ፈልግ

FRANCE-ARCHITECTURE-HERITAGE-RELIGION-CHURCH-RENOVATION FRANCE-ARCHITECTURE-HERITAGE-RELIGION-CHURCH-RENOVATION  (AFP or licensors)

የፓሪሱ ሊቀ ጳጳስ ለኖትር ዳም ካቴድራል ምርቃት የተለያዩ ዝግጅቶች መዘጋጀታቸውን ገለጹ

የፓሪስ ከተማ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብጹእ አቡነ ሎረንት ኡልሪች ፓሪስ ከተማ ውስጥ የሚገኘውን እና በእሳት ቃጠሎ ጉዳት ደርሶበት የነበረውን የኖትር ዳም ካቴድራልን ኅዳር 29 ቀን 2017 ዓ.ም. እንደገና ለአገልግሎት ለማብቃት የጸሎት ሳምንትን ጨምሮ መጠነ ሰፊ ሥራዎች እና ተነሳሽነቶች እንደተዘጋጁ ገልጸዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ይህ የፈረንሳይ ከተማ የ 16ኛው ክፍለ ዘመን ድንቅ ሥራ የሆነው የኖትር ዳም ካቴድራል ዳግም ከመከፈቱ 10 ወራት ቀደም ብሎ የተለያዩ የማስመረቂያ መርሃ ግብሮች እንደተዘጋጁ ብጹእ አቡነ ሎረንት ኡልሪች አመላክተዋል።

እነዚህም መርሃ ግብሮች በርካታ ክብረ በዓላትን እና የአምልኮ ጉዞዎችን የሚያካትት ሲሆን፥ ቀናቶቹም ከኅዳር 29 ቀን 2017 ዓ.ም. እስከ ሰኔ 1 ቀን 2017 ዓ.ም. እንደሚራዘም ተገልጿል። ይህም የሆነበት ምክንያት በዕለቱ የጴንጤቆስጤ ክብረ በዓል እንደ ዓለም አቀፍ ቤተክርስቲያን ስለሚከበር እንደሆነ ተነግሯል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ከዚህን በፊት ለፓሪስ ከተማ ሊቀ ጳጳሳት በላኩት መልዕክት በመልሶ ግንባታ ሥራ አማካይነት በእሳት ቃጠሎ ጉዳት የደረሰበት የፓሪስ ከተማ ካቴድራል ወደ ቀድሞ ስፍራው መመለስ ለእናት ቤተ ክርስቲያን፣ ለፓሪስ ሀገረ ስብከት ለፈረንሳይ ሕዝብ እና ለሰው ልጅ በሙሉ የእምነት ምልክት ነው ማለታቸውን ይታወሳል።

ካቴድራሉ ሚያዚያ 7 ቀን 2011 ዓ.ም. የእሳት አደጋ ደርሶበት እንደተቃጠለ የተገለፀ ሲሆን፥ የፓሪስ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብጹእ አቡነ ሎረንት ጥር 24 ባወጡት ደብዳቤ መሰረት ምእመናን ለካቴድራሉ ዳግም ምርቃት የበኩላቸውን እንዲያደርጉ ጥር አስተላልፈዋል።

ቤተክርስቲያኑ እንደገና ከመከፈቱ 15 ቀናት በፊት፥ የካቴድራሉን እንደገና ለአገልግሎት መዘጋጀት አስመልክቶ የፓሪስ ጎዳናዎች ላይ ትልቅ ትዕይንተ ሰልፍ እንደሚደረግም ተገልጿል።

በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደተሰራ የተነገረው፥ በካቴድራሉ ውስጥ የነበረው እና ከቃጠሎ የተረፈው፥ 1.8 ሜትር ቁመት ያለው የቅርጻ ቅርጽ ጥበብ የሆነው የእመቤታችን ድንግል ማሪያም እና የሕፃኑ ኢየሱስ ክርስቶስ ምስል፥ ከሉቭር ቤተ መንግሥት ፊት ለፊት በሚገኘው በቅዱስ ዠርሜን-አክዜሪዮስ ቤተ ክርስቲያን እንደተቀመጠም ተነግሯል።

