በአራተኛው ክፍለ ዘመን የነበሩ “የቤተ ክርስቲያን እናቶች”
በፈረንሳይ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1650 ዓ. ም. የተቋቋመ የገዳማውያት ማኅበር አባል እህት ክርስቲን ሼንክ በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ታዋቂ የነበሩ ገዳማውያት እህቶች ገዳማትን በማቋቋም ለዛሬው የገዳማውያት ያበረከቱትን አስተዋፅዖ በመዳሰስ ከጻፏቸው አራት ጹሑፎች መካከል አንዱ ይህ ሦስተኛው ጽሑፋቸው ነው።
4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በክርስቲያኖች ላይ በተለይም በምሥራቅ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከፍተኛ ስደት የጀመረበት ክፍለ ዘመን ነበር። ቆስጥንጢኖስ ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ጸሎቱን ካቀረብ እና ረጅም የሥልጣን ሽኩቻ ካካሄደ በኋላ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ324 ዓ. ም. ንጉሠ ሆነ።
የቆስጥንጢኖስ ልጆች እና እናቱ ሄለን ላበረከቱት የንጉሣዊ ቤተሰብ ድጋፍ ምስጋና ይግባውና ይህን ተከትሎ ቤተ ክርስቲያን ከዚያ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መልክ በዓለማዊ ሃያላን ላይ ተፅእኖ በመፍጠር ወደ ከፍታ ላይ ወጣች። በዚህ መሠረት የቤተ ክርስቲያን ሴቶች የነበሩ እንደ ኦሎምፒያስ፣ ታላቋ ሜላኒያ እና ፓውላ ከክርስቲያን መኳንንት ቤተሰብ መካከል የላቀ ድጋፍ ካደረጉት ሴቶች መካከል ይጠቀሳሉ።
ቀደም ሲል በትላልቅ ቤቶች ወይም ሕንፃዎች ውስጥ ይሰበሰቡ የነበሩ የክርስቲያን ማኅበረሰቦች በአሁኑ ጊዜ ጥሩ በሆኑ የሕዝብ መኖሪያ አከባቢዎች ለመገኘት በቅተዋል። ይህን እንጂ እነዚህ ለውጦች ክርስቲያን ሴቶች የሚያበረክቱትን ሕዝባዊ አገልግሎት ውጥረት ውስጥ ሳይጥሉ አልቀሩም።
በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሴቶች ሚና መቀየር
በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የሴት ጾታን ከመናፍቅነት ጋር የማዛመድ ዝንባሌ ታይቷል። ምንም እንኳን ሁለቱም ክርስቲያን ወንዶች እና ሴቶች በተለያዩ የክርስትና አተረጓጎም ውሎ አድሮ መናፍቃን ተብለው ተፈርጀዋል።በተለይም ሴቶች የመምህርነት ሚናን ከወሰዱ መናፍቃን ተብለው ለመፈረጅ እና ንጽሕናቸውን አጉድለዋል ተብለው የሚጠረጠሩበት አደጋ ተጋርጦባቸው ነበር። ይህ በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን “የቤተ ክርስቲያን እናቶች” የኖሩት እና የመሰከሩት የቤተ ክርስቲያን አውድ ነው።
ቀጥሎ ያለው ታሪክ አጭርም ቢሆን ጉልህ በሆነ መልክ በዘመን ቅደም ተከተል መሠረት ክርስቲያን ሴቶች እና ማኅበረሰባቸው በጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስልጣንን የተለማመዱበት መንገድ ይገልጻል።
በሴቶች የተፃፉ መጽሐፍት
