ፈልግ

በፖርት ኦ-ፕሪንስ ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች የወሮበሎቹን ጥቃት በመፍራት እየሸሹ ይገኛሉ በፖርት ኦ-ፕሪንስ ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች የወሮበሎቹን ጥቃት በመፍራት እየሸሹ ይገኛሉ  

በሄይቲ ውስጥ ስድስት የካቶሊክ ወንድሞች እና አንድ ካህን በታጣቂ ቡድኖች መታገታቸው ተነገረ

በካሪቢያን ሀገር እየተካሄደ ያለው የቡድን ጦርነት ቀጥሎ ባለበት በአሁኑ ወቅት፥ ባለፈው አርብ በፖርት ኦ ፕሪንስ ታግተው የነበሩት ስድስት የቅዱስ ልብ ማህበር ወንድሞች እና አንድ ካህን በአስቸኳይ እንዲፈቱ በሄይቲ የሚገኙ የሃይማኖት መሪዎች ጠይቀዋል።

 አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በሄይቲ ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመጣው የታጣቂ ቡድኖች እንቅስቃሴ መሃል፥ የካቲት 15 ቀን 2016 ዓ.ም. 6 የካቶሊክ ወንድሞች እና አንድ ካህን በሄይቲ ዋና ከተማ ፖርት-ኦ-ፕሪንስ መታገታቸውን በአከባቢው የሚገኝ የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ምንጮች ገልጸዋል።

ታጋቾቹ በአስቸኳይ እንዲፈቱ የቀረበ ጥሪ

የቅዱስ ልብ ጉባኤ አባላት የሆኑት ስድስቱ ወንድሞች አርብ ማለዳ ፖርት ኦ-ፕሪንስ መሀል ከተማ ወደሚገኘው ኤኮል ዣን 23ኛ ት/ቤት እየሄዱ ባለበት ወቅት በታጣቂ ቡድን ታፍነው ተወስደዋል። ይህ ት/ቤት ከፍተኛ ስጋት በሆኑ አከባቢዎች ውስጥ በሥራ ላይ የሚገኝ ብቸኛው ት/ቤት እንደሆነም ተነግሯል።

በዚያው ቀን በቢሴንቴናየር አውራጃ በሚገኘው የፋጢማ እመቤታችን ጸሎት ቤት ቅዳሴን ሲያሳርጉ የነበሩ አንድ ካህን ታግተው መወሰዳቸውም ተነግሯል።

በሄይቲ የሚገኙ የሀይማኖት አባቶችና ገዳማዊያት ባወጡት መግለጫ የታገቱት ሰዎች ባስቸኳይ እንዲፈቱ እና በሀገሪቱ ያለው የታጣቂ ቡድኖች ጥቃት እንዲቆም እንዲሁም የጸጥታው ችግር ቶሎ መፍትሄ እንዲሰጠው አሳስበዋል።

የአሁኑ እገታ የተፈፀመው ባለፈው ጥር 10 ቀን ስድስት የቅድስት አኔ እህቶች ማኅበር መነኮሳት ከሌሎች ሁለት ሰዎች ጋር በአውቶብስ እየተጓዙ በታጣቂዎች ታፍነው ተወስደው ከጥቂት ቀናት በኋላ ከተለቀቁበት ክስተት ከአንድ ወር በኋላ መሆኑ ታውቋል።

የሃገሪቷን ግዛቶች ለመቆጣጠር በሚሽቀዳደሙ የተለያዩ ወንጀለኛ ቡድኖች ሁከት ውስጥ በቆየችው ሄይቲ ለረጅም ጊዜያት እየተፈፀመ ካለው በርካታ አፈና ውስጥ እነዚህ የቅርብ ጊዜዎቹ ናቸው ተብሏል።

