ፈልግ

የፋጡማ እምቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የፋጡማ እምቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም   (Lazaro Gutierrez fotografo della archidiocesi di Managua )

ማርያም የስብከተ ወንጌል እናት

ቅድስት ድንግል ማርያም ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ሁል ጊዜ በሕዝቡ መካከል ትገኛለች፡፡ እርስዋ መንፈስ ቅዱስ ይመጣ ዘንድ ከደቀ መዛሙርት ጋር አብራ ጸለየች (የሐዋ.1፡14)፤ በመሆኑም በበዓለ ሃምሳ ዕለት የወንጌል ተልእኮ ተጀመረ፡፡ እርስዋ ወንጌልን የምታስተምር የቤተክርስቲያን እናት ናት፤ ያለ እርስዋ የአዲሱን ስብከተ ወንጌል መንፈስ በእውነት መረዳት ከቶ አንችልም፡፡

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ኢየሱስ ለሕዝቡ የሰጠው ስጦታ

ኢየሱስ በመስቀል ላይ የዓለምን ኃጢአትና የእግዚአብሔርን ምሕረት በገዛ ራሱ ሥጋ ላይ በተሸከመ ጊዜ በእግሮቹ ሥር የእናቱና የወዳጁ አጽናኝ መገኘት ተሰማው፡፡ በዚያ ወሳኝ ወቅት፣ አባቱ የሰጠውን ሥራ ሙሉ በሙሉ ከመፈጸሙ በፊት፣ ኢየሱስ ለማርያም ‹‹አንቺ ሴት፣ እነሆ ልጅሽ›› አላት፡፡ ቀጥሎም ውድ ወዳጁን ‹‹እነሆ እናትህ›› አለው (ዮሐ.19፡26-27)፡፡ እነኚህ በሞት አፋፍ ላይ የሚገኘው ኢየሱስ የተናገራቸው ቃላት በዋናነት ለእናቱ ያለውን ፍቅርና ጭንቀት የሚገልጹ አይደሉም፤ ይልቁንም የልዩ አዳኝ ተልእኮን ምስጢር የሚያሳዩ ገላጭ ፎርሙላ ናቸው፡፡ ኢየሱስ እናቱን የእኛም እናት ትሆን ዘንድ ሰጠን፡፡ ይህን ካደረገ በኋላ ብቻ ነው ኢየሱስ ‹‹ሁሉ ነገር ተፈጸመ› ›(ዮሐ.19፡28) ያለው፡፡ በመስቀሉ ሥር፣ አዲሱ ፍጥረት በተፈጠረበት የላቀ ሰዓት፣ ክርሰቶስ ወደ ማርያም መራን፡፡ እኛን ወደ እርስዋ ያመጣን ያለ እናት እንድንጓዝ ስላልፈለገ ነው፤ ሕዝባችንም በዚህ እናታዊ አምሳል ውስጥ የወንጌልን ምስጢሮች ሁሉ ያነባሉ፡፡ ጌታ ቤተክርስቲያንን ያለዚች የሴትነት ምልክት ሊተዋት አልፈለገም፡፡ በታላቅ እምነት ወደዚህ ዓለም ያመጣችው ድንግል ማርያም ‹‹የእግዚአብሔርን ትእዛዛት ከሚጠብቁና የኢየሱስን ምስክር አጥብቀው ከያዙ›› (ራእይ 12፡17) ጋር ትሆናለች፡፡ በድንግል ማርያም፣ በቤተክርስቲያንና በራሱ መንገድ ክርስቶስን በሚያሳውቅ እያንዳንዱ የምእመናን አባል መካከል ያለው የቀረበ ግንኙነት በብፁዕ ይስሐቅ ዘስቴላ ውብ አንደበት እንዲህ ተገልጾአል፡- ‹‹በመንፈስ በተቀሰቀሱ ቅዱሳት መጻሕፍት፣ ስለ ድንግል እናት ስለ ቤተክርስቲያን በአጠቃላይ የተነገረውን ነገር፣ በግል ስለ ድንግል ማርያም እንደተነገረ መረዳት ይቻላል፡፡….. በመሠረቱ እያንዳንዱ ክርስቲያን ደግሞ የእግዚአብሔር ቃል ሙሽራ፣ የክርስቶስ እናት፣ የእርሱም ሴት ልጅና እህት፣ ድንግልና  ፍሬያማ ነው….. ክርስቶስ በድንግል ማርያም ታቦተ ማሕፀን ውስጥ ለዘጠኝ ወር ኖረ፡፡ እስከ ዘመናት ፍጻሜ ድረስ በቤተክርስቲያን የእምነት ታቦት ውስጥ ይኖራል።በእያንዳንዱ ታማኝ ነፍስ ውስጥ ታውቆና ተወድዶ ለዘላለም ይኖራል››፡፡