ስለ 4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሴቶች ስናወራ እንደ ማርሴላ፣ ፓውላ፣ ማክሪና፣ ታላቋ ሜላኒያ እና ኦሎምፒያስ የመሳሰሉትን የሚገልጹ ሥነ-ጽሁፋዊ መረጃዎች በዋነኛነት የመነጨው ስለ እነርሱ ከጻፉት የተማሩ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ማለትም ዬሮኒዮስ፣ ጎርጎርዎስ፣ ፓላዲዮስ እና ዮሐንስ ክሪሶስቶም ነው።
በሴቶች የተፃፉ “ፕሮባ” እና “ኤጄሪያ” የሚል ርዕሥ የተሰጣቸው ሁለት ጽሑፎች አሉ። ፕሮባ በሚል ርዕሥ የተጻፈው መጽሐፍ እጅግ ተወዳጅ የሆነውን የሮም ቨርጂሊያን ቼንቶ እና የክርስትናን ታሪክ በማስተካከል እንደገና ለመኳንንት ወጣት ወንዶች ወንጌልን ስለመስበክ ይናገራል። ፕሮባ በክርስቲያን ወንዶች እና ሴቶች ላይ ለትውልድ የሚተላለፍ ባህላዊ የወንጌል ማስተማሪያ መንገድን አዘጋጅታለች።
ኤጄሪያ በምሥራቅ ወደሚገኙ ቅዱሳት ሥፍራዎች ያደረገችውን ጉዞ የሚገልጽ የጉዞ ማስታወሻ ደብተር ለእህቶቿ አዘጋጅታለች። ጉዞ ላይ በነበረችበት ወቅት ቱርክ ውስጥ በቅድስት ቴክላ ቤተ መቅደስ አቅራቢያ የሚገኙ ሁለት ገዳማትን የምታስተዳድር ተወዳጇ ጓደኛዋን ዲያቆን ቅድስት ማርታናን ስለማግኘት ጽፋለች። ሴት ዲያቆን ማርታና በክርስቲያን ወንዶች እና ሴቶች ላይ የአስተዳደር ሥልጣኗን የምትጠቀም ተጠቃሽ ምሳሌ ናት።
በምሥራቅ ባዚሊዮስ እና በምዕራብ ዬሮኒሞስ ለገዳም ሕይወት ዕድገት ያደረጉት ጥረት በተደጋጋሚ ሲነገር፥ ሁለት ሴቶች እነርሱም ማክሪና እና ማርሴላ ይህን አዲሱን ክርስቲያናዊ የአኗኗር ዘይቤን ከወንዶች ቀደም ብለው መኖር የጀመሩ ነበሩ።
ማክሪና (327-379 እ.አ.አ) በወንድሟ ባዚሊዮስ የተጻፈውን የገዳም ሕይወት ደንብ ምሳሌ የሆነውን እና በትንሿ እስያ ውስጥ የሚገኘውን የአኒሳ ገዳም መሠረተች። ባዚልዮስም ከጊዜ በኋላ የገዳማት አባት ሆኖ ተቆጠረ እንጂ ነገር ግን ማክሪና እናቱ ነበረች። እንደ መንፈሳዊ የመሪነት ሥልጣን፥ የቅድስት ሥላሴን ትምህርት ባዘጋጁት የሃይማኖት ሊቃውንት ወንድሞቿ በጎርጎርዮስ እና በባዚሊዮስ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳደረች።
ማርሴላ (325-410 እ.አ.አ) ሴቶችን በአቨንቲኖ ኮረብታ ላይ በሚገኝ ቤቷ ውስጥ ምዕመናን ሰብስባ ቅዱሳት መጻሕፍትን እያስጠናች አብረዋቸው ትጸልይ ነበር። ይህ የሆነው ዬሮኒሞስ ወደ ሮም ከመምጣቱ ከአርባ ዓመታት በፊት ነበር። ነገረ ግን ዬሮኒሞስ ወደ ኢየሩሳሌም ከተመለሰ በኋላ የሮም ካህናት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን የማብራራት ዕርዳታን ለማግኘት ማርሴላን ያማክሩ ነበር። ማርሴላ ከዚያ በፊት ቀዳሚ የእምነት አስተምህሮ ይህ ነው ተብሎ በተነሳው ውዝግብም ውስጥ በአደባባይ ተከራክራ ነበር።
ፓውላ (347-404 እ.አ.አ) በቤተልሔም የሚገኙትን ሁለት ገዳማት፥ አንደኛውን ለሴቶች እና ሌላኛውን ለወንዶች መሠረተች። ደጋፊዋ የሆነው ዬሮኒሞስ የግሪክን መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ላቲን ተርጉሞ እንዲያጠናቅቅ የወንዶቹን ገዳም ሰጠችው። ዬሮኒሞስም የፓውላ የዕብራይስጥ እውቀት ከራሱ እንደሚበልጥ ይናገር ነበር።
