በሄይቲ ታግተው የነበሩ አራት የካቶሊክ ወንድሞች እና አንድ መምህር ተለቀቁ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ሄይቲ መንግስትን ሊያፈርስ በሚችል የታጠቁ ወሮበሎች ጥቃት ምክንያት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ የምትገኝ ሲሆን፥ ከሁለት ሳምንት በፊት በፖርት-ኦው ፕሪንስ ታግተው ከነበሩት ሰባት ሰዎች መካከል አራት የልበ ቅዱስ ወንድሞች ማኅበር አባላት እና አንድ መምህር ሰኞ ዕለት ሲለቀቁ፥ ሁለቱ ግን አሁንም ድረስ እንዳልተለቀቁ ማህበሩ ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል።
ሁለት የልበ ቅዱስ ማህበር ወንድሞች አሁንም እንደታገቱ ነው
‘ኤስ አይ አር’ በተባለው የዜና ወኪል በኩል የተጋራው ጋዜጣዊ መግለጫው “የታገቱትን ለማስለቀቅ የሚደረገው ትግል አላለቀም፤ ምክንያቱም ወንድም ፒየር አይዛክ ቫልሜስ እና አዳም ሞንትክሊሰን ማሪየስ የተባሉ ሁለት ወንድሞች አሁንም በእስር ላይ ይገኛሉ” በማለት ትግሉ እንደሚቀጥል አሳውቀዋል።
ባለፈው የካቲት 15 ሰባቱ ሰዎች የፖርት-ኦው-ፕሪንስ ከተማ ማዕከል ወደሆነው፣ በወረበሎቹ ቁጥጥር ስር በሚገኘው ቢሴንቴኔሪ ሰፈር ውስጥ ወደሚገኘው ዣን 23ኛ ትምህርት ቤት እያመሩ በነበረበት ወቅት በታጣቂ ቡድን ታግተው እንደተወሰዱ መግለጫው በማስታወስ፥ ለታገቱት ሰዎች የተጠየቀው ገንዘብም ለአጋቾቹ እንደተሰጠ ተጠቁሟል።
በአሁኑ ጊዜ የእገታ ተግባር ሰፊውን የሀገሪቱን ክፍል እያመሰ እንደሚገኝ እና በተለይም አብዛኛውን የመዲናዋን ክፍል ተቆጣጥረው የሚገኙት የወንጀለኞች ቡድን ዋና ስራ ሆኖ መቆየቱን በመግለጫው ተነግሯል።
የሄይቲ ፕሬዝዳንት የነበሩት ጆቨኔል ሞይስ ሃምሌ 2013 ዓ.ም. ከተገደሉ በኋላ በሃገሪቷ የወሮበሎች ጥቃት በአስደናቂ ሁኔታ ጨምሯል። የፕረዚዳንቱ ግድያ በሀገሪቱ የወንጀል ድርጊቶችን በማባባስ ዛሬ ላይ ንፁሀን ዜጎች በየጊዜው ይገደላሉ፣ ይደፈራሉ እንዲሁም ታግተው ገንዘብ ይጠየቃሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኤሪያል ሄንሪ አሁንም ፖርቶ ሪኮ ይገኛሉ
ይህ በእንዲህ እያለ ባለፈው ሳምንት የካቲት 24 ቀን ጠቅላይ ሚኒስትር ኤሪኤል ሄንሪ በሃገራቸው የተከሰተውን የሰላም መደፍረስ ወደ ነበረበት ለመመለስ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሚደገፍ የጸጥታ አስከባሪ ሃይል ለማግኘት የሚቻልባቸውን መንገዶች ለማመቻቸት በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ በነበሩበት ወቅት፥ የታጠቁ ቡድኖች በሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞችን ከማረሚያ ቤት ካስለቀቁ በኋላ ይህች የካሪቢያን ሀገር ወደባሰበት ብጥብጥ ውስጥ ገብታለች።
ይሄን ተከትሎ በሃገሪቷ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቢታወጅም እነዚህ የታጠቁ ወረበሎች በፖሊስ ጣቢያዎች እና በሌሎች የመንግስት ተቋማት እንዲሁም በሆስፒታሎች ላይ ጥቃታቸውን አጠናክረው በመቀጠል ጠቅላይ ሚኒስትር ሄንሪ ከስልጣን እንዲለቁ ጠይቀዋል።
ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስትር ሄንሪ አሁንም ድረስ ፖርቶ ሪኮ ውስጥ እንደሚገኙ የተነገረ ሲሆን፥ የሄይቲን ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያዎችን የተቆጣጠሩት ወረበሎቹ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፖርት-ኦው-ፕሪንስ እንዳይገቡ ከልክለዋል።
ሁኔታው እየተባባሰ ባለበት በአሁኑ ወቅት ዩናይትድ ስቴትስ በሄይቲ የሚገኙ የኤምባሲ ሰራተኞቿን ከአገሪቱ በአውሮፕላን ለማስወጣት እንደወሰነች እንዲሁም የኤምባሲውን ደህንነት ያጠናከረች ሲሆን፥ በሄይቲ የሚገኘው የአውሮጳ ህብረት ልዑካንም ቢሮውን ለጊዜው በመዝጋት በኤምባሲው ውስጥ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ መገደባቸውን ገልጸዋል።
‘ካሪኮም’ የተባለው ህብረት በሄይቲ ጉዳይ ዙሪያ ለመወያየት በጃማይካ ተሰባስበዋል
‘ካሪኮም’ (CARICOM) ተብሎ የሚታወቀው የካሪቢያን ሃገራት መሪዎች ህብረት በሄይቲ ጉዳይ ዙሪያ ለመወያየት ሰኞ ዕለት በጃማይካ የተሰባሰበ ሲሆን፥ በሃገሪቱ ሰፊ መሰረት ያለው፣ ገለልተኛ እና ፕሬዝዳንታዊ አገዛዝ እንዲኖር እንዲሁም ዓለም አቀፍ የጸጥታ ሃይል ማሰማራት በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያ ተወያይተዋል። የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከንም በውይይቱ እየተሳተፉ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ስለ ሄይቲ ያላቸው ስጋት
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በሄይቲ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታዎችን በአንክሮ እየተከታተሉ ሲሆን፥ እሁድ ዕለት በነበረው የመልአከ እግዚያብሄር ጸሎት ወቅት በሃገሪቷ ለሚገኙ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት እና ለዓመታት ሲሰቃዩ ለነበሩት የሄይቲ ህዝብ ሁሉ ያላቸውን ቅርበት ገልጸዋል። ብጹእ አባታችን በሄይቲ የተፈጠረው አለመረጋጋት ማብቂያ እንዲያገኝ ሁሉም ምዕመን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነትን እንዲጸልይ ጠይቀዋል። በተጨማሪም ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በሚደረገው ድጋፍ ሰላምና እርቅ እንዲሰፍን ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ አሳስበዋል።