የፈረንሳይ ብጹአን ጳጳሳት መንግስት ያወጣውን 'ህይወት የማቋረጥ' ረቂቅ ህግን ተቃወሙ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን “ህይወት ማቋረጥን” በማስመልከት የተዘጋጀውን ረቂቅ ህግን አስመልክተው “የወንድማማችነት አብዮት” ብለው ያደረጉትን ንግግር በመቃወም የፈረንሣይ ብጹአን ጳጳሳት “ወንድማማችነትን አታዛቡ” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።
ሰኞ፣ መጋቢት 9 ቀን 2016 ዓ.ም. 100 የሚጠጉ የፈረንሳይ ጳጳሳት በሉርዴስ በተካሄደው የምልአተ ጉባኤ የመጀመሪያ ቀን ውሎ በረቂቅ ህጉ ላይ ጠንካራ ተቃውሟቸውን ገልጸዋል።
ይህ የብጹአን ጳጳሳት የተቃውሞ መግለጫ መጋቢት 10፣ ማክሰኞ ዕለት ታትሞ የወጣ ሲሆን፥ በተመሳሳይ ቀን ረቂቅ ህጉ ለሃገሪቱ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለግምገማ ቀርቧል።
ለማስታገሻ ህክምና ቅድሚያ መስጠት
ጳጳሳቱ በመግለጫቸው እንደጠቀሱት የብሔራዊ የምክክር ሥነ ምግባር ኮሚቴ የውሳኔ ሃሳቦችን በመከተል “የፈረንሳዊያን ባህል የሆነውን ተፈጥሯዊ ሞትን ለመሞት እና ለህመም ማስታገሻ ህክምናዎች ቅድሚያ መስጠት” እንደሚያስፈልግ በቁርጠኝነት ገልጸዋል።
የጳጳሳት ጉባኤው በተጨማሪም የፈረንሳይ ካቶሊኮች ከአካል ጉዳተኞች፣ ከአረጋውያን ወይም የሞት አፋፍ ላይ ካሉ ሰዎች ጋር ተገናኝተው እንዲንከባከቧቸው ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
ጳጳሳቱ “በእርዳታ ራስን ማጥፋት ወይም ‘ኢውታናዥያ’ የሚባለው ከስቃይ ለመገላገል በሌላ ሰው እርዳታ ህይወትን የማቋረጥ ጥያቄ ብዙውን ጊዜ የብቸኝነት እና የመረሳት ስሜት መግለጫ ሲሆን ይህም እኛ በራሳችን የማንችለው ጉዳይ እንደሆነ እና እራሳችንን መተው እንደማንችል ግልጽ ነው” ሲሉ ጳጳሳቱ አስረድተዋል።
በማርያም እና በኢየሱስ እቅፍ ውስጥ በክብር በመሞቱ የ“ሰላማዊ ሞት” ጠባቂ ተብሎ የሚጠራው የቅዱስ ዮሴፍ ክብረ በዓል በምናከብርበት ወቅት፥ የፈረንሳይ ብጹአን ጳጳሳት በሚቀጥለው ወር በኮሚቴ በሚከፈተው የፓርላማ ውይይት ላይ የራሳቸውን ተጽእኖ እንደሚያሳድሩ ተስፋ አድርገዋል።
የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ስለ ረቂቅ ሰነዱ ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ ‘የኢፎፕ-ፊዱሺያል ኢንስቲትዩት’ ከሱድ ራዲዮ ጋር በመተባበር ባደረገው ጥናት 81% የሚሆኑ ፈረንሳውያን ረቂቅ ሰነዱን እንደሚደግፉ ለማወቅ ተችሏል።
ለተጎጂዎች ድጋፍ
በዚህ ምልአተ ጉባኤ ላይ ብጹአን ጳጳሳቱ በብዙ አጀንዳዎች ላይ እንደሚወያዩ የሚጠበቅ ሲሆን፥ ከነዚህም ውስጥ ቤተክርስቲያኒቷ በመዋቅሮቿ ሥር ጉዳት ለደረሰባቸው ተጎጂዎች በምታደርጋቸው ድጋፍ ዙሪያ እየወሰደች ያለውን እርምጃዎች ለመከታተል በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ሰፊ ውይይት እንደሚያደርጉም ይጠበቃል። በተጨማሪም ከብሔራዊ ቀኖናዊ የወንጀለኛ መቅጫ ልዩ ፍርድ ቤት አባላት ጋር የሚወያዩበት መድረክም ተዘጋጅቷል።
ከብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ የሚጠበቀው ለተጎጂዎቹ ተብሎ የተቋቋመው የብሔራዊ ገለልተኛ እውቅና እና ካሳ ሰጪ ኮሚሽን (INIRR) የስልጣን ጊዜ ላይ እና እንዲሁም በቤተክርስቲያን ውስጥ በሚደርስባቸው በደል ሰለባ የሆኑ ጎልማሶችን ለመደገፍ የሚቻልባቸውን መንገዶች ላይ ውሳኔ ያስተላልፋል ተብሎ ይጠበቃል።
