ፈልግ

በሮም በሚገኘው ይስሐቅ አባርባኔል ዩኒቨርሲቲ የተቋቋመው የሥነ ምግባር ማዕከል የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት በሮም በሚገኘው ይስሐቅ አባርባኔል ዩኒቨርሲቲ የተቋቋመው የሥነ ምግባር ማዕከል የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት 

አዲስ የተቋቋመው የሥነ ምግባር ማዕከል በሮም የሚኖሩ አይሁዶችንና ክርስቲያኖችን አንድ ያደርጋል ተባለ

ከአይሁዶች ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ከሆነው ‘ማርሻል ቲ ሜየር’ ሴሚናሪ ጋር ግንኙነት ያለው አዲስ የከፍተኛ ትምህርት እና የምርምር አካዳሚክ ተቋም የሆነው የሥነ ምግባር ማዕከል በሮም ከተማ የተመረቀ ሲሆን፥ ይህ በይስሐቅ አባርባኔል ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የተከፈተው የሥነ ምግባር ማዕከል፥ የጳጳሳዊ የህይወት አካዳሚ ፕሬዝዳንት ከሆኑት ሊቀ ጳጳስ ቪንሴንዞ ፓግሊያ ጋር በመተባበር የተቋቋመ እንደሆነም ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ሐሙስ የካቲት 7 ቀን 2016 ዓ.ም. ሮም በሚገኘው አይዛክ አባርባኔል ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የተቋቋመውን አዲሱን የሥነ ምግባር ማዕከል መርቀው የከፈቱት የጳጳሳዊ የሕይወት አካዳሚ ፕረዚዳንት የሆኑት ብጹእ አቡነ ቪንሴንዞ ፓግሊያ ባደረጉት ንግግር፥ የሮም ከተማ ለእንዲህ ዓይነቱ ምቹ ቦታ ናት ወደሚል መደምደሚያ ላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል።

“ዓለም አቀፋዊ የትምህርት እድገቶችን እና የተለያዩ ሃይማኖታዊ አስተምህሮዎችን፥ በተለይም የአብርሀማዊ ሃይማኖቶችን የሚያቀራርብ እና በመካከላቸው ያሉ ምሁራንን፣ ተመራማሪዎችን እና የሃይማኖት መሪዎችን ያካተተ” ተቋም እንደሆነም ገልጸዋል።

በቺሊ እና በአትላንታ የህፃናት ጤና አጠባበቅ ውስጥ የሕክምና እና ባዮሎጂካል ምርምር ሥነ-ምግባር (ባዮኤቲክስ) ኮሚቴዎችን በማቋቋም ቁልፍ ሰው የሆኑት ረቢ አናሊያ ቦርትዝ በበኩላቸው በእያንዳንዱ ሰው ህይወት ውስጥ ያለውን የስነ ምግባር ዋጋ በመጠቆም፥ የሰው ልጅ በሁሉም የሕይወት ደረጃዎቹ ውስጥ እግዚአብሔር እንደሚያስፈልገው የሚናገረውን የመዝሙረ ዳዊት ጥቅስ በዕብራይስጥኛ ጠቅሰዋል።

“አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ወይም ሰው ሰራሽ አስተውሎት የማህበረሰባችን ፈተና ነው” ያሉት ደግሞ ከአዲሱ ማዕከል መስራች አባላት አንዱ የሆኑት አርጀንቲናዊው ሐኪም እና ፖለቲከኛ ክላውዲዮ ሬጋዞኒ ሲሆኑ፥ “የሥነ ምግባር ማዕከልን የምንፈልግበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው” ካሉ በኋላ፥ እስካሁን ድረስ ሰዎች በማሽን ላይ ስልጣን እንደነበራቸው፥ ነገር ግን በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እና አልጎሪዝም ይህ ሊለወጥ እንደሚችል አስምረውበታል።

የጳጳሳዊ የሕይወት አካዳሚ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብጹእ አቡነ ቪንሴንዞ ፓግሊያ በንግግራቸው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስን በመጥቀስ፥ “የምንኖረው የለውጥ ዘመን ላይ ሳይሆን የዘመን ለውጥ ላይ ነው” ብለዋል። በማከልም “እንዲህ ዓይነቱ ማዕከል አስፈላጊ የሆነውም በዚህ ምክንያት ነው፥ በሃይማኖቶች፣ በሳይንቲስቶችና በሁሉም ሰዎች መካከል ወንድማማችነት ያስፈልገናል” ሲሉ ተናግረዋል።

ይህ የስነ ምግባር ማዕከል የተመሰረተው በላቲን አሜሪካ የሚገኘው የራቢኒካል ሴሚናሪ ሃላፊ በሆኑት በረቢ አሪያል ስቶፈንማቸር ሲሆን፥ የምረቃው ሥነ ስርዓትም የተካሄደው በሮም በሚገኘው ፎክላር የመሰብሰቢያ ቦታ ነበር።

አዲሱን ማዕከል በማስመልከት በወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተገለጸው፥ “ዋና ዓላማው በሥነ ምግባር መስክ ትምህርታዊና የምርምር ፕሮግራሞችን ማጎልበትና ማዳበር፣ ለትክክለኛ አሠራር የሚተጉ መሪዎችን ማሠልጠን፣ በመንግሥትም ሆነ በግሉ ዘርፍ እሴቶችን ማስተዋወቅ፣ እና በተግባራዊ ሥነ ምግባር ውስጥ መሥራትን” እንደሚያካትት ተገልጿል።
 

16 February 2024, 12:58