የሶስት ቀናት ይፋዊ ምረቃ

ካቴድራሉ በይፋ ከሚመረቅበት ኅዳር 28 ቀን 2017 ዓ.ም. ቀደም ብሎ የሶስት ቀናት የመክፈቻ መርሃ ግብር እንደሚዘጋጅም ተነግሯል። በእነዚህም ቀናት የኖትር ዳም ካቴድራል ከግዛቱ ባለቤት ለካቶሊክ ቤተክርስቲያን የሚሰጥበትን ሥነ ስርዓትን እንደሚያካትት የተገለፀ ሲሆን፥ በተጨማሪም በተለያዩ ሙዚቃ መሳሪያዎች የተቀነባበሩ መንፈሳዊ ዜማዎች፣ የጸሎት ሥነ ስርዓቶች፣ እና ሥርዓተ አምልኮዎች እንደሚታጀብም ተገልጿል።

የመሠዊያው ቅድስና የሚከናወነው በዳግማዊ ትንሳኤ ሁለተኛ እሑድ፥ ኅዳር 29 ቀን 2017 ዓ.ም. በታደሰው ካቴድራል ውስጥ በሚደረገው በመጀመሪያው ቅዳሴ ወቅት እንደሆነ እና በማግሥቱ ሰኞ ኅዳር 30 የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ክብረ በዓል እንደሚደረግ ተነግሯል።

ካቴድራሉ ከኅዳር 29 - ታህሳስ 6 ባሉት ቀናት ዳግም ይከፈታል

የኖትር ዳም ካቴድራል ከኅዳር 29 - ታህሳስ 6 2017 ዓ.ም. ድረስ በሚዘጋጁ የተለያዩ መርሃ ግብሮች ዳግም ለአገልግሎት እንደሚበቃ ተገልጿል።

ብጹእ አቡነ ሎረንት እንደገለጹት በሥነ ስርዓቱ ላይ የፈረንሳይ መንግሥት ተወካዮች፣ ለጋሾች፣ በካቴድራሉ እድሳት ወቅት ለአምስት ዓመታት ያገለገሉ ቡድኖች፣ የእሳት አደጋ በደረሰበት ወቅት ህንፃው ሙሉ በሙሉ እንዳይቃጠል ያዳኑ የእሳት አደጋ ሠራተኞች፣ የፈረንሣይ ጳጳሳት፣ የውጭ አገር ጳጳሳት እና የፈረንሳይ ሃገረ ስብከት ተወካዮችን ጨምሮ በርካታ የሕዝብ ተወካዮች እንደሚገኙ የጠቆሙ ሲሆን “የፓሪስ ከተማ ነዋሪዎች” በሥነ ስርዓቱ ላይ እንዲገኙም ጥሪ አስተላልፈዋል።

ሊቀ ጳጳሱ ከታህሳስ እስከ ሰኔ ባሉት ስድስት ወራት ውስጥ በፓሪስ ከሚገኙት ደብሮች እና የፓሪስ አውራጃ አህጉረ ስብከት ምእመናን ወደ ስፍራው መንፈሳዊ ንግደት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

ሊቀ ጳጳሱ አበክረው እንደተናገሩት “ይህንን ሥነ ስርዓት ሁሉም ክርስቲያኖች፣ በሁሉም የዕድሜ ክልል የሚገኙ እና በዬትኛሁም ሁኔታ ያሉ ሰዎች እንዲያከብሩት እንፈልጋለን” ካሉ በኋላ፥ “በቤተክርስቲያን ዝግጅቶች ወቅት ከምንም በላይ የሚያስደስተው ነገር የተለያየ ባህል ያላቸው ሰዎች፣ የመንደሩ ነዋሪዎች፣ ሕፃናት፣ ወጣቶች፣ ጎልማሶች፣ አዛውንቶች፣ ጤነኞች እና ታማሚዎች፣ አካል ጉዳተኞች፣ የውጭ አገር ሰዎች አንድ ላይ ተሰብስበው ማየት ነው ብለዋል። የክርስቲያን ማኅበራት ማንንም ወደ ኋላ ባለመተው፣ በጣም ለተጨነቁ፣ ለተገለሉ፣ ለተረሱ ሰዎች ተጨንቀው ቦታ ሲያዘጋጁላቸው ከማየት በላይ ደስታ የሚሰጥ ነገር ዬለም፥ እነዚህ ሁሉ በኖትር ዳሙ ዝግጅት ይገኛሉ” ብለዋል።

ከሚያዝያ 2014 ዓ.ም. ጀምሮ የፓሪስ ሊቀ ጳጳስ ሆነው እያገለገሉ የሚገኙት ብጹእ አቡነ ሎረንት ኡልሪች፥ የኖትር ዳም ካቴድራል እንደገና እንዲገነባ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ላደረጉ ለጋሾች እና ደጋፊዎቻቸው ያላቸውን አድናቆት በመግለጽ ደብዳቤያቸውን አጠቃለዋል።
 

06 February 2024, 13:16