የፈረንሳይ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት የሆኑት ብጹእ አቡነ ኤሪክ ደ ሙሊንስ ቤውፎርት በመክፈቻ ንግግራቸው ላይ እንደተናገሩት “የፈረንሳይ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በመካከለኛ እና ለረጅም ጊዜ የተሾመ አገልጋይም ይሁን ኃላፊነት ያለበት የተቋሙ ሰራተኛ ባህሪ ወይም ድርጊት በቁም ነገር የሚመለከት ማንኛውንም ቅሬታ መስማት መቻል አለባት” ሲሉ አረጋግጠዋል።
ዲያቆናት እና የክህነት ተማሪዎች
“ቤተክርስቲያኒቷ በዚህ ዓመት በምታከብረው 60ኛ ዓመትን” ምክንያት በማድረግ በፈረንሣይ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ካሉት የተለያዩ አገልግሎቶች ውስጥ በሳምንት ለሁለት የሥራ ሰዓታት በቋሚ ዲያቆናቱ ትምህርት እንደሚሰጥ ብጹእ አቡነ ኤሪክ ደ ሞሊንስ-ቢፎርት አጽንኦት ሰጥተው በመግለጽ፥ ይህ የስነ-መለኮት ጥናት ቋሚ ዲያቆናቱ በቤተክርስቲያኗ አገልግሎት ውስጥ ያላቸውን ተልእኮ ለማክበር መንገድ ይሆናል ብለዋል።
ብጹእነታቸው በማከልም “ቋሚ ዲያቆናቱ ሃዋሪያዊ ሥራቸውን በትጋት እንዲሰሩ ለረዷቸው እና አሁንም ድጋፍ እያደረጉላቸው የሚገኙ ሚስቶቻቸውን፣ ልጆቻቸውን እና የልጅ ልጆቻቸውን እናመሰግናለን” ብለዋል።
በተጨማሪም ተቋማዊ አገልጋዮችን በተመለከተ፣ ጳጳሳቱ የካቴኪስቶች አገልግሎት ላይ ወጥ የሆነ ውሳኔ ይሰጣሉ ተብሎም ይጠበቃል።
የፈረንሣይ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት እነዚህ “የተቀቡ ካህናት ወይም የተቋቋሙ አገልጋዮች በእውነት የእግዚአብሔር ስጦታዎች ናቸው፣ ከሞት የተነሳው የክርስቶስ ስጦታዎች ናቸው” ብለው ስለሚያምኑ ይህንን ጉባኤ የምስጋና ማቅረቢያ መንገድ አድርገው ይመለከቱታል።
በርካታ ማሻሻያዎች ተደርገዋል
በመጨረሻም የፈረንሳይ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት ይህ ጉባኤ በፈረንሳይ ቤተክርስትያን አደረጃጀት ላይ በተደረጉ የተለያዩ ለውጦች ላይ ድምጽ መሰጠቱን አስታውቀዋል።
ከእነዚህ ውሳኔዎች አንዱ ብጹእ አቡነ ፍራንሷ ቱቬት እና የኮሙዩኒኬሽን ምክር ቤት ያከናወኑት ሰፊ ስራን ተከትሎ የክርስቲያን ሬዲዮዎችን የወደፊት ሁኔታ አንዱ እንደሆነም ተገልጿል። በመሆኑም ውሳኔ ሊወስኑ ለሚገባቸው ጳጳሳት ሪፖርት ቀርቧል። የሪምስ ሊቀ ጳጳስ ይህን በማስመልከት እንደተናገሩት “ይህን ሪፖርት በጋራ ገምግመን ውጤቱን መግለጽ አስፈላጊ ነው” ብለዋል።
ጉባኤው በተጨማሪም አዲሱን የተቋማዊ ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ የሆኑትን ሴሊን ሬይናድ-ፎርቶንን ተቀብሎ ያነጋገረ ሲሆን፥ የመምሪያው ተግባር የመንግስት ተነሳሽነትን መከታተል እና ከሲቪል ማህበረሰብ ጋር ያለውን ግንኙነት ማጠናከር እንደሆነም ተገልጿል።
የፈረንሳይ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት ስለ መምሪያው ጠቀሜታ ሲገልጹ “ከተለያዩ የኩባንያዎች ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር የተደረጉት ጥቂት ስብሰባዎች የኩባንያዎቹ ውሳኔ ሰጪዎች ስለ ጉባኤያችን እና ስለ አሠራሩ ምንም እንደማያውቁ እንዳስተውል አድርገውኛል” ብለዋል።
ይህ አዲስ ተቋም በመጨረሻ ጉባኤውን በንኡስ ሴክተሮች እንደገና እንደሚያደራጅ እና ከእነዚህ ውስጥ ሦስቱ በጳጳሳዊ ኮሚሽኖች እንደሚመሩ ያሳያል ተብሏል።
የዘንድሮው ምልአተ ጉባኤ መጋቢት 23፣ ዕለተ ዓርብ ላይ እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል።