ፈልግ

ፍቅር በቤተስብ ውስጥ፤ ፍቅር በቤተስብ ውስጥ፤  (Vatican Media)

ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ፤ ፍቅር እና እርግዝና

እርግዝና አስቸጋሪ ነገር ግን ድንቅ ጊዜ ነው። አንዲት እናት የአዲስ ሕጻን ተአምር ለማሳየት ከእግዚአብሔር ጋር ትተባበራለች። እናትነት “የሴት አካል ለአዲስ ሰው ጽንሰትና ልደት የታለመ ልዩ የፈጠራ እምቅ ኃይል” ውጤት ነው። እያንዳንድዋ ሴት “በእያንዳንዱ ልደት በሚታደስ የፍጥረት ምሥጢር” ትሳተፋለች። መዝሙረኛው፥ “በእናቴ ማሕፀን ውስጥ አበጃጅተህ ሠራኸኝ” ይላል (መዝ. 139፡13)። በእናቱ ማሕፀን ውስጥ የሚያድግ እያንዳንዱ ሕጻን፡- “በማሕፀን ሳልሠራህ አወቅሁህ፤ ከመወለድህ በፊት ለየሁህ”” (ኤር. 1፡5) የሚለው የእግዚአብሔር አብ የዘላለማዊ ዕቅድ አካል ነው። እያንዳንዱ ሕጻን ከጥንት ጀምሮ በእግዚአብሔር ልብ ውስጥ ቦታ አለው። እርሱ ወይም እርስዋ አንዴ ከተፀነሱ የፈጣሪ ዘላለማዊ ሕልም እውን ይሆናሉ። ስለዚህ ከጽንሰት ጀምሮ ያለውን የዚያን ፅንስ ታላቅ ዋጋ እናስብ። እርሱንም ምን ጊዜም ከመልክ ባሻገር በሚመለከተው በእግዚአብሔር ዐይን እንመልከተው።

እርጉዝ ሴት ስለ ልጅዋ እያለመች በእግዚአብሔር ዕቅድ ትሳተፋለች። “ለዘጠኝ ወራት እያንዳንድዋ እናትና እያንዳንዱ አባት ስለ ልጃቸው ያልማሉ… ያለ ሕልም ቤተሰብ ሊኖራችሁ አይችልም። አንድ ቤተሰብ ማለም ካልቻለ ሕጻናት አያድጉም፤ ፍቅር አያድግም፤ ሕይወትም ይደርቅና ይሞታል”። ለክርስቲያን ባለትዳሮች ጥምቀት የዚያ ሕልም አካል መስሎ መታየቱ ተገቢ ነው። ምክንያቱም ወላጆች በጸሎት ለጥምቀት ይዘጋጃሉ፤ ገና ከመወለዱ በፊት ሕጻን ልጃቸውን ለኢየሱስ አደራ ይሰጣሉ።

ዛሬ ያለው የሳይንስ ዕድገት የልጅን የጸጉር ቀለም ለመምረጥ ወይም ሊያጋጥሙት የሚችሉ የበሽታ ዓይነቶች ምን እንደ ሆኑ አስቀድመን እንድናውቅ አስችሎናል። ምክንያቱም ሥጋዊ ባህርያት ሁሉ ገና በጽንስ ደረጃ በሰው ዘረ-መል ቀመር ውስጥ ተጽፈው ይገኛሉና። ሆኖም ስለ ሕጻኑ ሙሉ በሙሉ የሚያውቀው ፈጣሪው እግዚአብሔር አብ ብቻ ነው። የሕጻኑን ውስጣዊ ማንነትና ዋጋ የሚያውቀው እርሱ ብቻ ነው። ነፍሰ ጡር እናቶች ልጆቻቸውን በጥልቀት ለማወቅና በማንነታቸው ለመቀበል የሚያስችላቸውን ጥበብ እንዲሰጣቸው እግዚአብሔርን መለመን ያስፈልጋቸዋል። አንዳንድ ወላጆች ልጃቸው በጥሩ ጊዜ እንዳልመጣ ይሰማቸዋል። እንዲፈውሳቸውና እንዲያበረታቸው እንዲሁም ልጃቸውን በሙሉ ልብ ለመቀበል እንዲረዳቸው እግዚአብሔርን መለመን ይኖርባቸዋል። በዚህም ሕጻን ተፈላጊ መሆኑ እንዲሰማቸው ማድረግ ጠቃሚ ነው። ሕጻኑ ተጨማሪ ዕቃ ወይም የግል ፍላጎት ማርኪያ አይደለም። ሕጻን  ልጅ ትልቅ ዋጋ ያለውና ለግል ጥቅም ሲባል ከቶ ሊገለገሉበት የማይገባ ሰብዓዊ ፍጡር ነው። ስለዚህ ይህ አዲስ ሕይወት ለእናንተ ምቹ ይሁን አይሁን፣ ወይም እናንተን የሚያስደስቱ ባሕርያት ይኑሩት አይኑሩት ወይም ከእናንተ ዕቅድና ምኞት ጋር ይስማማ አይስማማ እምብዛም አይገድም። ምክንያቱም “ሕጻናት ስጦታ ናቸው… እያንዳንዱም ልዩና ምትክ የሌለው ነው… ልጆቻችንን የምንወደው ውብ ስለ ሆኑ እና እኛን ስለሚመስሉ ወይም እንደ እኛ ስለሚያስቡ ወይም የምኞታችን ተምሳሌት ስለ ሆኑ ሳይሆን ልጆች ስለ ሆኑ ነው። የምንወዳቸው ልጆች ስለ ሆኑ ነው። ልጅ ልጅ ነው”። የወላጆች ፍቅር እግዚአብሔር አባታችን የራሱን ፍቅር የሚያሳይበት መንገድ ነው። እርሱ የእያንዳንዱን ሕጻን መወለድ በጉጉት ይጠባበቃል። ያንን ሕጻን ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ይቀበለዋል። በደስታና በነጻነትም ያስተናግደዋል።

እኔም የወደፊት እናቶችን ሁሉ በታላቅ ፍቅር እንዲህ በማለት አበረታታቸዋለሁ፡- ደስተኞች ሁኑ፤ ውስጣዊ የእናትነት ደስታችሁ እንዲወሰድባችሁ አትፍቀዱ። ልጃችሁ የእናንተ ደስታ ያስፈልገዋል። ፍርሃት፣ ጭንቀት፣ የሌሎች ሰዎች አስተያየት ወይም ማናቸውም ችግር አንድን አዲስ ሕይወት ወደዚህች ዓለም ለማምጣት የእግዚአብሔር መሣሪያ የመሆናችሁን ደስታ አይቀንስባችሁ። ለልጃችሁ ልደት ያለ ፍርሃት ተዘጋጁ፤ “ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች፤ መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ትደሰታለች፤ እርሱ የባሪያይቱን ውርደት ተመልክቶአልና” (ሉቃ. 1፡ 46-48) በሚለው በማርያም የውዳሴ መዝሙር ተካፈሉ። ይህን ድንቅ ስሜት በብዙ ጭንቀቶቻችሁ መካከል ለመለማመድ ሞክሩ፤ ወደ ልጃችሁ ታስተላልፉ ዘንድ ጌታ ደስታችሁን እንዲጠብቅላችሁ ለምኑት።

ምንጭ፡ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ በሚል ርዕሥ ለጳጳሳት፣ ለካህናትና ለዲያቆናት፣ ለመነኮሳት፣ ለክርስቲያን ባለ ትዳሮች እና ለምእመናን በሙሉ ያስተላለፉት የድኅረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ምክር ከአንቀጽ 167-171 ላይ የተወሰደ መሆኑን እንገልጻለን።

አዘጋጅ፥ ክቡር አባ ዳንኤል ኃይለ

09 March 2024, 18:05