ድንግል ማርያም የከብቶችን በረት በጨርቅ ለተጠቀለለና በፍቅር ለተሞላ ኢየሱስ መኖሪያ አደረገችው፡፡ እርስዋም ለእርሱ የውዳሴ መዝሙር የምትዘምር የአብ ሴት አገልጋይ ናት፡፡ በሕይወታችን ውስጥ የወይን ጠጅ እንዳይጠፋ የምትጨነቅ ወዳጅ ናት፡፡ ልብዋ በጦር የተወጋ ሴትና የእኛንም ጭንቅ ሁሉ የምታውቅ ናት፡፡ የሁሉም እናት በመሆንዋ በፍትህ እጦት ውጋት ለሚጨነቁ ሕዝቦች የተስፋ ምልክት ናት፡፡ ወደ እኛ የምትቀርብና በሕይወታችን ዘመን ሁሉ አብራን የምትጓዝ፣ በእናታዊ ፍቅርዋ ልባችንን ለእምነት የምትከፍት ልዑክ ናት፡፡ እውነተኛ እናት በመሆንዋ፣ ከጎናችን ትሄዳለች፣ ትግላችንን ትጋራለች፣ በእግዚአብሔር ፍቅርም ዘወትር ትከበናለች፡፡ ብዙውን ጊዜ ለእርስዋ መታሰቢያነት በተሰየሙ ቅዱሳን ስፍራዎች በምትታወቅባቸው በርካታ የማዕረግ ስሞችዋ አማካይነት፣ ድንግል ማርያም ወንጌልን የተቀበለ የእያንዳንዱን ሕዝብ ታሪክ ትጋራለች፤ የታሪካዊ ማንነታቸውም አካል ትሆናለች፡፡ ብዙ ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸው በማርያማዊ ቅዱሳን ቦታዎች እንዲጠመቁላቸው ይጠይቃሉ፤ ይህም ለእግዚአብሔር አዲስ ልጆችን በሚያመጣ በእርስዋ እናትነት ላይ ላላቸው እምነት ምልክት እንዲሆንላቸው በማሰብ ነው፡፡ በእነዚያ በብዙ ቅዱሳን ቦታዎች ድንግል ማርያምን ለማየትና በእርስዋም ለመታየት ሲሉ በመንፈሳዊ ተጓዥነት በጥረት የሚመጡ ልጆችዋን እንዴት እንደምትሰበስብ ማየት እንችላለን፡፡ እዚህ ቦታ ላይ በሕይወታቸው ውስጥ የሚገጥማቸውን ድካምና መከራ ይታገሡ ዘንድ ከእግዚአብሔር ብርታትን ያገኛሉ፡፡ ድንግል ማርያም ለሁዋን ዲዩጎ እንዳደረገችለት፣ ለእነርሱም እናታዊ መጽናናትና ፍቅርን ትሰጣቸዋለች፣ በጆሮአቸውም ‹‹ልባችሁ አይጨነቅ…. እኔ እናታችሁ እዚህ አይደለሁምን?›› ትላቸዋለች፡፡

የአዲሱ ስብከተ ወንጌል ኮከብ

ይህ ለመላው ክርስቲያን ማኅበረሰብ የቀረበ አዲስ የስብከተ ወንጌል ጥሪ ተቀባይነት እንዲኖረው ትማልድልን ዘንድ የሕያው ወንጌልን እናት እንለምናታለን፡፡ ድንግል ማርያም በእምነት የምትኖርና የምትጓዝ የእምነት ሴት ናት፣ ‹‹እርስዋ ልዩ የእምነት ጉዞ ለቤተክርስቲያን የዘወትር ማጣቀሻ ናት››፡፡ ድንግል ማርያም ወደ አገልግሎትና ፍሬያማነት በሚያደርስ የእምነት ጉዞዋ መንፈስ ቅዱስ ይመራት ዘንድ ፈቀደች፡፡ ዛሬ እኛም ለሰው ሁሉ የማዳን መልእክት እንድንሰብክ እንድትረዳንና አዲሶቹ ደቀ መዛሙርትም በበኩላቸው የወንጌል ሰባኪዎች እንዲሆኑ እንድትደግፋቸው የእርስዋን ረድኤት እንለምናለን፡፡ በዚህ የስብከተ ወንጌል ጉዞ ላይ የድርቀት፣ የጨለማና የድካም ወቅቶች ያጋጥሙናል፡፡ ድንግል ማርያም ራስዋ ኢየሱስ በናዝሬት ባሳለፈባቸው የልጅነት ጊዜያት እነዚህ ነገሮች አጋጥመዋታል፡፡ ‹‹ይህ የወንጌል፣ የምስራች ቃል፣ መጀመሪያ ነው፡፡ ይሁን እንጂ፣ በዚያ ጅምር ውስጥ፣ ከእምነት ሌሊት፣ ቅዱስ ዮሐንስ ዘመስቀል እንዳለው፣ አንድ ሰው ወደማይታይ አምላክ የሚጠጋበትና ከምስጢሩ ጋር በቅርበት የሚኖርበት ‹‹መጋረጃ›› ከሚመስል ሁኔታ የተነሣ ልዩ የሆነ ልባዊ ኀዘን እንደሚሰማ መረዳት አያዳግትም፡፡ ይህም ድንግል ማርያም፣ ለብዙ ዓመታት፣ ከልጅዋ ምስጢር ጋር በቅርበት የኖረችበትና በእምነት ጉዞዋ የተጓዘችበት መንገድ ነው››፡፡

የቤተክርስቲያን የስብከተ ወንጌል ሥራ ማርያማዊ ‹‹ዘዴ›› ያለበት ነው፡፡ የድንግል ማርያምን ረድኤት በጠየቅን ጊዜ ሁሉ፣ የፍቅርንና የርኅራኄን ለዋጭ ባህርይ እንደገና ወደ ማመን እንደርሳለን፡፡ ትሕትናና ደግነት የደካሞች ትሩፋቶች ሳይሆኑ የራሳቸውን ታላቅነት በማሰብ ሌሎችን ዝቅ አድርገው የማይመለከቱ ብርቱዎች የሚሠሩአቸው በጎ ሥራዎች መሆናቸውን በእርስዋ እናያለን፡፡ ስለ ድንግል ማርያም ስናሰላስል፣ ‹‹ገዢዎችን ከዙፋናቸው ያወረደውን›› እና ‹‹ሀብታሞችን ባዶአቸውን የሰደደውን›› (ሉቃ.1፡52-53) እግዚአብሔርን ያመሰገነችው እርስዋ የፍትህ ፍለጋችንን የምትደግፍ መሆንዋን እንረዳለን፡፡ እንዲሁም ‹‹ይህንን ሁሉ በልቧ ይዛ ስታሰላስል›› (ሉቃ.2፡19) የነበረችው እርስዋ ናት፡፡ ድንግል ማርያም በትልቅም ሆኑ በትንሽ ክስተቶች ውስጥ የእግዚአብሔርን መንፈስ ምልክቶች ማወቅ ቻለች፡፡ በዓለማችን፣ በሰው ልጅ ታሪክና በዕለታዊ ኑሮአችን ውስጥ የእግዚአብሔርን ምስጢር ዘወትር ታሰላስላለች፡፡ በናዝሬት ሳለች  የጸሎትና የሥራ ሴት ነበረች፤ ሌሎችን ለመርዳት ከከተማዋ ‹‹ፈጥና የምትነሣ›› (ሉቃ.1፡39) ረዳት እናታችን ናት፡፡ ይህ የፍትህና የርህራሄ፣ የማሰላሰልና ለሌሎች የመጨነቅ ሁኔታ ቤተክህነት ድንግል ማርያምን የስብከተ ወንጌል ምሳሌ አድርገው እንዲመለከቷት ያደርጋቸዋል፡፡ ስለዚህ፣ ቤተክርስቲያን የብዙ ሕዝቦች ቤት፣ የሕዝቦች ሁሉ እናት እንድትሆንና ለአዲስ ዓለም ልደት በር እንዲከፈት እናታዊ አማላጅነትዋን እንለምናለን፡፡ ‹‹እነሆ፣ ሁሉን ነገር አዲስ አደርጋለሁ›› (ራእይ.21፡5) ብሎ የሚነግረንና በእምነትና በማይናወጥ ተስፋ እንድንሞላ የሚያደርገን ከሞት የተነሣው ክርስቶስ ነው፡፡ ስለዚህ፣ ይህ የተስፋ ቃል እንዲፈጸም ከድንግል ማርያም ጋር በመተማመን ወደፊት እንጓዛለን፣ ወደ እርስዋም እንዲህ በማለት እንጸልያለን፡