ታላቋ ሜላኒያ (350-410እ.አ.አ) አንድ ታዋቂ የቤተ ክርስቲያን ሰው የነበረውን ኤቫግሪየስን ወደ ገዳም ሕይወት በመምራት ሰዎችን እንዲያስተምር እና እንዲለውጥ አገዘችው። በአንጾኪያ 400 የሚደርሱ መነኮሳትን ያሳተፈውን አለመግባባት ለመፍታት የተደረገውን ጥረት በማሳካት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽዖ አበርክታለች። ማኅበረሰቦቿ በቅዱሳት መጻሕፍት ጥናት፣ በጸሎት እና በበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ የተሰማሩ የደብረ ዘይት ሁለት ገዳማትን በገንዘብ ደግፈዋል።
ኦሎምፒያስ (368-408 እ.አ.አ) የቆስጥንጥንያ ጳጳስ በነበሩት በአቡነ ነክታሪዮስ የዲቁና ማዕረግ የተቀበለችው ኦሎምፒያስ፥ ሰፊውን የቤተሰቧን ሃብት ቤተ ክርስቲያንን ለመደገፍ እና ድሆችን ለመርዳት ተጠቅማለች። ሦስት ሴት ዘመዶቿ የዲቁና ማዕረግ የተቀበሉበትን እና ከሐጊያ ሶፍያ አቅራቢያ የሚገኝ አንድ ትልቅ ገዳም መሥርታለች። ብዙም ሳይቆይ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ቤተሰብ የሆኑት የሮማውያን ሴቶች ገዳሙን ተቀላቀሉት። በኋላም የሴት ገዳማውያት ቁጥር ወደ 250 አደገ።
እነዚህ የ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሴቶች ማኅበራቸው ለዘመናዊ ምንኩስና ሕይወት ካደረጓቸው ጥቂት ምሳሌዎች መካከል ቀዳሚዎቹ ናቸው። የቤተ ክህነት ምስክርነታቸው እና ሥልጣናቸው በዘመናቸው በነበሩት የክርስቲያን ማኅበረሰቦችም ሆነ በመጪዎቹ ዘመናት ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል።
አንዳንድ ጊዜ ወንድ ምእመናን ሴቶች በአደባባይ እንዳይናገሩ እና እንዳያስተምሩ ሲከለክሉ እና በቤት ውስጥ ብቻ እንዲቆዩ በሚጠይቋቸው በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ውስጥ ክርስቲያን ሴቶች ሥልጣን በማግኘት ጠቃሚ የቤተ ክርስቲያን ጉዳዮችን የሚናገሩ፣ ወንዶችንም ሆነ ሴቶችን ያስተምሩ እንደነበር ማስረጃዎች ይገልጻሉ። ሕይወታቸን በሙሉ ለኢየሱስ ክርስቶስ አሳልፈው መስጠታቸውንም በግልጽ መስክረዋል።
ይህ ጽሑፍ ጥቅም ላይ እንዲውል የቀረበው አብዛኛው ጥንታዊ ታሪክ፥ “‘ክሪስፒና እና እህቶቿ’፥ ሴቶች እና ስልጣን በጥንታዊ የክርስትና ዘመን" በሚል ርዕሥ “ፎርትሬስ” አሳታሚ ድርጅት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2017 ዓ. ም. ካሳተመው መጽሐፍ የተወሰደ ነው። የጥንት ክርስቲያን ሴቶች ለቤተ ክርስቲያን ግንባታ ያበረከቱትን ንቁ አስተዋጽዖ አስመልክቶ ትንታኔን የሚሰጥ አራተኛውንና የመጨረሻውን ርዕስ በሚቀጥለው ጊዜ እናቀርብላችኋለን።
የጽሑፉ ተርጓሚ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን