈጸማቸውን ተናግረዋል።
በግጭቱ አንድ ሚሊዮን ሰዎች ተፈናቅለዋል
በሞዛምቢክ የተቀሰቀሰው ግጭት ከ4,000 በላይ ሰዎች ሕይወትን የቀጠፈ ሲሆን እንደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (ዩኤንኤችሲአር) ዘገባ ከሆነ በክልሉ በአንድ ሚሊዮን የሚገመቱ ሰዎች እንደተፈላቀሉ ይህም ከጠቅላላው የአገሪቱ ህዝብ መካከል ሦስት በመቶው እንደሆነና በርካቶችም ከገጠራማው አካባቢ ወደ ተጨናነቁ ከተሞች የሄዱ እንደሆነ ተናግሯል። አንድ ካኅን ለካቶሊክ በጎ አድራጎት ድርጅት እንዳስረዱት፥ ሰዎች የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች በቅርብ ስለሚከታተሏቸው ከካህናት እና ከመነኮሳቱ ጋር ሲሆኑ የበለጠ ደህንነት እንደሚሰማቸው አስረድተዋል።
ከቤተ ክርስቲያን የሚሰጥ ድጋፍ
የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሞዛምቢክ ውስጥ የተፈናቀሉትን እየደገፈች እንዲሁም ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ስታግዝ ቆይታለች። የካቶሊክ በጎ አድራጎት ድርጅት “ኤሲኤን” በሞዛምቢክ የሚያደርገው ድጋፍ ለሽብር ሰለባዎች፣ ለሚሲዮናውያን፣ ለማኅበረሰብ ማዕከላት ግንባታ፣ ለሐዋርያዊ እና የምክር አገልግሎት እንደሚውል ታውቋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሁድ የካቲት 10/2016 ዓ. ም. ባቀረቡት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ወቅት፥ በሞዛምቢክ ውስጥ እንደገና እያገረሸ ባለው ቀውስ ትኩረት በመስጠት “በአካባቢው ሕዝቦች ላይ የሚደርስ ስቃይ ቆሞ ሰላም እንዲሰፍን እንጸልይ” ማለታቸው ይታወሳል።
በ 2023 (እ.አ.አ) ጥቃቱ ቀንሶ ነበር
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2023 ዓ. ም. በሰሜን ሞዛምቢክ ውስጥ አማፂዎች የሚያደርሱት ጥቃት መቀነሱ ዓለም አቀፍ ታዛቢዎችን ተስፋ እንዲኖራቸው አድርጓቸዋል። የሞዛምቢክ መከላከያ ሠራዊት፥ በታህሳስ ወር አጋማሽ በ 90% የካቦ ዴልጋዶ ግዛት ውስጥ የደህንነት ጥበቃ እንደገና መዋቀሩን አስታውቋል።
ነገር ግን በርካታ አዋቂዎች እንደሚሉት፥ እስላማዊ ታጣቂ ቡድን በቀላሉ የሚሸነፍ ሳይሆን ጥቃታቸውን ለጊዜው እንደቀነሱ እና የደቡብ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (SADC) ጦራቸውን ከአካባቢው ማውጣት ሲጀምሩ ጥቃት ለመፈጸም ዝግጁ እንደሆነ አስጠንቅቀዋል።
“ፊደስ” የተሰኘ የቤተ ክርስቲያን የዜና ወኪል የአካባቢውን ነዋሪዎች ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው፥ ታጣቂ ቡድኑ በከፈተው አዲስ ጥቃት ከሕዝቡ ጋር ለመወዳጀት አዲስ ስልት መጠቀሙን ገልጿል። ሰላማዊ ዜጎችን ከመግደል ይልቅ ግብር በማስከፍል ሕይወታቸውን እና ንብረታቸውን ከጉዳት እንደሚጠብቅ፥ ሙስሊሙ ማኅበረሰብም ባለበት እንዲቆይ በማረታታት የዓርብ ዕለት ጸሎታቸውን እንዲሳተፉ መጋበዙን የዜና ወኪሉ አክሎ አስታውቋል።