ማርያም ፣ድንግል እናት፣ በመንፈስ ቅዱስ ተነሣሥተሽ  የሕይወትን ቃል በትሁት እምነት የተቀበልሽ፣ ራስሽን ሙሉ በሙሉ ለዘላለማዊ አምላክ እንደሰጠሽ፣ ምን ጊዜም አስቸኳይ ለሆነው ጥሪ፣ ይኸውም የኢየሱስን የምስራች ቃል ለመስበክ እኛም ‹‹እሺ›› እንድንል እርጂን፡፡ በክርስቶስ መኖር ተሞልተሸ፣ መጥምቁ ዮሐንስን አስደሰትሽው፣ በእናቱ ማሕፀን ውስጥ እንዲፈነድቅ አደረግሽው። በደስታም ተሞልተሸ፣ እግዚአብሔር ስላደረገው ታላቅ ነገር ዘመርሽ።በማይናወጥ እምነት በመስቀሉ ሥር ቆመሽ፣ የትንሣኤን ደስታና መጽናናት አገኘሽ፤ ወንጌልን የምትሰብክ ቤተክርስቲያን ትወለድ ዘንድ፣ ከደቀ መዛሙርት ጋር ሆነሽ የመንፈስ ቅዱስን መምጣት ተጠባበቅሽ። እኛም ለሰው ሁሉ የሕይወትን ወንጌል እናደርስ ዘንድ፣ ሞትን የሚያሸንፍ የትንሣኤን አዲስ እሳት አሰጪን። የማይደበዝዝ የውበት ስጦታ፣ ለሰው ሁሉ ይደርስ ዘንድ፣ አዲስ መንገድ የምንሻበትን የተቀደሰ ብርታት ስጪን፡፡

የምታዳምጪና የምታሰላስዪ ድንግል፣ የፍቅር እመቤት፣ የሰላማዊ ሠርግ ሙሽሪት ሆይ፣ አንቺ ንጽሕት ምልክቷ ነሽና፣ በራስዋ የተዘጋች ከቶ እንዳትሆን፣ ወይም የእግዚአብሔርን መንግሥት የመመሥረት ፍላጎትዋን፣ እንዳታጣ ለቤተክርስቲያን ለምኚላት። የአዲስ ስብከተ ወንጌል ኮከብ ሆይ፣ የወንጌል ደስታ ወደ ዓለም ዳርቻዎች እንዲደርስ፣ የዓለማችንን ዳርቻዎች ጭምር እንዲያበራ፣ የአንድነት፣ የአገልግሎት፣ የጋለና ለጋስ እምነት፣ የፍትህና ድሆችን የመውደድ፣ አንፀባራቂ ምስክሮች እንድንሆን እርጂን። የሕያው ወንጌል እናት፣ ለእግዚአብሔር ታናናሾች ፣ የደስታ ምንጭ የሆንሽ ሆይ፣ ለምኚልን፡፡ አሜን፡፡ ሃሌሉያ !

 

21 February 2024, 11:37