የቆሰሉት ብጹእ አቡነ ፒየር-አንድሬ ዱማስ የጤና ሁኔታ እየተሻሻለ ነው

የወሮበሎቹ ፍጥጫ የቤተክርስቲያን ሰዎችን እንኳን እንደማይምር የተረጋገጠው፥ የሄይቲ ጳጳሳት ጉባኤ ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑትን የአንሴ ቪው ሚራጎን ሊቀ ጳጳስ ብጹእ አቡነ ፒየር-አንድሬ ዱማስ ለጉብኝት ፖርት-ኦፕሪንስ በነበሩበት ወቅት ጥር 19 ቀን 2016 ዓ.ም. በደረሰው የቦንብ ፍንዳታ መቁሰላቸው ይታወሳል። ሊቀ ጳጳሱ ቀዶ ሕክምና ተደርጎላቸው የጤና ሁኔታቸው እየተሻሻለ መምጣቱን የአካባቢው የቤተክርስቲያን ምንጮች ገልጸው፥ በቅርብ ቀን የፍሎሪዳ ከተማ የሆነችው ማያሚ ውስጥ ወደሚገኝ ሆስፒታል ይዘዋወራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ሃምሌ 2013 ዓ.ም. ፕሬዝዳንት ጆቨኔል ሞይስ በኮሎምቢያ ቅጥረኛ ቡድን ከተገደሉ ወዲህ የወረበሎቹ የታጣቂ ቡድኖች እንቅስቃሴ በሄይቲ በአስደናቂ ሁኔታ እንደጨመረ የመጣ ሲሆን፥ ይሄም የሃገሪቷን የደህንነት ሁኔታ እያባባሰው በመምጣቱ ዛሬ ላይ ንፁሃን ዜጎች በየጊዜው ይገደላሉ፣ ይደፈራሉ ብሎም ለገንዘብ ሲባል ይታገታሉ።

በጥር ወር ብቻ ከ1,000 በላይ ሰዎች ተገድለዋል፣ ቆስለዋል ወይም ታግተዋል

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደዘገበው በጥር ወር ብቻ ቢያንስ 1,108 ሰዎች ተገድለዋል፣ ቆስለዋል ወይም ታግተዋል ያለ ሲሆን፥ ይሄም ካለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ አስከፊው ወር እንደነበረ ተገልጿል። በተጨማሪም የካቲት ወር መጀመሪያ ላይ ዋና ዋና የሄይቲ ከተሞች በተቃዋሚ መራሹ ሰልፈኞች ጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር ኤሪኤል ሄንሪ ስልጣን እንዲለቁ የሚጠይቁ ህዝባዊ ተቃውሞዎች ሲናጡ እንደነበር ይታወቃል።

በታህሳስ 2014 ዓ.ም. በተጠናቀቀው የፖለቲካ ስምምነት መሠረት ጠቅላይ ሚኒስትር አሪኤል ጥር 29 ምርጫ እንዲደረግ መፍቀድን የነበረባቸው ቢሆንም፥ የብሔራዊ አንድነት መንግሥት ለመመስረት በሚል ሰበብ አሁንም ድረስ በሥልጣን ላይ ይገኛሉ።

ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ ለፕሬዚዳንትነት ሲካሄዱ የነበሩ ምርጫዎች አሁንም ክፍት እንደሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ ፕረዚዳንት ሞይስ ከተገደሉ በኋላ አገሪቱ ሰፋፊ የግዛቷን ክፍሎች በሚቆጣጠሩ ታጣቂዎች የበለጠ ትርምስ ውስጥ ገብታለች።

የጳጳሳት የጸጥታ ጥሪ

የሄይቲ ጳጳሳት በሃገሪቷ የጸጥታ ሁኔታ እንዲሻሻል ደጋግመው የተማጸኑ ሲሆን፥ በቅርቡ በሰጡት መግለጫ የሄይቲ ዜጎች ለአመፅ እጅ እንዳይሰጡ እና “ለሀገር ጥቅም ሲሉ” ከጠ/ሚ አሪኤል ጎን እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።
 

26 February 2024, 13:26